Skip to main content Scroll Top

ብዙ እረኞች ያላነሡት ድንጋይ

ብዙ እረኞች ያላነሡት ድንጋይ

(ዘፍ 29፤1-12)                                                                                                               www.kidusyared.org

13 ሰንበት (የቅበላ  እሑድ) ግጻዌና ስብከት፡-  በሀገራችን  የቀመር ጥናት ላይ የተመሰረተው  የማኅሌታውያኑ ይትበሐል  እንዲህ ይላል።   «መዝሙር  ዘቅበላ፤ ቃበላ ሲያጥር ጥር 23 ቀን ይደርሳል፤ በዚህ ጊዜ «ሖረ ኢየሱስ» ከሚለው መዝሙር  ቀጥሎ ወብዙኃን ኖሎት መጽኡ» ይባላል።  ቅበላ ሲረዝም ግን እስከ የካቲት 27 ቀን  ስለሚደርስ ሌሎች መዝሙሮች የመባል እድል ያገኛሉ።» /መጽሐፈ ዚቅ ገጽ 29/

ማውጫ፡-

መዝሙር ርእስ፡- ወብዙኀን ኖሎት መጽኡ

 

 

 

 

(ብዙ እረኞች መጡ)

 

2. በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች

በገባሬ ሠናዩ ዲ/ን ሮሜ 1፤1-17

በንፍቅ ዲ/ን 1ኛ ጴጥ 9፤20 እስከ ፍጻሜው

በንፍቁ ቄስ የሐዋ ሥራ 11፤1-19

ምስባክ፡- አግረረ ለነ አሕዛበ ወሕዝበ ታህተ እገሪነ፣

ወኅረየነ ሎቱ ለርዕሰቱ፣

ሥኖ ለያዕቆብ ዘአፍቀረ። መዝ 46፤3-4

በአማርኛ፡-   አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን

በታች አስገዛልን፣

የያቆብን ውበት የወደደ  ለርስቱ እኛን መረጠ።

ትርጉም ፡-  ሐዋርያት ሰብአ አርድእት ፣ ምእመናነ- አሕዛብ ምእመናነ-እስራኤልን በእጃችን ጭብጥ በእግራችን እርግጥ አድርጎ አስገዛልን >> ይላሉ ። ርስት ሊሆነን ርስት ልንሆነው መግንሥተ ሰማያትን ሊያወርሰን የመረጠን የያዕቆብንም ምግባር ሃይማኖት የወደደ፣ የያዕቆብን ሥጋ ለመዋሐድ የወደደ እርሱ ነው፡፡

ጥቅስ ለሰባኪው፡ ‹‹ወሥኑሰ ለያዕቆብ ዘይቤ ይእቲ ሥጋ እንተ ነሥኣ መድኅን እማርያም፤ የያዕቆብ  ውበት  ያለው መድኅን ከማርያም የነሳትን  ሥጋ ነው›› (ሊቅ ያሬድ)

ወንጌል፡-     ዮሐ 4 ፣ 1-27 ።

ቅዳሴ፡       የጌታችን (ነአኲተከ)።

www.kidusyared.org

 

የዕለቱ የትምህርት ርእስ

የዕለቱ የትምህርት ርእስ

ብዙ እረኞች ያላነሡት ድንጋይ

የእግዚአብሔር ሰው ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ወደ ካራን ሲጓዝ መሽቶበት በመንገድ አደረ፤  የእግዚአብሔርን ክብር አይቶ እግዚአብሔርም እንደማይለየው ቃል ገብቶለት የጀመረውን ጉዞ ከአምላኩ ጋር እንዲጓዝ ተስፋ ከፈጣሪ ከተቀበለ በኋላ ወደ ምሥራቅ አገር ሰዎች ደረሰ፤  በሜዳም ሁኖ  ጉድጓድ አየ፤ ጉድጓዱም የውኃ ጉድጓድ ነው፡፡ የዚያች አገር ሰዎች በጎችም ውኃ የሚጠጡት ከዚያ ነበረ፡፡  በጉድጓዱ አፍ ላይ የተገጠመው ድንጋይ በጣም ትልቅ ስለ ነበረ ማንኛውም እረኛ እንደ ደረሰ ድንጋዩን አንሥቶ ውኃውን ለበጎቹ ማጠጣት አይችልም ነበር፡፡

