Skip to main content Scroll Top

አስተርእዮ =መገለጥ

አስተርእዮ =መገለጥ

ይህ ዘመን በቤተ ክርስቲያን ዘመነ አስርእዮ፣ የመገለጥ ዘመን ይባላል። አምላክ በሰው ሥጋ  የተገለጠበት፣ ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ዘመን በመሆኑ ነው። መድኃኒታችን ከሰማያት ወርዶ (ዮሐ 3፤13) ጊዜው ሲደርስ ከሴት ተወለደ (ገላ 4፤3, ሉቃ 2፤1-10) በሥጋ ተገለጠ መሰል እና ወደር በሌለው ብርሃን ውስጥ የሚኖር አምላክ ሲሆን ሟች ሥጋችንን ለብሶ፣ ተገለጠ፡፡ ዳዊት አስቀድሞ ‹‹በከመ ሰማእነ ከማሁ ርኢነ›› ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንደ ተናገሩ ከድንግል ተወልዶ ፥ በሥጋ ተገልጦ አየነው ብሎ በትንቢት እንደ ቀደመን፤ የተስፋ ሰዎች ደግሞ በሥጋ ተወልዶ አየነው (መዝ 47፤7) ቅዱ ጳውሎም በጢሞቴዎ መልእከቱ ስለ ጌታ መገለጥ ‹‹በሥጋ የተገለጠ በመንፈስ የጸደቀ ለመላእክት የታየ በአህዛብ የተሰበከ በዓለም የታመነ በክብር ያረገ›› ብሎ ሰበከ (1ኛ ጢሞ 3፤16)፣ ቅዱ ኤፍሬም ‹‹ዘኢይትአወቅ ተከሥተ ወዘኢይትረአይ ተርእየ- ያልታወቀ ተገለጠ የማይታየው ታዬ›› አለ፡፡

ቅዱስ ያሬድም ‹‹አስተርአየ ዘኢያስርኢ ወርኢነ ብዕለ ስብሐቲሁ – የማይታየው ታዬ የጌትነቱን ክብር ምስጋናም አየን›› አለ (ዛቲ) ቅ.ያሬድ እንደሁም ‹‹እሙነ ኮነ አስተርዕዮቱ መገለጡ እውን ሆነ›› አለ፡፡ በሥጋም በመጣበት ጊዜም በመሲሁ መምጣት የተማረከችው ሐና የምትባለው ነቢይት እናት በጸሎት በአምልኮት ከምትኖርበት ወጥታ የተገለጠውን መድኃኒት አይታ እግዚአብሔርን እያመሰገነችና የኢየሩሌምን ቤዛ ለሚጠብቁ የተገለጠው እርሱ እንደሆነ መመስከሯን ወንጌል በቅዳሴ ሰዓት ሰማን (ሉቃ 2፤36) ሕያው አምላክ በሥጋ ተገለጠ።

ለምን ተገለጠ ? ዲያብሎስ ያቆመውን እኛን ያስጨነቀበትን በዓለማችንም ገዝፎ ይታይ የነበረውን የነቢት እንባ ያልፈነቀለውን የብሉይ ኪዳን ካህንናት (ሌዋውያን) የሚነፉት የመለከት ድምፅ ያላናወጠውን ቋሚ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ተገለጠ ። (1ዮሐ 3፤8)፣ የዲያብሎ ሥራ ምን ነበረ ቢሉ ሞት፣ ኃጢአት፣ ሐሰት፣ (ዮሐ 8፣44 1ዮሐ 3 ፣ 8-9) ናቸው ፡፡ ሞትን በሞቱ ኃጢአትን በመሥዋዕትነቱ፣ ሐሰትን በትምህርቱ ያፈርስበት ዘንድ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ሞት የሆነውን ዲያብሎስን ከስሥልጣኑ ይሽረው ዘንድ (ዕብ 2 ፣ 14-16) የሞትና የሲኦልን መክፈቻ ከጠላታችን እጅ ይነጥቅ ዘንድ (ራዕ 1፤17-18) እኛን ከኃጢአታችን ያድነን ዘንድ (1ጢሞ 1፤15)፣ ሕይወታችንን አጥተን ወደ መቃብር ለምንወረደው ሕይወትን ሊያበዛልን (ዮሐ 10፤10)፣ ወደ ሕይወት የሚወሰደውን መሥመር የሱራፌል ሰይፍ ስለ ዘጋብን መንገድ ሊሆነን (ዮሐ 14፤6)፣ ሌሎች ጎደሎዎችንም ሊሞላልን በሥጋ ተገለጠ፡፡

ቅዱስ ያሬድ ‹‹ተወልደ ኢየሱስ በተድላ መለኮት ተወልደ ተወልደ ተወልደ ተጠምቀ… ከመንትሣሕ በልደቱ ወንትሐሠይ በአስተርእዮቱ›› ይላል፡፡ ምን ማለት ነው? = በመለኮታዊ ተድላ ክብር ኢየሱስ ተወለደ ፣ ተወለደ ተወለደ ተወለደ ተጠመቀ በልደቱ እንደሰት በመገለጡም ሐሤት እናደርግ ዘንድ ። ማለት ነው፡፡

በሥጋ ተገልጦ ጠላትን ለረገጠ፣ በምእመናን ነግሦ ለሚኖረው መድኃኒት ክብር ይሁን፡፡ አሜን!

ከሥርዐተ አምልኮ  መጽሐፍ /በመምህር ልዑለቃል አካሉ ዓለሙ/ የተወሰደ። ይቆየን!

Leave a comment