Skip to main content Scroll Top

ቅድስና

PostFeaturedImage_KibreQidusan_Final (8)

ቅድስና

2 ሰንበት (እሑድ) የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ቅድስት›› ይባላል ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ሲሆን የመዝሙሩ ርእስ የጾመ ድጓው መክፈያ ሆኖ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ ከቅድስት ሰኞ ጀምሮ ጾመ ዐርብአ ጾመ ኢየሱስ ይባላል፡፡ ከዚህ ሰኞ ጀምሮ ለእግዚአብሔር መገዛት፣ መስገድ እንድንችል ለእግዚአብሔር መቀደስ ስለሚገባን፣ ቅድስናን ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች፡፡ ለዚህም በመዝሙሯ በቅዳሴዋ፣ ሁሉ ቅድስናን የሚያንጸባርቁ ቃላት ሞልተዋል፡፡ በዚህ ቀን ስለ ክብረ ሰንበት፣ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ይዘመራል በቅዳሴ ጊዜም የሚነበቡት ቅዱሳት መጻሕፍትም ስለቅድስና የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

ማውጫ፡

  1. የመዝሙር ስ፡ ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ

(እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ጥሩ)

  1. በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች
  2. በገባሬ ሠናዩ ዲ/ን 1ተሰሎ 4፤1-13
  3. በንፍቁ ዲ/ን 1ጴጥ 1፤13 እስከ ፍጻሜው
  4. በንፍቁ ቄስ የሐዋ ሥራ 10፤7-30

ምስባክ ፡- እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ

አሚነ ወሠናይት ቅድሜሁ

ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ

በአማርኛ፡- እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ

ምስጋና ውበት በፊቱ ነው

ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡

መዝ 95(96)፤5

ትርጉም፡ እግዚአብሔርስ ምን አደረገ ትለኝ እንደሆነ እግዚአብሔርስ አምላክ ነውና ሰባቱን ሰማያት ሠራ፡፡ ሃይማኖት ምግባር በፊቱ ነው ማለት ሃይማኖት ምግባር ያለው ሰው ይወዳል፡፡ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ መመስገንም ገንዘቡ ነው፡፡

ወንጌል፡– ማቴ 6፤16-25

ቅዳሴ፡ የኤጲፋንዮስ ቅዳሴ (ዐቢይ)

ለቱ የትምህርት

ቅድስና

ቅዱስ ተብሎ የሚስገን የቅድስና ምንጭ በቅድስናው የተቀደሰ፣ ፍጥረት የለገሰችው ቅድስና ከፍጥረት የተሰጠ ቅድስና የሌለው በቅድስና የሚኖር ቅድስና የባሕርዩ የሆነ ቅዱሳንን የሚቀድስ ቅዱሰ ቅዱሳን እግዚአሔር ነው፡፡ በእስራኤል የመዝሙር መጽሐፍ ‹‹አቤቱ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማነው በምስጋና የተፈራህ፣ ድንቅንም የምታደርግ፣ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማነው›› ተብሎ እንደተጻፈ፣ አምላከ አማልክት እግዚአ አጋዕዝት ጌታ በቅድስና የከበረ ነው ምስጋውም ‹‹ቅዱስ›› እንደሆነ ያየውና የሰማው ኢሳያስ ስሙን ‹‹ቅዱሱስ›› ብሎ ጠርቶታል (ኢሳ 6 ፣ 1-10 ። ኢሳ 40 ፣ 25) ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹አንተ ብቻ ቅዱ ነህ›› ብለው መላእክት በሰማይ በባሪያው በሙሴ መዝሙር እንደሚያመሰግኑት ጽፎልናል (ራእ 15፤4) እግዚአብሔር የሰማት ሐናም ‹‹እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና … ከአንተም በቀር ቅዱስ የለም›› ብላ ዘምራለች (1ሳሙ 2 ፣ 2-3) ፈጣሪ ራሱ ራሱን እንዲህ ሲል ገለጠው ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ›› (ዘሌ 19፣2 ። 1ጴጥ 1፣ 16)፡፡

