Skip to main content Scroll Top

ወንጌል፡ ወንጌል ምንድን ነው?

PostFeaturedImage_KibreQidusan_Final (5)

ፍቺው:- ቃሉ ከግሪክ ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙ የምሥራች ቃል ማለት ነው። የሰው ልጅ በበደሉ ምክንያት ከመጣበት ሞትና ኩነኔ፥ ፍዳና መርገም የምንድንበትንና የዳንንበትን ዜና የያዘውን የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያው አራት ክፍለ መጽሐፍ “ወንጌል” ይባላል። ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፥ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ሕይወት፥ተአምራት፥ ጌትነት፥ አምላክት፥ ቤዛነት፥ ልደት፥ ልህቀት፥ ሕማም፥ ሞት፥ ትንሣኤ፥ ዕርገት፥ ነቢረ የማን፥ (በአብ ቀኝ መቀመጥ)  ዳግም ምጽአት የተገለጸበት፥ ሕይወት ደኅንነት የተሰበከበት የምሥራች ቃል ነው። በሐዲስ ኪዳን መግቢያ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ወንጌላዊውና ሰማያዊው ቅዱስ ገብርኤል «ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ = እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ» ብሎ ቃለ ሕይወት ወንጌልን ለድንግል ማርያም እንደ ሰበከ ቅዱስ ሉቃስ መዝግቧል። ሉቃ 1፥27-30 ።

ይህ የምሥራች ነው ተብራርቶ በአራት ክፍል ቀርቦ ለአራቱ መዓዝነ ዓለም የሕይወትና የምሥራች መልእክት የሆነው።

ወንጌል

በብሉይ ኪዳን የተገለጸውን የእግዚአብሔር ጽድቅ የሚገልጽ የሕይወት መልእክት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ «በነቢያቱ አፍ በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ተስፋ ለሰጠው ለእግዚአብሔር ወንጌል» እንዳለ። ሮሜ 1፥1።

በገላትያ መልእክቱም «ወንጌል አስቀድሞ ተሰበከ» ብሎ የተስፋውን ፍጻሜ እንደ መሰከረ ወንጌል የብሉይ ኪዳን ተስፋ ፍጻሜ ነው። ገላ 3፥8።

ወንጌል አስቀድሞ ለነቢያት የተገለጠ፤ የአውሬውን ራስ መመታት (መቀጥቀጥ) ለአዳም ያበሠረ፤ በአቤል ሕይወት ቅንነት፥ በሔኖክ የሞትን ኃይል መሸነፍ፥ በኖኅ መርከብ ከጥፋት ውኃ የሰዎች መዳን፥ በአብርሃም በረከት እና የተባረከ ዘር ፣ በይስሐቅ መሥዋዕትነት፥ በያዕቆብ እስራኤል መባል፥ በዮሴፍ መሸጥና ለወገን ሲሳዩን ማዘጋጀት፣ በሙሴ አገልግሎት እና ነቢይነት፣ በኢያሱ መድኃኒትነት፣ በቀይ ባሕር መከፈል፣ በዮርዳኖስ መቆም፣ በኢያሪኮ ግንብ መፍረስ፥ በረድኤት ደመና፥ በሕይወት ውኃ የተገለጸ የተሰፋ ቃል ነው። በነቢያት «ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳልች» ተብሎ የተሰበከ። በሌሎችም የትንቢትና የመዝሙራት ክፍሎች በምልዓትና በስፋት የተሰበከ የሕይወት መልእክት ነው። ኢሳ 9፥7። ኢሳ 53 መዝ 21።

ሄሬኔዎስ በሃይማኖተ አበው «ኦሪት ነቢያት ወንጌል ክርስቶስን አስተማሩ» ብሎ እንደ ተናገረ ወንጌል ክርስቶስ የተገለጸበትና ያስተማረውም የሕይወት ቃል ነው። ሃይማኖት አበው ም7፥ ክ1 ቍ 2።

ወንጌል ተደላድለንና ተመሥርተን ልንኖርበት ከሰማይ በታች ላለነው ሁሉ የተሰበከ የሕይወት መልእክት ነው። «ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል። ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው። እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንኩ» እንዳለ ሐዋርያው ቅ ጳውሎስ። ቈላ1፥23።

ወንጌል ሰዎችን ሁሉ ለማዳን ኃይል ያለው የማያሳፍር የእግዚአብሔር መልእክት የዓለምን ሕዝብ ሁሉ የሚያድን ቃል ነው። «በወንጌል አላፍርምና አስቀድሜ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና» እንዳለ ሐዋርያው። ሮሜ 1፥16። ቲቶ 2፥11-13።

