የማይመረመር አምላክ በሥጋ ተገለጠ
በኦርትዕት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ሰንበት ግጻዌ፣ ትምህርትና መልእክት፤
ሰንበት (እሑድ)፡- ከየካቲት 15-20
ማውጫ፡-
የመዝሙር ርእስ፡- ተበሀሉ ጻድቃን (ጻድቃን እርስ በርሳችሁ እንዲህ ተባባሉ)
በቅዳሴ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች
በገባሬ ሠናዩ ዲ/ን ዕብ 12፤12-22
በንፍቅ ዲ/ን 2ኛ ጴጥ 1፤19 እስከ ፍጻሜ
በንፍቁ ቄስ የሐዋ ሥራ 7፤29-35
ምስባክ፡- እግዚአብሔር ስቡሕ በምክረ ቅዱሳን፣
ዐቢይ ወግሩም ዲበ ኩሎሙ እለ ዐውዱ፣
እግዚኦ አምላክ ኃያላን መኑ ከማከ።/መዝ 88፥7/
አማርኛ፡- በቅዱሳን ምክር እግዚአብር ክቡር ነው
በዙሪያው ባሉት ሁሉ ታላቅና ግሩም ነው
አቤቱ የሠራዊት አምላክ እንዳንተ ያለ ማነው?
ትርጉም፡- እግዚአብሔር በመላእክት ቃል እንዲሁም በነቢያት በካህናት ቃል የተመሰገነ ነው፡፡ በመንግሥቱ ዙሪያ ባሉ በሱራፌል በኪሩቤል ላይ እንዲሁ በምድር ላይ ባሉ አህዛብ ዘንድ ግሩም ነው፡፡ አቤቱ የኃያላኑ ባለቤት ማዳን መታደግ የሚቻለው እንዳንተ ያለ ማነው ማለት ነው፡፡
ወንጌል፡- ዮሐ 10፤34 እስከ ፍጻሜ
ቅዳሴ፡- እምቅድመ ዓለም (የዲዮስቆሮስ ቅዳሴ)
የዕለቱ የትምህርት ርእስ
የማይመረመር አምላክ በሥጋ ተገለጠ
እግዚአብሔር ያለና የነበረ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ሰው እንዲህ ነው ብሎ ባሕርዩን ሊመረምር አይችልም፡፡ እግዚአብሔር በማንም የማይመረመር መንፈስ (ዮሐ 4፤24) ይህ ነው የማይባል ብርሃን (1ዮሐ 1፤5) የማይለወጥና የማይተረጎም ፍቅር (1ኛ ዮሐ 4፤8) ነው፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሑር ራሱን ከገለጠ ልናውቀው እንችላለን (ዮሐ 17፤3)፡፡ እናውቀዋለንም ፣ ስለ ተባለ ባሕርዩን መርምረን በስፋት ማለት ሳይሆን እሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ እናውቀዋለን ነው፡፡ ነቢዩ ሙሴ እግዚአብሔር ማየት ፈቀደ፡፡ በክብርህ በባሕርይህ ሁነህ ልይህ ብሎ ጥያቄ አቀረበ <<…እግዚአብሔርም … ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም›› ብሎ መለሰለት (ዘጸ 33 ፣ 17-23) የእግዚአብሔር ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ መንገዱም ከመንገዳችን ልዩ በመሆኑ አይመረመርም (ኢሳ 55፤8)፡፡ ኢዮብ ይህንን የማይመረመርና የማይታይ ባሕርይ ‹‹የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል ምን ልታደርግ ትችላለህ ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል ምን ልታውቅ ትችላለህ ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል›› ይላል (ኢዮብ 11፤7-10)
ቅዱስ ጳውሎም የማይታይና የማይመረመር መሆኑን አስተማረን 1ኛ ጢሞ 6 ፣ 16 ። ዮሐንስ እግዚአብሔርን ያየው ሊያየውም የሚችል አለመኖሩን እና በልጁ በክርስቶስ ብቻ እንደ ተገለጠልን እና ልጁም እንደ ሰበከልን (ዮሐ1፤18) በቅዳሴ ጊዜ በዲያቆኑም የተነበበው መልእክት በደብረ ሲና የተገለጠውን የማይመረመር የእግዚአብሔር ክብር ተተርኮበታል፡፡ መድኃኒታችንም በወንጌል የእግዚአብሔር ቃል ከተሰበከላቸው የቃሉ አገልጋዮች ከሆኑ ነቢያት ካህናት ይልቅ የተለዬ የባሕርይ አምላክ መሆኑን መግለጹ ተጽፏል፡፡ በመሆኑም ዛሬ ቅዱስ ያሬድ የዘመረው መዝሙር የማይመረመረው አምላክ ግዙፍ ሥጋን መልበሱን የማይታየውም የሚታየውን ሥጋ ለብሶ መገለጡን የተገለጠው አምላክ አካላዊ ቃል የማይመረመር መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ የመዝሙሩ ኃይል ቃል እንደሚከተለው ነው፡፡
ተባሃሉ ጻድቃን በበይናቲሆሙ እንዘ ይብሉ ቦኑ ዘርኢክምዎ ለልዑል ።
ኢሳያይሳኒ ይቤ ርኢክዎ ለልዑል ርእየ ወስዕነ ጠይቆቶ
ሙሴኒ ይቤ ዘርእዮ በዐምደ ደመና ርኢክዎ ለልዑል ርእየ ወስዕነ ጠይቆቶ
ማርያምኒ ትቤ እንተ ጾርቶ በከርሣ ርኢክዎ ለልዑል ርእየት ወክህለት ጸዊሮቶ
ዮሐንስኒ ይቤ ዘአጥመቆ በዮርዳኖስ ርኢክዎለልዑል ርእየ ወስዕነ ጠይቆቶ
ትርጉም፡- ጻድቃን እርስ በራሳቸው እንዲህ ተባባሉ ልዑሉን አያችሁትን?
በደመና ዐምድ ያየው ሙሴም እንዲህ አለ፤ ልዑልን አየሁት ፥ አየው ነገር ግን መመርመር አልሆነለትም
ኢሳይያስም እንዲህ አለ ልዑልን አየሁት፣ አየው ነገር ግን መመርመር አልሆነለትም
በማኅፀኗ የተሸከመችው ማርያምም እንዲህ አለች ልዑልን አየሁት፣ አየችው ወሰነችው
በዮርዳኖስ ያጠመቀው ዮሐንስም እንዲህ አለ፤ ልዑልን አየሁት ነገር ግን ባሕርዩን መመርመር አልሆነለትም . . . ያልታየው ታይቷልና ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ አለ፡፡
አንባቢ ሆይ፡-በባሕርዩ የማይታይ በሥጋ ማርያም ተገለጠ
በባሕርዩ የማይመረመር በሥጋ ማርያም ታዬ
በባሕርዩ የማይዳሰስ በሥጋ ማርያም ተዳሰሰ
በባሕርዩ የማይወሰን በሥጋ ማርያም ተወሰነ
የባሕይ ክብሩን ገለጠልን፡፡
የአባቱን ክብር የአባቱን ኃይል የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መለኮታዊ ክሂሎቱን በሥጋ ተገልጦ ገለጠልን፡፡
ክብር ለአምላክ ይሁን!
ምንጭ ሥርዐተ አምልኮ በመምህር ልዑለቃል አካሉ።

