ሰሙነ ሕማማት ከትንሣኤ በፊት ከሆሣዕና ጀምሮ ያለው ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ስያሜዎች አሉት ። ከነዚህም መካከል የተለመዱት ፦
1ኛ ሰሙነ ሕማማት ።
2ኛ የመጨረሶው ሳምንት ።
3ኛ ቅዱስ ሳምንት ። የሚሉት ናቸው ።
ይህ ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙና ሞቱ የሚታሰብበት ሳምንት ነው ። በዓመተ ፍዳ ማለትም እንደ ቤተ ክርስቲናችን አቈጣጠር ከክርስቶስ ሰው መሆን በፊት ባለፉት ዓመታት የነበረውን የሰዎችን ሕማምና ሞትም እናስብበታለን ። ክብር ይግባውና ጌታችን የታመመው የሰዎችን ሕማም ፥ የሞተውም ስለ ሰዎች ኃጢአት ነውና ። ስለዚህ ሰሙነ ሕማማት ይባላል ። ካሳ ያልተፈጸመበትን ዘመን ለማስታዎስ አንድ አንድ ሥርዓታተ ቤተ ክርስቲያን አይፈጸሙበትም ። ሰሙነ ሕማማት ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣበትና የማዳን ሥራውን ስላጠናቀቀበት ደግሞ የመጨረሻው ሳምንት ይባላል ። ደመ ክርስቶስ ፈስሶ ዓለም የተቀደሰበት ሳምንት በመሆኑም ቅዱስ ሳምንት ይባላል ።
ሰሙነ ሕማማት እስከ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ከዐቢይ ጾም ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር ፤ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም ፥ ሰሙነ ሕማማትም ፥ ትንሣኤም ፥ በተከታታይ እንዲውሉ ተደርጓል ። ምዕራባውያን ከ40 ጾም የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይሉታል ፤ በምሥራቃውይን ግን 40 ቀን ካለቀ በኋላ ያለውን ተከታይ ሳምንት ሰሙነ ሐማማት እናደርጋለን ፤ የሰሙነ ሕማማት መጀመርያም የሆሣዕና እሑድ ነው ።
1ኛ, እሁድ ሆሣዕና «ሆሣዕና» በዕብራይስጥ«ሆሼዕናህ» የሚል ሲሆን ትርጉሙም «እባክህ አሁን አድን» ማለት ነው ፤ ቃሉ በብሉይ ኪዳን የታወቀ ነበር ፤ የግዝ አቻ ቃል «ኦ እግዚኦ አድኅን ሶ» የሚለው ነው ። መዝ117 ፥ 26 ።
የሆሣዕና በዓል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትም የሚከተሉትም ሕዝብ አእሩግና ሕጻናት «ሆሳዕና በአርያም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው» በማለት ነበር ። ማቴ 21 ፥ 1-11 ።
ስለዚህ በዕለቱ በተዘመረው መዝሙር ዕለቱ «ሆሣዕና» ይባላል ። የሚያመሰግኑት በእጃቸው የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው «ሆሣዕና በአርያም» እያሉ ይዘምሩ ስለ ነበር ዕለቱ የዘንባባ /ጸበርት/ እሑድ እየተባለም ይጠራል ። በዚህ ዕለት የተከናውነውን ትምህርትና ተአምራት ፣ እንዲሁም ታሪክ ለመረዳት በአራቱ ወንጌላውን የተጻፈውን ክፍል እናንብብ ። ማቴ21 ፥ 1-11 ። ማር11 ፥ 1-10 ። ሉቃ 19 ፥ 28-40 ። ዮሐ12 ፥ 12-26 ።
