Skip to main content Scroll Top

ትንሣኤ ክርስቶስ

በአራቱ ወንጌላውያን እንደ ተጻፈ ሕይወትን ሞት ሊገዛው ስለማይችል ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ› ብሎ የሰበከው ጌታ ተነሣ ዮሐ 11 ፥ 25 ።
ክርስቶስ በሥጋ ከመገለጡ በፊት ቀኑ ጨለማ ነበር ፤ ሲወለድ ሌሊቱ (ጨለማው) በራ ። በተመሳሳይ ክርስቶስ ሲሰቀል ቀኑ ጨልሞ ነበር ፤ ሲነሣ ደግሞ ሌሊቱ በራ ‹‹ሌሎችን አዳነ ራሱን ግን ማዳን አይችልም›› የተባለው ጌታ በኩረ ምእመናን ሁኖ ተነሣ ። ማቴ 27 ፥ 42 ። 1ቆሮ 15 ፥ 20-24 ።
በሕማማቱ ወራት በግርፋት የተለወጠው ሰውነቱ ፥ ሞት አጥልቶበት የነበረው ፊቱ ፥ በሄሮድስና በጲላጦስ ፊት ተንገላቶ የቆመ ሕይወቱ ተለውጦ ብርሃን ለብሶ ብርሃን ተጎናጽፎ ተነሣ ። በአንጻሩ በመስቀሉ ፊት የፈካው ቀናተኛው የሊቃነ ካህናቱ ፊት ደግሞ ሬሳ ፊት ሆነ ። ወታደሮች ‹‹እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት›› የሚል የሀሰት ሪፖርት እንዲቀርብ ካህናቱ መከሩ ። ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ፣ ወታደሮቹ በገዦቻቸው ፊት ሥራቸውን እንዳልሠሩ አድርገው እንዲያቀርቡ ጠየቁ ። የይሁዳን ልብ በገንዘብ እንደ ገዙ የወታደሮቹንም ልብና መንፈስ በገንዘብ ለመግዛት ሞከሩ እናም ተሳካላቸው ገዙ ፤ ግን እውነትን በብር ሸሽጎ ማስቀረት አልቻሉም ።
ለይሁዳ ልብ ለወታደሮች አፍ ያወጡት ብር ከሰረ ፣ ጌታም ሞትን ድል ነሥቶ ተነሣ ። ካህናቱ የኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት መነሣት ሲሰሙ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወደቀ ። ሕዝቡንም ፈሩ ፣ በመሆኑም እንደ አማራጭ የወሰዱት የክርስቶስን ትንሣኤ መካድ ነበር ፤ በዚህ መሠረት ወታደሮቹን በገንዘብ ሸነገሉ ፣ ጲላጦስንም ዝም አሰኙት ፣ የሐሰት ወሬአቸውን በሰፊው አሰራጩ ይሁን እንጂ ዝም ሊያሰኙዋቸው የማይችሉ ምስክሮች አጋጠሟቸው ። ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን›› ብለው እንደ ጮኹ አልቀሩም ደም በእነሱ ላይ እንደሚሆን ተገነዘቡ ። ማቴ 27 ፥ 25
‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት እኔ በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ›› ያለው ቃሉ በትንሣኤው ተረጋገጠ ። ዮሐ 2 ፥ 19 ።
አስቀድሞ በትምህርቱ ‹‹ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል ። እኔ በፈቃዴ እኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም ። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞ ላነሣት ሥልጣን አለኝ ›› እንዳለ ። ዮሐ 10 ፥17) ።
ክርስቶስ የሞትን ማሰሪያ የሚበጥስ ታላቅ መለኮታዊ ኃይል አለው ።
ትንሣኤውም ለብዙዎቻችን ትንሣኤ በኩር ነበር ።1ተሰ 4 ፥ 14 ። ኢየሱስ ክርስቶ ከሙታን ሲነሣ ብዙ ምርኮኞችን ይዞ ወጣ ፤ ክርስቶስ ሲሞት የደረሰው የመሬት መናወጥ የብዙ ሙታንን መቃብር ከፈተ ፣ ሙታንም በመስቀሉ ኃይል ተነሥተው ትንሣኤውን መሰከሩ ። በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ስለ እውነት በመመስከር የሞቱ ቅዱሳን ከሞት ላስነሣቸው ጌታ ምስክር ሊሆኑ ተነሡ ። የክርስቶስን ትንሣኤ ከመቃብር በታች የነበሩ ተነሥተው መሰከሩ ፣ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ለመመስከር የገንዘብ ጥቅም አፋቸውን የማይዛቸው ሰዎች ተፈጠሩ ፣ በአይሁድ ጉቦ ያልተያዙ ሰዎች ከመቃብር ወጥተው መሰከሩ ።
ዛሬ በስም ክርስቲያን ከሆኑ ሰዎች ይልቅ ከሞት ከመቃብር (ከዓለም ኑሮ) ተጠርተው ትንሣኤውን የሚሰብኩ ሰዎች ይበዛሉ ፣ ሕያዋን የተባሉት ግን መመስከር ተስኗቸዋል ። አልአዛርን ፥ ወልደ መበለትን ፥ ወለተ ኢያኢሮስን ያስነሣ ጌታ በልዩ ትንሣኤ ተነሣ ። ትንሣኤውም አሥነሽ የማያሻው ትንሣኤ ነው ፣ በሐዲስ ሥጋ (አካል) የተከናወነ ትንሣኤ ነው ። ሞትን የማያስከትል ፍጹም ትንሣኤ ነው ። ትንሣኤውም ተነሥተው እንደሞቱት ሰዎች ትንሣኤ አልነበረም ፣ ለዘላለም በሕይወት ለመኖር ሞት ደግሞ ላይገዛው ፈጽሞ ተነሣ እንጂ ። አዳምን ፥ ሔዋንን ፥ አቤልን ፥ ኖህን ፥ አብርሃምንም ፥ ይስሐቅን ፥ ያዕቆብን ፥ ዮሴፍን ፥ ሙሴን ይዞ ያስቀረ መቃብር ድል ተነሣ ። የሞት መዝጊያም ተሰበረ ፣ የመቃብር ድንጋይም ተንከባለለ፣ መላእክትም ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ ? ተነሥቷል እንጂ በዚህ የልም›› በማለት ትንሣኤውን ሰበኩ ። ቅዱሳት አንስት ፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም ባዶውን መቃብር ተመለከቱ።

ከሥርአተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተወሰደ።

Leave a comment