ወንጌል ለፍጥረቱ ሁሉ ማለት ለሰው ልጆች ሁሉ እንዲሰበክ ከጌታ የተሰጠ የእግዚአብሔር መልእክት ነው። ማር 16፥15

ወንጌል የእግዚአብሔር መንግሥት አዋጅ፥ የንስሐ ጥሪ፥ የኩነኔ ዘመን ማክተም፥ የነቢያት ትንቢት መደምደም፥ የመንግሥተ ሰማያት መቅረብ የተበሰረበት መልእክት ነው። በመሆኑም ማርቆስ «ኢየሱስም የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ» እያለ ወደ ገሊላ መጣ ብሎ ጽፎአል። ማር 1፥15።

ወንጌል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚሰበክ በተአምራት በመንክራት የተገለጠና በጽድቅ በብዙ ተአምራት በመንክራት መረዳት የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው። «ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደናንተ አልመጣምና» እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ። 1ተሰ 1፥5። ዕብ 2፥4። ማር 16፥20።

ወንጌል ጨለማ የማያሸንፈው ብርሃን፥ ሐሰት ያልተቋቋመው እውነት፥ ከንቱነት ያልተቀላቀለበት የጽድቅ ሐሳብ ነው። የዚህም ዓለም ገዥ የማያምኑትን ሰዎች ልቦና የክርስቶስን የክብሩን ወንጌል ብርሃን እንዳያዩ ቢያውርም በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ ጌታ የወንጌሉን ብርሃን ለሰዎች ሁሉ ያበራል። 2ቆሮ 4፥2-6።

አባታችን «ቃላችን (ወንጌል) አዎንና አይደለም አይሆንም» ብሎ እንደ ተናገረ የእውነት ቃል ነው። 2ቆሮ 1፥18።

በዚህ መልእክቱ «የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም እውነትን በመግለጥ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለሰው ሕሊና ራሳችንን እናመሰግናለን» ብሎ እንደ ተናገረ፣ ጥሩ መልእክት (ነቅዕ ንጹሕ) ነው። 2ቆሮ 2፥21።

ወንጌል በልቦና ውስጥ የሚያበራ የሕይወት ብርሃን ነው። «ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉት ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ። ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ሆነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና ስለ ኢየሱስም ራሳችንን ለእናንተ ባሪያዎች እናደርጋለን። በክርስቶስ ፊት የእግዚብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና» እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ። 2ቆሮ 4፥3-7።

ወንጌል ለዘላለም የማይለወጥ (የማይሻር) የእግዚአብሔር ቃል ነው። «ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያዋ ድረስ በእጃቸው ላከው» ተብሎ እንደ ተጻፈ ለሁሉም የሆነ የድኅነት መልእክት ነው። ማር 16፥ 8።

የወንጌል አደራ ለአንባቢው!

ውድ አንባቢ ሆይ የወንጌል መልእክት የአደራ መልእክት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ወደ ዓለም ሁሉ ሂደው ወንጌልን እንዲሰብኩ ሰጣቸው። የማይለወጠውን የወንጌል መልእክት በእጃቸው ወደ ዓለም ሁሉ ላከው። ማር 16፥18። ማር 16፥15። ማቴ 28፥18።

ይህ ለሐዋርያት የተሰጠው የአደራ መልእክት ወንጌል በሐዋርያት ድካም ተሰብኳል፣ ለኛም ደርሶናል። ቅዱስ ጳውሎስም መድኃኒታችን «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስብኩ» ብሎ ለሐዋርያት የተሰጠውን የአደራ መልእክት ወንጌልን እንደ ሐዋርያት ከጌታ እንደ ተቀበለ ሲገልጽ «እኔ ደግሞ የተቀበልኩትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ» ብሎ የተቀበለውን አደራ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አደራ ይሰጣል። 1ቆሮ 15፥3።

ለልጁ ለጢሞቴዎስም አደራ ሲል «ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ» ብሎ ሲመክረው እንሰማለን። 2 ጢሞ 2፥2-3።

ልጁ ጢሞቴዎስም አደራውን እንዲወጣ አባቱና መምህሩ «ቃሉን ሰበከ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ ዝለፍና ገሥጽ ምከረም» ብሎ ይመክረዋል። 2ጢሞ 2፥2-3።

ይህንንም ይዘው የቤተ ክርስቲያን አባቶች በቅዳሴ ጊዜ ወንጌልን ሊያነቡ ሲሉ እንዲህ ይላሉ። ገባሬ ሠናይ ቄስ «ነዋ ወንጌለ መንግሥቱ ለወልደ እግዚአብሔር» ማለት «የወልደ እግዚአብሔር የመንግሥቱን ወንጌል እንሆ!» ብሎ ለንፍቁ ቄስ ሲሰጠው ፣ ረዳቱ (ንፍቁ) ቄስ ደግሞ “መንግሥቶ ወጽድቆ ዘአወፈየኒ አወፈይኩክ” ማለት «የሰጠህኝን መንግሥቱንና ጽድቁን (ወንጌልን) ሰጠሁህ» ብሎ ለዲያቆኑ ይሰጠዋል። ከዚህ በኋላ የመንግሥቱ ወንጌል ይነበባል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ወንጌል ከመድኃኒታችን ለሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ለቀደምት አበው፣ ከቀደምት አበው ለእኛ የተሰጠ፥ እኛም ለሌሎች አደራ ብለን ልንሰጥ የሚገባን የሕይወት መልእክት መሆኑን ነው።

አንባቢ ሆይ!