የተናቀችን ነፍስ የሚያከብር መሆኑንም ለማጠየቅ በአህያ ጀርባ ንጉሠ ሰላም ሁኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል ። ለጦርነት ስላልመጣ በፈረስ ላይ ሳይሆን በአህያ ላይ ተቀምጦ ነው ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ። የታሰሩትን ለመፍታት የመጣው ጌታ ከእስራት በቃሉ ባስፈታቸው አዕዱግ ጅርባ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ ። /የቀረውን በሆሣዕና እሑድ ትምህርት ላይ ይመልከቱ/ ።
2ኛ-ሰኞ በማርቆስ አገላለጽ መሠረት ፣ በሆሣዕና ማግስት ሰኞ ጌታ ዳግመኛ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቷል ። እሑድ የሆሣዕና ዕለት ጊዜው መሽቶ ስለ ነበር በማግስቱ ማለትም በዚሁ ዕለት ሰኞ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ሁለት ነገሮችን አድርጓል ። እነሱም፦
ሀ) ቅጠል እንጂ ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟታል ፣
ለ) ወደ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል ፣ ይህንንም በተመለከተ በሦስቱም ወንጌላውን ትምህርቱም ፥ ታምራቱም ፥ ታሪኩም ፥ ተሟልቶና ተብራርቶ ተጽፋል ። ማቴ 21 ፥ 12-17 ። ማር 11 ፥ 17 ። ሉቃ 19 ፥ 45-46 ።
በቤተ ክርስቲያን ይህ ሰኞ የዚህ ታሪክ መታሰቢያ ነው ፦ ዛሬስ ቢሆን ጌታ ወደ እኛ ሕይዎት ሲመጣ የሚያገኘው ምንድር ነው ? ፍሬ ወይስ ቅጠል ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ ይለናል ። ማቴ 2 ፥ 8 ።
ስለዚህ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የሃይማኖት ፍሬ /በገላትያ መልእክት ላይ የተዘረዘሩትን የመንፈስ ፍሬዎች ይዘን ልነገኝ ይገባል። ገላ 5 ፥ 22 ።
3ኛ/ ማክሰኞ በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል ፤ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆች እና የሕዝብ አለቆች ሲሆኑ ጥያቄውም በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው ? የሚሉ ነበሩ ። ነገር ግን ጥያቄያቸው ለፈተና የቀረበ ስለ ነበር ጥያቄያቸውን በጥያቄ መልሶ አሳፍሯቸዋል ። መድኃኒታችን ከዚህ ጥያቄ ጋር አያይዞ ረጅም ትምህርት በቤተ መቅደስ ሰጥቷል ። ይህም ትምህርት በሦስቱም ወንጌሎች ተጽፏል ። ማቴ 21 ፥ 23-25 ። ማር11 ፥ 21 ፥ ሉቃ 20 ፥ 1-8 ።
ዛሬም ቢሆን ሥራ በሠራን ቊጥር አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ተፈታታኝ ጥያቄዎችን እንደሚያቀርቡልን ልንገነዘብ ይገባል ። እንዲሁም ፈታኝ ጥያቄዎች የመከራ ዋዜማ ናቸው ። ይህንን አስቀድመን ካወቅን ደግሞ በመከራ ሰዓት እንኳን በልበ ሙሉነት እውነትን ለመናገርና ለሚቀርበው ጥያቄ ሁሉ ተገቢውን መልስ በመስጠት ሥራችንን መሥራት እንችላለን ።
4ኛ/ረቡዕ በማቴዎስና በማርቆስ ወንጌላት እንደ ተጻፈ ፣ በዚህ ዕለት ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ተከናውነዋል ።
1) የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች በጌታ ላይ ተማክረዋል ፣ 2) ጌታ በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት ሴት ሽቶ ቀብታዋለች ፣ 3) ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ለመስጠት ወደ ካህናት አለቆች ሲሄድ 30 ብር ሰጥተውታል ፣ አይሁድ «ሲንድርየም» በመባል የሚታወቅ ሸንጎ ነበራቸው ፣ አብዛኛቹ ሰዱቃውያን ሲሆኑ ጥቂቶቹ ጻፎችና ፈሪሳውያን ነበሩ ። እነሱውም ቀያፋ በሚባል ሊቀ ካህናት ግቢ ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር ። ይህም ሸንጎ 72 አባላት የነበሩት ሽንጎ ነበር፣ እነሱም ተሰብስበው ኢየሱስን በተንኮል አስይዘው እንዴት እንደሚያስገድሉት ተማከሩ ፤ ይህን ባወቀ ጊዜ ነበር ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ የገንዘብ ፍቅር ስላሸነፈውና ከረጢት ይዞ ከሚገባው ገንዘብ ሁሉ እየሰረቀ የሚዎስድ ሌባ ስለ ነበር የምትፈልጉትን ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኝ አላችሁ ? ብሎ ጠየቀ ። እነሱም ሠላሳ ብር ሊሰጡት ተስማሙ ።
ይሁዳ ይህንን ያደረገው ጌታ በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የሆነ የአልባስጥሮስ ሽቱ ከቀባችው በኋላ ነበር ፤ ያንጊዜ ሽቶውን ሽጦ ገንዘቡን ለራሱ ይፈልገው ስለ ነበር ለምን ተሽጦ ለድሆች አልተሰጠም ብሎ ጌታን ሲጠይቀው ስላልተ ቀበለው በመቆጣት ነበር ። በዚህ ምክንያት 30 ብር ከአይሁድ ካህናት ተቀብሎ ጌታን አሳልፎ ሰጠው ። ይህም ታሪክ በአራቱም ወንጌላት ተገልጧል ። ማቴ 26 ፥ 3-16 ። ማር 14 ፥ 1-11 ። ሉቃ 22 ፥ 1-6/ ። ዮሐ 12 ፥ 3- 8 ።
ከዚህ ታሪክ ዛሬም ብዙ እንማራለን ክርስቲያኖች ነን እያሉ እምነታቸውንና የቆሙበትን እውነት በገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም ቢሆን እንደ ይሁዳ ጌታን እየሸጡት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል ። ለድሆች መመጽዎት ተገቢ ተግባር ነው ። ነገር ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ንብረት በመግፈፍ ለግል ጥቅም ማዋል ኃጢአት ነው ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ሰዎችን ለችግር ፣ ባልንጀራውን ለመከራ ፥ ለሥቃይ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም ፣ እኛ ግን ራሳችንን ለገንዘብ ሳይሆን ለእውነትና ለእምነታችን ለባልንጀራችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባል እንጂ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጎ ምቹ ሆነን መገኘት የለብንም ።
5ኛ/ ሐሙስ በሕማማት ውስጥ ያለው ይህ ሐሙስ በተለያዩ
ስያሜዎች ይጠራል ።
1.) ጸሎተ ሐሙስ ይባላል ምክንያቱም፦