የአገሩ እረኞች ተሰብስበው ለኀምሳ ለስልሳ ሁነው ከጉድጓዱ አፍ ድንጋይ ገፍተው በጎቻቸውን ያጠጡ ነበር።  ከዚያም መልሰው ይዘጉት ነበር፡፡ ያዕቆብ በአካባቢው ያሉትን እረኞችን ከየት የመጣችሁ ናችሁ ቢላቸው የካራን ነን አሉት።  አጎቱን  ላባን እንደሚያውቁት ቢጠይቃቸው አዎን  እናውቀዋለን አሉት፡፡ እንዲያውም ልጁ ራሔል በጎቿን ይዛ ወደ ውኃው እየመጣች ነው ብለው ነገሩት፡፡ ያዕቆብም የአጎቱን የላባን ልጅ ራሔልን ከበጎቿ ጋር ባየ ጊዜ አለቀሰ።  እርሷንም ሳማት ከዚያ በኋላም ብዙ እረኞች ተሰብስበው ድንጋዩን መክፈት ስለማይችሉ የሌሎችን እረኞች መምጣት ይጠባበቁ ነበር፡፡  ያዕቆብ ግን ብቻውን ያንን ከባድ ድንጋይ ከጉድጓዱ አፍ ገልብጦ የአጎቱን የላባን በጎች አጠጣ። ያዕቆብም ለራሔል የአባቷ ዘመድ አጎቷ መሆኑን ነገራት፤  እሷም ሄዳ ለአባቷ ነገረችውና ወደ ቤቷ ወሰደችው (ዘፍ 29፤1-12) ይህም ታሪክ ይገለጥ ዘንድ ላለው ለኢየሱስ ክርስቶስ (የእረኞች አለቃ) አስተርእዮ /መገለጥ/ ምሳሌ ነበር፡፡ ቅ/ያሬድ ይህንን ሲተረጉም በዛሬው መዝሙር ሰምተናል፡፡

የመዝሙሩ ዘር በግእዝ፡- ወብዙኀን ኖሎት መጽኡ ወስዕኑ ከሲቶታ ለዕብን እም አፈ አዘቅት፤ እስከ ይመጽእ ያዕቆብ ዘክቡት ውስተ ኀቌሁ፤ ዘሀሎ ይሰጎ እም ሰብእ ከሠተ ወአስተየ  መርዔቶ፤  ወከማሁ መጽኡ ብዙኃን ነቢያት ወሰዕኑ ከሢቶታ ለጥምቀት እስከ ይመጽእ ዐቢይ ኖላዊ እም ሰማይ፤  ከሠተ ወአጥመቀ ብዙኀነ አሕዛበ በውስቴታ። መንክር ተአምሪሁ ለመድኃኒነ፡፡

ትርጉም፡- የያሬድ መዝሙር በአማርኛ፡- ብዙ እረኞች መጡ ፥ ከጉድጓዱ አፍ ድንጋዩን መክፈት (መገልበጥ) አልሆነላቸውም ። ከሰው ወገን ሰው የሚሆነው ጌታ በአብራኩ ያለ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ፤ እሱ ከፍቶ መንጋውን አጠጣ ። እንደዚሁ ሁሉ ብዙ ነቢያት መጡ፣ ጥምቀትን መመሥረት አልሆነላቸውም ፤  ደገኛው እረኛ ከሰማይ እስኪመጣ ድረስ፤  (እርሱ መጥቶ) ሥርዓተ ጥምቀትን መሠረተ፣ ብዙ አሕዛብን አጠመቀ የአምላካችን ተአምሩ ድንቅ ነው፤ የሚል ነው፡፡

