የበዓላተ ትንሣኤ (ሰንበታት) ሥርዓተ አምልኮ (በዓለ ኀምሳ)
በዓለ ኀምሳ የሚባለው ከትንሣኤ እስከ በዓለ ጰንጠቆስጤ (በዓለ ጰራቅሊጦስ) ድረስ ያሉት ኀምሳ ዕለታት ናቸው ። በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ትንሣኤ ታከብራለች ። በክርስቶም ያገኘችውን ዕረፍተ ነፍስ በምልዓት ትሰብካለች ፡፡ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ታስባለች ፣ በነዚህ ዕለታት ዓርብ ፣ ረቡዕ አይጾሙም ፤ ቀኖና ለተነሳሕያን አይሰጥም ፤ ከበደልና ከመበደል ነጻ ሁነን፣ ከበደለኛ አእምሮ ወቀሳ ድነን የምኖርባት መንግሥቱ በትንሣኤ ትሰጠናለች፣ በትንሣኤውም በደላችንን ሁሉ ሽሯል ለማለት ነው። እንዲሁም በስግደት ፥ በድካም ፥ በትምህርት የሚኖሩ ሁሉ በዕረፍት በዐለ ሐምሣውን ያሳልፋታል ። በዚህ ወቅት ቅዳሴ ፥ መዝሙር ፥ ድካም የማያስከትል ሥርዓተ አምልኮት ይፈጸማል ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በክርስቶስ ዕረፍተ ነፍስ አግኝተናል ። ጌታ የትንሣኤያችን በኩር ነው ።
እኛም ከተነሣን በኋላ እግዚአብሔር ረኃብ ፥ ጥማት ፥ ድካም ፥ ሕማም ፥ ፈተና ፥ ሞት ፥ ፈታኝ መቃብር ፥ ብልየት ፥ ልደት ፥ ልህቀት ፥ ኃይለ ዘርዕ ፥ ኃይለ ንባብ ፥ ኃይለ እንሰሳ የሌለበትን ፣ ሥርዓተ ምድር አልፎ በአዲስ ሥርዓተ ሕይወት የምትመራውን ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን ለማለት ሲሆን ፣ ቀኖና የማይሰጠው በሥጋም ሆነ በነፍስ ከመበደል ጌታ ነጻ ያወጣናል ፣ ባለመበደል በአፋችን ምስጋና መልቶ ሕይወታችን ከበደል ተለይቶ የምንኖርበት ዘመን ይመጣል ። በትንሣኤው ፥ በዕርገቱ ጽድቅና ጸጋ ሕይወት ተሰጥቶናል ። ከተዋርዶ ነፍስ ድነናል ለማለት ነው ። በአጠቃላይ ድኅነተ ነፍስ ፣ ድኅነተ ሥጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቶናል ፣ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት የዘለዓለም ሕይወት ተዘጋጅቶልናል ማለት ነው ።
የአንደኛው ሳምንት እሑድ፡-
እሑድ በዓለ ትንሣኤ ሲሆን ጌታችን ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን ፣ሞትን በሞቱ ድል መንሣቱን ፣ ሙስና መቃብርን (በመቃብር ፈርሶ በስብሶ መቅረትን) ማጥፋቱን ፣ በሞቱ በመስቀሉ ያዳናቸውን በትንሣኤው ማጽደቁን ፣ በዝግ ቤት ገብቶ በፍርሃት ለነበሩት ሐዋርያት ሰላምን እርቅን መስበኩን ቤተክርስቲያን ታስባለች ።
ሰኞ ፥ ማዕዶት ይባላል፤ማዕዶት ማለት መሻገር ማለት ሲሆን ፣ በዚህ ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት ፣ ከሐሳር ወደ ክብር ፣ ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውን ፣ ፋሲካችን ክርስቶ መሆኑን ታስባለች ። 1ቆሮ 5 ፥ 7 ።
ማክሰኞ ፥ -ቶማስ ይባላል
በዚህ ዕለት ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን ፥ ችንካር (በሚስማር) የተቸነከረ እጁን እግሩን ፥ ካላየሁ አላምንም ማለቱን ፣ ክርስቶም ቶማስን ‹‹ጣትህን ወደዚህ አምጣና በጎኔ አግባው ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው ፤ ቶማስም ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት ኢየሱስም ስለ አየኸኝ አምነሀል ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዐን ናቸው አለው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ ። ዮሐ 20 ፥ 27-29 ።