ሀ/ ጌታ ኅብስቱን በባርከ ጊዜ ስለ ጸለየ ፣
ለ) በዮሐ 17 ያለውን ጸሎት ስለ ጸለየ ።
ሐ) በጌቴ ሴማኒ ስለ ጸለየ ነው ።
2.) የትእዛዝ ሐሙስ ይባላል ምክንያቱም፦
ሀ) ከሕጽበተ እግር በኋላ ጌታ «እናንተም እንዲሁ አድርጎ»
ብሎ ስላዘዘ ነው ።
ለ) በጌቴ ሴማኒ ጌታ« ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ» ብሎ ስላዘዘ ፣
ሐ) ሥርዓተ ቊርባንን ከሠራ በኋላ «ከመዝ ግበሩ ተዝካርዬ» ብሎ ስላዘዘ ፣ እንዲሁም ሌሎችንም የሐዲስ ኪዳን ትእዛዛት ለማስታዎስ ነው ።
1) የነጻነት ሐሙስ ይባላል ምክንያቱም፦
«ከእንግዲህ ወዲህ ባሪያዎች አልላችሁም ወዳጆች ግን ብያችሁአለሁ» ያለውን የነጻነት ቃል ለማስታዎስ ነው ። ዮሐ 15 ፥ 15 ። 1ጴጥ 2 ፥10 ።
2) ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል ምክንያቱም፦
በዚህ ቀን የደቀ መዛሙርቱን እግር ስለ አጠበና ‹እናንተም እንዲህ አድርጉ› ብሎ ባዘዘንም መሠረት ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን መታሰቢያ ስለሚደረግ ነው ።
3) የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል ምክንያቱም፦
በዚህ ቀን ምሽት ጌታ «ይህ የሐዲስ ኪዳን ደሜ» ነው በማለት የሰጠንን ዘለዓለማዊ ኪዳን የሚያስታውስ ነው ፤ እስከ አሁን በስያሜው እንደ ተመለከትነው በዚህ ዕለት የተፈጸሙት ክንውኖች /ድርጊቶች/ በወንጌላት እንደሚከተለው ተገልጸዋል ።
ሀ) የፋሲካ ዝግጅት ተደረገ
ለ) ከፋሲካው በዐል ጋር ጌታ ሥርዓተ ቊርባንን ሠራ ፣
ሐ) በዮሐ 17 ያለውን ጸሎት በጌቴ ሴማኒ ጸለየ ፣
መ) በዚህ ዕለት ይሁዳ ጌታን አሳልፎ ሰጠው ወታደሮችም ያዙት/ ማቴ 26 ፥ 11-46 ። ማር14 ፥ 12- 52 ፣ ሉቃ 22 ፥ 1-53 ፣ዮሐ 18 ፥ 1-12/ ይመልከቱ ።
ሠ) በዚህ ቀን ጌታችን ፍጹም ትሕትናውን ለመግለጽ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ ። ዮሐ13 ፥ 4-17 ።
ረ) በዚህ ዕለት ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ረጅም የማጠቃለያ ትምህርት አስተምሯል ። የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ አራትና አሥራ ስድስትን በሙሉ ይመልከቱ ።
ይህ ቀን ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የነበረበት የመጨረሻ ቀን ነበር ። ስለዚህ በጸሎቱ ያደረጋቸው ነገሮች ፍቅሩ የተገለጸባቸው ክንውኖች ናቸው ። ስለዚህ ሁኔታ ዮሐንስ «የወደዳቸውን እስከ መጭረሻው ወደዳቸው» ሲል ጽፏል ። ዮሐ 13፥1 ።
በዚህ ቀን ከሐዋርያት ጋር ጸልዮአል ፣ እግራቸውን አጥቧቸዋል ፣ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዐተ ቊርባን መሥርቶላቸዋል ፣ ሕይወቱንም ስለ ሁሉ አሳልፎ ለክፉዎች እጅ በመስጠት ፍቅሩን ገልጧል ።