ቅ/ያሬድ በመዝሙሩ እንዳስተማረን ድኅነተ-ዓለም ሕይወተ ዓለም፣ ጽድቀ ዓለም፣ ክብረ ዓለም የተገለጠው፣  ለሰዎችም የተሰጠው፣ የመርገም ድንጋይ የተወገደው በነቢያት፣ በካህናትና በጻድቃን (መዝራእተ ጽድቅ ኲርናአ ጽድቅ) የጽድቅ ክንድ ሳይሆን ከሰማይ በመጣው እረኛ በመለኮታዊ እረኛ ኃይል  ነበር፡፡  አብርሃም ያልገፋው  የያዕቆብ አቅም ያልቻለው በሰው ድካም ያልተወገደው የአዳም የሔዋን መርገም  በእረኞች አለቃ በአበ አበው  በክርስቶስ  ተወገደ፤  ሃብተ ወልድና ስመ ክርስትና የተገኘው በክርስቶስ ነው፡፡ ወደ ዓለም የተላኩ ብዙ እረኞች ነበሩ፤  ነገር ግን ከሕይወት ውኃ ላይ የተጋረደውን የመርገም ድንጋይ ማስወገድ አልቻሉም ። በጎቹ ከሕይወት ውኃ ተከልክለው  ነበር። ድንጋዩም ብዙዎችን አስጨንቆ እረኞችም እየተጉላሉ አቅም ያለውን ሰው ጠበቁ።  ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመጣልንግን በጎቹ የዕረፍትን ውኃ አገኘን፡፡

በወንጌለ ዮሐንስ እንደ ተጻፈልን ወንጌልን ከማመኗ በፊት ባለማወቅ ሳምራዊቷ ሴት ሰማያዊውን እረኛ ‹‹አንተ ከያዕቆብ ትበልጣለህን? እርሱም በጎቹም ከዚህ ጠጡ›› አለችው፤  ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ሁለተኛ አይጠማም አላት፡፡

የሐንስ ወንጌላዊ  እንደ ጻፈልን ሰማያዊው እረኛ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀምጦ ሳለ ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም ‹‹ውኃ አጠጪኝ›› አላት እርሷ ግን ‹‹እንዴት ትለምነኛለህ›› አለችው፤  በአይሁድና በሳምራውያን ዘንድ  መተባበር አልነበረምና ማለት ሳምራውን በአይሁድ ዘንድ የሚናቁ ሰዎች  ነበሩ።   እውነተኛው እረኛም ‹‹የእግዚአብሔርን ስጦታ፣ ውኃ አጠጭኝ የሚልሽን ማን እደሆነ ብታውቂ፣ አንቺ ትለምኝው ነበር፡፡ የሕይወትንም ውኃ ይሰጥሽ ነበር›› አላት፡፡ ሴቲቱም ‹‹መቅጃ የሌለህ የሕይወት ውኃ ከየት ታገኛለህ ይህን ጉድጓድ ከሰጠን ከያዕቆብ አንተ ትበልጣለህን?  እርሱም ልጆቹም፣ ከብቶቹም ከዚህ ጠጠትተዋል » አለችው።  መለኮታዊው እረኛም  «ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁለተኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘለዓለም አይጠማም ፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ» አላት፡፡

