Skip to main content Scroll Top

መስቀል

PostFeaturedImage_KibreQidusan_Final (6)

የመስቀል ትርጉም፦ መስቀል ማለት በመንፈሳዊ (ግብራዊ) ትርጉሙ ፦ መከራ ማለት ሲሆን አካላዊ /ፊደላዊ   ትርጉሙ ደግሞ የተመሳቀለ ን የሚመስል ማለት ነው ።

መስቀል ቅድመ ክርስትና፦ መስቀል በስቅለት ተቀጥተው ከሚሞቱ ወንጀለኞች ታሪክ ጋር የተያያዘ ታሪክ ነበረው ። መስቀል ቅድመ ክርስቶስ በምድረ አሕዛብ የታወቀ የክፉዎች መስቀያ ፣ መከራ ስቃይ እንዲበዛበት ፣ ውርደት እንዲሰፍንበት የፈለጉትን ሰው በሞት መቅጣት አልበቃቸው ፣ ትኩሳታቸውን አላበርድላቸው ስላለ ሞቱ አይበቃም እና የስቃይ ሞት ይሙት ብለው የፈረዱበት ሰው አሰቃይቶ በውርደት ሞት ለመግደል ሮማውያን እና ሌሎች መሰል አሕዛብ ለፍርድ መሣሪያነት ይጠቀሙበት ነበር ። መምለክያነ ጣዖት የሆኑት የአሕዛብ የምድር አምላክ እንዳይቆጣ ፣ የክፉ ሰው ደም እንዳይነካው ብለው በመስቀል ላይ ይቀጡ ነበር ይባላል ። ለነሱ ስለ መሰላቸው ነው እንጂ ያ ሰው የሚቀበረው ከተፈጠረበት ምድር ላይ በመሆኑ ክፉውንም ያስተማረው ሰይጣን በመሆኑ በሞቱ አብረው ነው የሚኖሩት ። አይሁድም ከአሕዛብ ያን ባህል ወርሰው  ሟቹን ለማሰቃየት በመስቀል ሰቅለው ይገድሉት ነበር ። በሮማውያን ተገዝተው የአሕዛብን ሥርዐት ሥርዐታቸው እስኪያደርጉ ድረስ ከመስቀል ይልቅ በድንጋይ ውግረት ይቀጡ ነበር ። ዘዳ 21 ፥ 21-23 ፤ ኢያ 10 ፥ 26 ። የሐዋ 7 ፥ 58 ።

የመስቀል ሞት የውርደት ሞት ነው ። ክርስቶስ እኛን ያከብር ዘንድ  በመስቀል ሞተ ። ፊል 2 ፥ 8 ፤ ዕብ 12 ፥ 1-2 ።

የኃፍረት ሞት ነው ። ክርስቶስ የዓለምን ኃፍረት ይጋርድ ፣ የተዋረዱትንም ያከብር ዘንድ ስለ መጣ በመስቀል ላይ ሞተ ። በመስቀል ተሰቅሎ የሚሞት የተረገመ ነበር ። ገላ ፥ 3-13 ።

ክርስቶስ ግን መርገመ ሥጋችንን እና መርገመ ነፍሳችንን ይሽር ዘንድ በመስቀል ላይ ሞተ ። ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ሞትን ገድሎ ፣ ጥልን ገድሎ ለሰው ልጆች ሕይወትን አድሎ በትንሣኤው ብርሃን በመገለጡ መስቀል የድል ፣ የሕይወት ፣ የክብር ፣ የነጻነት ፣ የአሸናፊነት ግርማ ሆነ ።

ሰዎች ክርስቶስን ወንጀለኛ ነው ለማለት በአደባባይ ከወንጀለኞች መካከል ሰቀሉት ። እርሱም መጽሐፍ “ተኈለቈ ምስለ ጊጉያን” «ከበደለኞች ጋር ተቈጠረ» ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ በመስቀል ከነፍሰ ገዳዮች ጋር ተሰቀለ ። ነገር ግን የሰው ልጆች በሱ (በእርሱ) ከወንበዴዎች መካከል መሰቀል ከማኅበረ አጋንንት ወጡ ። ከማኅበረ መላእክትም ተጨመሩ ። በመሆኑም የመስቀሉ ቃል የሕይወት መልእክት ሆነ ። 1ቆሮ 1 ፥ 17-25 ፤ ቈላ 1 ፥ 19-20 ።