6ኛ/ ዓርብ በሕማማት ሳምንት ያለው ይህ ዓርብ «የስቅለት ዓርብ» በመባል ይታዎቃል ፣ መድኃኒታችን ስለ ዓለም ኃጢአት መሰቀሉና መሞቱ የሚታሰብበት ዕለት ነው ። በሌላ መልኩ ደግሞ ክርስቲያኖች መልካሙ ዓርብ እያሉ ይጠሩታል ። ዓለም ሁሉ የዳነበት ዕለት ስለሆነ ነው ፤ ሐሙስ ማታ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይ ሳለ በጭፍሮች ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስኪሰቀል ድረስ ብዙ መከራ ተቀብሎአል ፣ ሞቱም በመስቀል በመሆኑ በጣም ከባድ ሞት ነበር ፤ አራቱ ወንጌላውያን ከሐሙስ ማታ እስከ እሑድ ጧት ማለትም ከመያዙ እስከትንሣኤው ያለውን በሚያስደንቅ ሁኔታ ጽፈውታል ፤ በወንጌላት የተገለጹት ዋና ዋና ነገሮችም ከዚህ የሚከተሉት ናቸው ፦
በጽባሕ
1) በሊቀ ካህናቱ ፊት በሃይማኖት ክስ በሐሰት አስመሰከሩበት ፣
2) ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡትና በፖለቲካ በሐሰት በአውደ ጲላጦስ አስመሰከሩበት ፤
3) ጲላጦስ ወደ ገሊላው ገዥ ወደ ሄሮድስ ላከውና በዚያ ተጠየቀ ፣
4) ሄሮድስ ንቆ ወደ ጲላጦስ መለሰው ፣ ጲላጦስም መረመረው ፣
በሠለስት
5) ጲላጦስም በርባንን ፈትቶ ኢየሱስን ግን ገርፎ ይሰቀል ዘንድ አሳልፎ ሰጠው ፣ ሞት ተፈረደበት ።
6) ፕራይቶሪዮን በሚባል ግቢ ቀይ ልብስ አልብሰው የሾህ አክሊል ደፍተው ዘንግ አስይዘው ዘበቱበት ።
7) መስቀሉን አሸክመው ሊሰቅሉ ወሰዱት ።
በስድስት ሰዓት
8) በ6 ሰዓት ጎልጎታ/ቀራንዮ/ በተባለው የራስ ቅል ስፍራ እጅ እግሩን ቸንክረው በሁለት ወንበዴዎች መካከል ሰቀሉት ።
9) ልብሱን ለአራት ተካፈሉት በእጀ ጠባቡ ላይ እጣ ተጣጣሉ ።
10) በመስቀል ላይ ሳለ ሰደቡት ፣ ተፉበት ፥ ሆምጣኤም አጠጡት፥ጎኑንም በጦር ወጉት ።
በዘጠኝሰዓት
11) በመስቀል ላይ ከ6-9 ሰዓት ከቆየ በኋላ በ9 ሰዓት ነፍሱን ስለ ሁላችን አሳልፎ ሰጠ ፤ ታመ ፥ ሞተ ።
በአሥራአንድ ሰዓት
12) ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር በአሥራ አንድ ሰዓት ቀበሩት ። ይህ የስቅለቱ ታሪክ በአራቱ ወንጌላውን ተጽፋል ። /ማቴ 26 ፥ 37 ፤ 27 ፥ 61 ። ማር14 ፥ 53 ፤ 15 ፥ 45 ። ሉቃ 22 ፥ 54 ፤ 23 ፥ 56 ። ዮሐ 18 ፥ 12 ፤ 19 ፦24/ ።
በቤተ ክርስቲያን የሚታወቁት አሥራሦስቱ ሐማማተ መስቀል
1) ተኮርኦተ ርእስ /ራስን መመታት/
2) አክሊለ ሶክ /የሾህ አክሊል መድፋት/
3) ተአስሮ ድኅሪት /የኋሊት መታሰር/
4) ሰትየ ሐሞት /ሐሞት መጠጣት/
5) ወሪቀ ምራቅ /ምራቅ መትፋት/
6) ተቀስፎ ዘባን /ጀርባን መገረፍ/
7) ተጸፍኦ መልታኅት /ፊትን መመታት/
8) ርግዘተ ገቦ /ጎንን በጦር መወጋት/
9) አምስቱ ቅንዋት /ሳዶር ፥ አላዶር ፥ ዳናት ፥ አዴራ ፥ ሮዳስ / ማቴ 26 ፥ 26 ። ትርጓሜ ወንጌል ይመልከቱ/
ጌታችን ከስድስት ሰዓትእስከዘጠኝ ሰዓት በመስቀል ሳለ የተደረጉ ሰባት ታምራት
v ፀሐይ ጨለመች
v ጨረቃ ደም መሰለች
v የቤተ መቅደስ መጋረጆ ከሁለት ተቀደደ
v ምድር ተናወጠች
v አለቶች ተሰነጠቁ
v መቃብራት ተከፈቱ
v ሙታን ተነሡ /ማቴ 27 ፥ 45-64/ ።
ሰባቱ አጽርሐ መስቀል
መድኃኒታችን በመስቀል ላይ ሁኖ የተናገራቸው ሰባቱ የፍቅርና የርኅራሄ ቃላት ሰባቱ አጽርሐ መስቀል በሚል ይታወቃሉ ።
v ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ /ማቴ 27 ፥ 46/ ።
v ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ/ሉቃ 23 ፥ 43/ ።
v አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ /ሉቃ 23 ፥ 46/ ።
v አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ።
/23 ፥ 34/ ።
v እነሆ እናትህ እነሆ ልጅሽ /ዮሐ19 ፥ 26-27/ ።
v ተጠማሁ /ዮሐ19 ፥ 29/ ።
v ተፈጸመ/ዮሐ 19 ፥ 30/ ናቸው ።
ከምድር /ከሰዎች/ወደመስቀሉ የተገሩ ቃላት
= «ከመስቀልህ ውረድ» /ማቴ27 ፥ 39-40/
= «በመንግሥትህ አስበኝ» /ሉቃ 23 ፥ 44/
= «ራስህንም እኛንም አድን» / ሉቃ 23 ፥ 39/
= «የዓለም መድኃኒት ፥ የእግዚአብሔር ልጅ ፥ የእስራኤል
ንጉሥ» እያሉ አፌዙበት ። /ማቴ 27 ፥ 42-43/ ።
= «ኤልያስን ይጣራል» /ማር15 ፥ 34/
= «አንተስ የአይሁድ ንጉሥ ከሆንህ ራስህን አድን» /ሉቃ 23፥ 36-37/ ።
= «ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ» /ማር15 ፥39/ ።
7ኛ/ ቅዳሜ ፥ ሶስት ስያሜዎች አሉት 1) ቅዳም ስዑር ይባላል ፣ይህ ስያሜ ሰንበተ አይሁድ መሻሩን ያመለከክታል የሚሉ ሊቃውንት አሉ ፤ ምክንያቱም በክስቶስ /ሰንበተ ክርስቲያን/ ተተክቷልና ፤ እንዲሁም ጌታችን ሙስና መቃብር እያጠፋ በመቃብር ስላሳለፈው ነው «ስዑር» የተባለው የሚሉም አሉ ።
2) ሌላው ስያሜ ደግሞ «ዐቢይ ሰንበት» የሚል ነው ፣ ሰንበት ማለት ዕረፍት ማለት ሲሆን ጌታችን ሥራውን ፈጽሞ በመቃብር አርፎበታልና ትልቁ ሰንበት ነው ለማለት ነው ።
3) የፋሲካ ሰንበት ቅዱስ ሰንበት እያሉ የሚጠሩትም አሉ ፤ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን በመቃብር ያኖሩት በመዘጋጀት በመከራው ቀን ዓርብ ማታ ነበር ፣ ሰንበትም ሊጀምር ሲል ነበር ፤ ቅዳሜ ከገባ በኋላ እንደ ትእዛዙ ሰንበት ስለ ሆነ ዐረፉ ። /ሉቃ 23 ፥ 56/ ። /ምንጭ በመጋቤ ብሉይ ሠይፈ ሥላሴ ዮሐንስ የተዘጋጅ የደቀመዛሙርት ማስተማሪያ ከግል መስታዎሻዬ የተገኘ /
አክፍሎት
እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና አስተምህሮ ሐዋርያት በጌታችን ሞት እጅግ አዝነው ነበር ፤ ከዓርብ ጀምሮ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል አልበሉም ውኃም አልጠጡም ፤ ይህን ለማስታዎስ የቻለ ከዓርብ ጀምሮ ያከፍላል ፤ ያልቻለ ደግሞ ቅዳሜን ብቻ አክፍሎ ውሎ ያድራል ፤ ይህ ጾም አክፍሎት ይባላል ፣ ሙሽራው ሲወሰድ ሚዜዎቹ ይጾማሉ ብሎ ነበር መድኃኒታችን ።/ማቴ 9 ፥15/ ።
ይህም ጾም ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን የምናስብበት የኃዘናችን መግለጫም ነው ። በአይሁድ ቅንዓት ስለ ሁላችን የተቀበለውን ሕማማተ መስቀልና ሞቱን እያሰብን ብርሃነ ትንሣኤውን የምንናፍቅበት ጾም ነው ።