አንባቢ ሆይ! አንተስ በያዕቆብና በክርስቶስ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ታውቀዋለህን?  ያዕቆብ ካዘጀው ጉድጓድ የበለጠ የሕይወት ውኃ መዝገብ እንዳለውስ ልብ ብለሃልን?  ከውስጥህ የሚፈልቅና  የማይደርቅ የሕይወት ውኃን የሚሰጠው እውነተኛ እረኛ በጎቹን በለመለመ መስክ በዕረፍት ውኃ የሚያሰማራ እረኛ  ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡   ከእርሱ የሚገኘው የሕይዎት ውሀ ሁለኛ አስጠማም፤ ሕይዎትን የሚያረሰርስ ነፍስና  ሥጋን የሚቀድስ ሕይዎትነት ያለው ውሀ ከእርሱ የሚገኝ መንፈሱ ነው/ዮሐ 7፥37-39/።  አግዚአብሔር የሕይዎት ውሀ ምንጭ መሆኑን ነቢያት አስተምረዋል፤ ከእርሱም ሰዎች መራቅ እንደሌለባቸው « አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና»  ሲሉ ወቅሰዋል/ኤር 17፥13/። ከእርሱ የሚገኘው ቃለወንጌልም  ከኢየሩሳሌም  ፈልቆ ወደ ዓለማችን  እንደ ሚዳረስ  የተነገረው ተስፋ ትንቢት «በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል። »/ዘካ 14፥8/ የሚል ነበር። በእርሱ አምነን  የምንስማራበትን የሕይዎት መስክ የሚያለመልም የእረፍት ውሀ ነው/መዝ22፥1-3/።  በእርሱ የሚያምኑትም የዘለዓለም በእርሱ ጸጋ ከመረስረሳቸው የተነሳ የሕይዎት ውሃ ከውስጣቸው ይፈልቃል« በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ፥ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል» እንዳለ መድኃኒታችን/ዮሐ 7፥38/።  ምዕመናነ ክርስቶስ የሚኖሩባትም  ዓለም በዚሁጸጋ ያጌጠች ናት፤«በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ » እንዲል/ራዕ 22፥1/። ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያኑም በዓለም በደል የተቃጠሉትንና ሕይዎትን የተጠሙትን ሁሉ ሁል ጊዜ ወደዚህ ሕይዎት ይጋብዛሉ።«መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ። የሚሰማም። ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ» እንዲል /ራዕ 22፥17/።

ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁንና ለሰው የማይቻለው ለእርሱ ብቻ የሚቻለው፣  ለሰው ያቃተው ለእርሱ ብቻ የሚሆንለት፣ መዳናችንን ብቻውን ያከናወነ፣ አዘቅቱን ብቻውን  የከፈተ፣ መጥመቂያውን ብቻውን የረገጠ እርሱ ነው። በደህንነታችን ላይ የተጋረደውን የመርገም  ድንጋይ ብቻውን አንከባለለው፤   በፊታችን ላይ የተዘጋውን የሕይዎት  በር ብቻውን ከፈተው፤ ብዙዎች ያልቻሉትን አንዱ አደረገ። አንዱ ስለሁሉ ሞተ። በአንዱ ሁሉም ዳኑ ። ሰዎችን ለመፍጠርም ሆነ ለማዳን ማንም ያልተጋራው እርሱ ጌታችን  ነው።  የሕይወት ውኃ ምንጭም እርሱ ነው።  ለበጎች እረኛ  ለክርስቶ ኢየሱስ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡ካህናቱና ሌዋውያኑ ያላነሱትን ቁስለኛ ሕይወታችንን ላነሣው ሳምራዊ (ክርስቶስ) ምስጋና ይግባው፡፡ (ሉቃ 10፤30-37)

ጥቅስ፡-« ወአልቦ ካልዕ ሕይወት ወአልቦ ካልዕ ስም በታሕተ ሰማይ ዘይትወሀብ ለእጓለእመሕያው በዘየሐዩ፤

ሰዎች ይድኑበት ዘንድ የተሰጠ ከሰማይ በታች ሌላ ስምና ሕይዎት  የለም።»  (የሐ ሥራ 4፤12)

www.kidusyared.oreg

ምንጭ

ሥርዓተ አምልኮ በመምህር ልዑለቃል  አካሉ

Leave a comment