በአፈ መላእክት የሚጠራውና የሚቀደሰው በልሳነ ሰብእም (በሰዎች አንደበት) ‹‹ይትቀደስ ስምከ -ስምህ ይቀደስ›› እየተባለ የሚጠራ ስሙ ቅዱ ነው፡፡ ስሙም ከስሞች ሁሉ በላይ ስለ ሆነ ጌታ እግዚአብሔር  ራሱን ሲገልጥ ‹‹እኔ ቅዱ ነኝ›› ብሎ ቅዱስ መሆኑን ተናገረ። ነቢዩም ‹‹ስሙ ቅዱ የሆነ ከፍ ያው ልዑል›› ብሎ ይጠራዋል (ኢሳ 57፤15) ባለቤቱም ‹‹ቅዱስ ስሜን አረከሱ . . . እኔም ስለ ቅዱስ ስሜ  ስል እራራለሁ›› አለ (ሕዝ 36፤20-21) ቅዱሱን የጸነሰችው የቅዱሱ እናትም ‹‹ወቅዱስ ስሙ ስሙ ቅዱ ነው›› አለች (ሉቃ 1፤50) ቅዱሱም ለዘለዓለም በስሙ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እየተባለ ይመሰገናል (ኢሳ 6፤3 ። ራእ 4 ፣ 8) ስሙ ቅዱስ የሆነ ፈጣሪም በቅድስናው የሱ የሆኑትን ይቀድሳል (ዘጸ 28፤41)፡፡ ስሙ የሚጠራበትን በጎ የሚነገርበትን ሥጋው ወደሙ የሚፈተትበትን ይቀድሳል (ዘጸ 3፤5)፡፡ የመለኮታዊ ሥራው ፍጹምነት ምልክት የሆነችውን ዕለተ ዕረፍት ዕለተ አምልኮ ሰንበትንም የቀደሰ እርሱ ነው። (ዘፍ 2፤3)፡፡ የምንሰጠውን መባ የሚቀድስ፣ ንዋያተ ቅድሳትን የሚቀድስ ሁሉን የሚቀድስ እርሱ ነው (ኢያሱ 6፤9)፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ የእግዚአብሔር የሆኑ ምእመንም ቅዱሳን ናቸው፡፡ ጌታችን ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው›› እንዳለ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ-ምእመናን በፈጣሪዋ እውነት በመሲሁ ደም ከኃጢአቷ ተቀድሳ ‹‹ቅዱሳን ሁኑ›› ያለው ንጉሥ ተከታይ ሁናለች፡፡

አንባቢ ሆይ፡- በክርስቶ ብትኖር ቅዱስ ልትሆን እንደምትችል ታውቃለህን? (1ቆሮ 1፤2) እንዲሁም ቊጥር 30 በፈጣሪህ ጽድቅ በኑሮህ ልትቀደስ እንደምትችል (ዮሐ 17፤17-19) ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደህ የቀዳማዊ አዳምን መርገም ፈጣሪህ ጥሎልህ ቅዱሳንን በቀደሰው ተቀድሰህ ለመኖር ሁለተኛ በሐዲስ ተፈጥሮ በክርስቶስ መፈጠርህን ታውቃለህ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ አንደኛ ዲያቆን ያነበበው መልእክት ‹‹የእግዚአብሔር ፈቃድ መቀደሳችሁ ነውና ከዝሙት እንድትርቁ …    ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ (አካል) በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ . . . ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና›› ይላል (1ኛ ተሰሎ 4፤3-8)፡፡

በረዳቱ ዲያቆን የተነበበው መልእክትም ‹‹የጠራችሁ  ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ  በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ›› ይላል ። በረዳቱ ቄስ (በንፍቁ) የተነበበውም ‹‹የተቀደሰውን አታርክስ›› ይላል (1ጴጥ 1፤13-17, የሐዋ 10፤12-30) ቅዱስ ያሬድም ስለ ቅድስና ዘምሯል።አንተስ በጥምቀት የእግዚአብሔር ማደሪያ (ቤተ መቅደስ) የሆነ አካልህን ታረክሳለህን ወይስ ተቀድሰሃል? በል ተቀደስ፡፡

 

ምንጭ

ሥርዐተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

በመምህር ልዑለቃል አካሉ

 

 

Leave a comment