ወንጌል እንዲህ ከሆነ እርሰዎስ ስለ ክርስቶስ ሕይወትነት፥ መድኃኒትነት፥ ጌትነት፥አምላክነት፥ በክርስቶስ ስለ ተገለጠው ሕይወት የሰሙትን ለሌሎች ነግረዋልን? ምናልባት መክሊተዎን ቆፍረው ቀብረውታል ይሆን?

ይበሉ ሲሞላለዎትም ሲጎድልበዎትም፥ ሲያዝኑም ሲደሰቱም፥ሲበረቱም ሲደክሙም፥ በጧትም በማታም፥ በመዓልትም በሌሊትም፥ በጊዜውም አለጊዜውም፥ የክርስቶስን ወንጌል ይስበኩ። ዘመናችን የሕይወትን ቃል ከመናገር ዝም የምንልበት ጊዜ አይደለምና። በወንጌሉ አይፈሩ፥ ስሙ ሕይወት መድኃኒት እንደ ሆነ ይስበኩ። ጨርቅ አጠረቀመ፥ ግንድ ተሸከመ ብለው የመስቀሉን ነገር ይናገሩ። ታመመ፥ ሞተ፥ ተነሣ፥ ዐረገ ብለው ሕማሙን ሞቱን ትንሣኤውን ዕርገቱን ይስበኩ አይፈሩ። ወንጌል የማያሳፍር የሕይውትና የኃይል መልእክት ነውና።  ሮሜ 1፥16።

መድኃኒታችን ሁለተኛ በመጣ ጊዜ በስሙ የሚያፍሩቱን በአባቱ ፊት ያፍርባቸወል። ያላፈሩበትን ደግሞ በሰውና በመላእክት ፊት ይመሰክርላቸዋልና። «ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ» ተብሎ እንደ ተጻፈ። ማቴ 10፥ 32-33።

የወንጌል አገልጋዮቹን ባዘጋጀበት መንፈሱ ለአደራው ቃል ያዘጋጀን። አሜን።

ጸሎተ ወንጌል

ዲያቆኑ ምስባክ ከመስበኩ በፊት

አቤቱ አምላካችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርትህና ለንጹሐን ሐዋርያትህ እንዲህ ያልካቸው። እናንተ የምታዩትን ያዩ ዘንድ በዙ ነቢያትና ጻድቃን ወደዱ፥ አላዩም። እናንተ ዛሬ የምትሰሙትንም ይሰሙ ዘንድ ወደዱ፥ አልሰሙም። የናንተ ያዩ ዓይኖቻችሁና የሰሙ ጆሮዎቻችሁ ግን የተሰመገኑ ናቸው። እኛንም እንደነሱ የበቃን አድርገን፤ በቅዱሳን ጸሎት የከበረ የወንጌልን ቃል ሰምተን እንሠራ ዘንድ። ማቴ 13፥16።

ካህኑ ወንጌል ከማለቱ በፊት

አምላካችንና መድኃኒታችን ሰውንም የምትወድ እግዚአብሔር ሆይ ቅዱሳን የሚሆኑ ደቀ መዛሙርትህንና ንጹሐን ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሁሉ ዳርቻ የሰደድካቸው አንተ ነህ ! የመንግሥትህን ወንጌል ይሰበኩና ያስተምሩ ዘንድ በሕዝብህ ውስጥ ያለውን ደዌውንና በሽታውን ሁሉ ይፈውሱ ዘንድ፥ የተሰወረውን ምሥጢርህንም ያስተምሩ ዘንድ።

አሁንም ጌታችንና አምላካችን ሆይ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክልን፣ ያሳባችንንና የልባችንን ዐይኖች አብራልን፥ የከበረ የወንጌልህን ቃል በመጨከን እንሰማ ዘንድ የበቃን አድርገን። የምንሰማ ብቻ አይደለንም እንደ ሰማን ልንሠራ ነው እንጂ፣ ስለ አንዱ ፈንታ ሠላሳና ስድሳ መቶም ያማረ ፍሬ በላያችን ያፈራ ዘንድ፥ ለመንግሥተ ሰማያትም የበቃን እንሆን ዘንድ አሜን” (ሥርዓተ ቅዳሴ)።

በመጋቤ ሐዲስl መምህርል ልዑለቃል አካሉ ዓለሙ

ክብረ ቅዱሳን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያትል ዋሽንግተን።

Leave a comment