ቶማስ የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን የማመኑ ነገር የሚታሰብበት ቀን እንዲሆን ስለ ተወሰነ ቤተክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች ።
ረቡዕ ፥ አልዓዛር ይባልል፡-
በዚህ ዕለት ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞተ ከተቀበረ ከአራት ቀን በኋላ ማስነሣቱን ፥ ለአይሁድ ቅንዓት ለጌታ ሞት ምክንያት ከሆኑት ታላቅ ተአምራቶቹ አንዱ የአልዓዛር ትንሣኤ መሆኑን ፥ አልዓዛርን በብሉይ ሥጋ በቃሉ ጠርቶ ከመቃብር ያስነሣው ጌታ በሐዲስ ሥጋ መነሣቱን ፥ ሞት ይይዘው ዘንድ የማይችል አምላክ መሆኑን ፥ እርሱ ለፍጥረት ሁሉ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን ፥ የምናምንበትን ሁሉ ትንሣኤ ዘለክብር የማያምኑበትን ትንሣኤ ዘለሐሳር ማስነሣት የሚቻለው ጌታ መሆኑን፥ ቤተክርስቲን ታስባለች ። (ዮሐ 11 በሙሉ) ።
ሐሙስ ፥ አዳም ፥ ወይም አዳም ሐሙስ ይባላል
በዚህ ዕለት ለሁላችን አባት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ ፣ አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለ መውጣቱ ይታሰባል ። ዘፍ 3 ፥ 15 ።
ዓርብ ፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይባላል
በዚህ ዕለት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በክርስቶ ሞትና ትንሣኤ ስለ መመሥረቷ ፥ እራሱን ስለ እርሷ አሳልፎ ስለ መስጠቱ ፥ ቤተ ክርስቲያንም የእርሱ አካል ስለ መሆኗ ። ኤፌ 5 ፥ 21 ። የነቢያትና የሐዋርት መሠረት በሆነው በክርስቶስ ላይ ስለ መመሥረቷ ፥ መሰብሰቢያዋም ክርስቶስ ስለ መሆኑ ። (ኤፌ 2 ፥ 19-22) ።
በክቡር ደሙ ፈሳሽነት ስለ መታጠቧ (ራእ 1 ፥ 6-8)
ከነገድ ከቋንቋ ስለ መመረጧ ፣ በደሙ ተዋጅታ አንድ መንጋ ስለ መሆኗ ፥ በሰማይ ሠራዊት በምድር የሰው ፍጥረት ያላገኘችውን ሕይወት በእርሱ ብቻ ስለ ማግኘቷ (ራእ 5 በሙሉ) ። በወርቅ በብር ሳይሆን በክቡር በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ስለ መዋጀቷ (1ጴጥ 1፤18-21)
ከልዩ ልዩ አነዋወር ተጠርታ በእርሱ ላይ ስለ መታነጿ ። (1ጴጥ 2 ፥ 4-6) ።
እያሰበች ቤተክርስቲያን የቤተክርስቲያንን ሕይወት ትሰብካለች ።
ቅዳሜ፡- ቅዱሳት አንስት
በዚህ ዕለት የክርስቶስን አካል ሽቱ ለመቀባት ፍርሃታቸውን በክርስቶስ ፍቅር ለውጠው በጋለ ፍቅር አካሉን መፈለጋቸውን ፥ ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ማደራቸውን ፥ ማርያምም ትንሣኤውን ቀድማ ስለማየቷ ፥ ሴቶችም የመላእክትን ራእይ ስለ ማየታቸው ፥ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምርበት ዕለት ነው ። ማቴ 28 ፥ 1-15 ። ማር 16 ፥ 1-8 ። ሉቃ 24 ፥ 1-12 ። ዮሐ 20 ፥ 1-18 ።
ከሥርአተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተወሰደ።