የጥል ግድግዳ የወደቀበት የዕርቅ መሣሪያ ሆነ ። ኤፌ 2 ፥ 14-16 ።

መስቀል ከክርስቶስ ሞትና ትንላ፦ የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት መስቀል የእግዚአብሔር ኃይል ይገለጥበት ጀመር ። ዕውራን መስቀሉን ሲዳስሱ ዐይናቸው በራ ። ሙታን በመስቀሉ ኃይል ሕይወት አገኙ ። በዚህ ጊዜ የመሲሕ ገዳዮች ጻድቁን እንደ ገደሉ እንዳይ ታወቀባቸው በመስቀሉ የሚደረጉትን ተአምራቶች እንደ ጦር ፈሩአቸው ። በመሆኑም ስሙን የሚጠሩትን ፣ በስሙ የሚሰብኩትን ፣ በስሙ ኃይል የሚያደርጉትን ሐዋርያት እና ቤተ ክርስቲያን በእስራት እና በሞት ከፊታቸው እንዲወገዱ ጥረት ሲያደርጉ መስቀሉንም በስውር ቦታ ጣሉት ። በተቻላቸው መጠን የገደሉትን መሢህ በክብር እንዳይገለጥ ጥረት አደረጉ ። ነገር ግን የክርስቶስ ክብር ዕፀ መስቀሉም ቢቀበር አብሮ የማይቀበር ፣ ሐዋርያት ቢታሰሩ አብሮ በእስር ቤት የማይወሰን ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በሰይፍ ብትመታ ስለት የማይዳፈረው መለኮታዊ ኃይል በመሆኑ ወንጌል እየሰፋ የመሢሕ ምስክሮች ቍጥር እየጨመረ ሄደ ። በመስቀሉ ላይም የወሰዱት እርምጃ ለተወሰነ ጊዜ ሠምሮላቸው ነበር ። ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ዕፀ መስቀሉ ከቤተ ክርስቲያን ፊት ተወስዶ ነበር ። ነገር ግነ የተሰቀለው ክርስቶስ ሁል ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ፊት ነበር ። በኋላ ታሪክ እንደሚነግረን በንግሥት እሌኒ ጥረት የተጣለው መስቀል ተነሣ ፣ የተሰወረው መስቀል ተገለጠ ፣ የጠፋው የድል አርማ መስቀል መጋቢት አሥር ቀን ተገኘ ። በቤተ ክርስቲያንም በኢየሩሳሌም አሳንጻ በዚያ አስቀመጠችው ። መጋቢት 10 ቀን ዓቢይ ጾም ላይ ስለሚውል ክብረ በዓሉ በቅዳሴ ቤቱ መስከረም 17 እን እንዲሆን ተወሰነ ። ስለዚህ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ስለኛ የተሰቀለበት መስቀሉን መገኘት ምክንያት በማድረግ በመስቀሉ የፍርድ ጨለማውን እንዳራቀ ሁሉ በአዲስ ዓመት ክረምቱ አልፎ  የፀሐይ ዘመን በወሚመጣበት በመስከረም «መስቀሉን አበራ ፣ ሰማይንም በከዋክብት አስጌጠ ፣ ከሁሉ ይልቅ ፀሐይን አሳየ (እንዲወጣ አደረገ) እያለች በቋንቋዋ = መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሰርገወ ሰማየ እም ኩሉሰ ፀሐየ አርአየ” እያለች ታከብረዋለች።

በንግሥት እሌኒ አድሮ መካነ መስቀሉን የገለጠውን ፣ መስቀሉን የኃይል ምንጭ ያደረገውን ፣ ለኛም ዘመኑን ለውጦ ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋግሮ ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ የጠራ ሰማይ የተዋበች ፀሐይን እንድናይ ያደረገውን አምላክ ቤተ ክርስቲያን ታከብራለች ። በመሆኑም በዚህ ዕለት የመስቀሉን መገኘት ምክንያት በማድረግ ታላቅ በዓል እናደርጋልን ።

 

ዕፀ መስቀሉ በኢትዮጵያ  

በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በግሸን ማርያም መቀመጡን ታሪክ ይመሰክራል ። በመሆኑም መስከረም 21 ቀን ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ግሸን ማርያም በመሄድ የመስቀሉን በዐል በታላቅ ሥነ-በዓል ያከብራሉ ። ይህም ለሁላችን የታደለ ታላቅ በረከት በመሆኑ ደስ ሊለን ይገባል ።

የሀገራችን ታሪክ እንዲህ ይላል ። “ዳዊት ካልዕ ወልዱ ለሰይፈ አርእድ ነግሠ 20ወ9ተ ዓመት ። ወበመዋእሊሁ መጽአ ዕፀ መስቀሉ ለክርስቶስ ወገብረ ፍሥሐ ወአሰርገዎሙ ለካህናት ካፓ ወአጽገየ” ።

አማርኛ፦ “ሁለተኛው ዳዊት የአጼ ሰይፈ አርእድ ልጅ 29 ዓመት ነገሠ ። በዘመነ መንግሥቱም የጌታችን ዕፀ መስቀል (ግማደ መስቀል) መጣ ። ታላቅ ደስታ (ሥነ-በዓል) አደረጉ ካህናቱንም በካባ አስጌጣቸው…” (የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ)

መልእክት፦ ዛሬም እንደ እሌኒ የተቀበረውን መልካም ነገር የሚፈልጉ የክፎዎችን ምክር የሚያርቁ ልጆችን ቤተ ክርስቲያን ትሻለች ። የዛሬው ትውልድ በማወቅ ይሁን ባለማወቅ በብዙ መልካም ነገሮች ላይ አራሙቻ ጥሎ እያለፈ የአይሁድን ሥራ እንዳይደግም ያስፈራል ። ሁላችንም የተሰቀለው የክርስቶስ ክብር እንዲገለጥ መስቀሉ አላማችን ፣ ወንጌሉ ከተማችን ይሁን ። የተሰወረውን የምንገልጥ ያልታየውን የምናሳይ የመልካም ነገር መሣሪያዎች ያድርገን ።

“መስቀል ኃይልነ ፥ መስቀል ጽንዕነ ፥ መስቀል ቤዛነ ፥ አይሁድ ክህዱ ንህነሰ አመነ ፥ ወእለ አመነ መስቀሉ ድኅነ”

የቀረውን ሥርዓተ አምልኮ ክፍል አንድ መጽሐፍ ላይ ይመልከቱ

የመስቀሉ ኃይል ይጠብቀን አሜን ።

Leave a comment