Skip to main content Scroll Top

ደብረ ታቦር

ደብረ ታቦር ማለት የታቦር ተራራ ማለት ነው ። የሚገኘው ከገሊላ ባሕር በምሥራቃዊ ደቡብ በኩል 1ዐ ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ ነው ። የታቦር ተራራ በሐዲስ ኪዳን በግልጽ ባይጠቀስም በብሉይ ኪዳን ግን ተጠቅሶ ይገኛል (መሳ. 4 ፥14) ።የተወደዳችሁ ክርስቲያን ! ጌታችን ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ ከስድስት ቀን በፊት በፊልጶስ ቂሣርያ ደቀ መዛሙርቱን በጠየቃቸው ጊዜ አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ፣ ሌሎችም ኤልያስ ፣ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ ብለውት ነበር ። እናንተስ ማን ትሉኛላች ? ሲላቸው ቅ/ጴጥሮስ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ መልሶለት ነበር ። እግዚአብሔር አብ ለቅ/ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ከገለጸለት ከስድስት ቀን በኋላ ሐዋርያት ሰዎች ኤልያስ ፥ ኤርምያስ፥ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል ካሉት ከስድስት ቀን በኋላ፣ እሞታለሁ እሰቀላለሁ ሲል ጴጥሮስ ልትሞት አይገባህም ሲለው በጴጥሮስ አንጻር ሰይጣንን ከኋላዬ ወግድ ካለው ከስድስት ቀን በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ሦስቱን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ወጣ ።
ወደ ተራራው ከወጣ በኋላ በፊታቸው ተለወጠ ፣ ሐዋርያቱ የክርስቶስን የክብሩን ብርሃን ሲያዩ ፊቱ ሲለወጥባቸው በሐዋርያት ልብ ያደረው ሥጋዊ መንፍስ ራቀ ፣ በውስጣቸው ያለው ጨለማ ተወገደ። የእግዚአብሔርን ክብር እንዲያስተውሉ አእምሯቸው ብሩህ ሆነ ።
በቤተ ልሔም የተወለደው ፣ በበረት የተኛው ፣ በአሮጌ ጨርቅ የተጠቀለለው ፣ ከብቶች ያሟሟቁት ፣ መዋቲ ደካማ ሥጋን የለበሰው ፣ ድሀ መስሎ በአርአያ ገብር የታየው ጌታ ክብሩ ተገለጠ፣ ፊቱ ተለወጠ ። እንደ ፀሐይ አበራ ለሐዋርያት በውስጣቸው ያለውን የጨለማ ፍርሃትን ያለማወቅን ነገረ ኑፋቄን ፣ ጥርጥርን ፥ ክፉ መንፈስን ፥ አለማመንን ሥጋዊነትን እነዚህን ነገሮች ሁሉ ከልቡናቸው አስወገደላቸው ። በብርሃነ መለኮቱ እንዲራመዱ አደረጋቸው ፣ ክብሩን ገለጠላቸው ። እኒያ በብዔል ዜቡል ነው አጋንንትን የሚያወጣው ያሉት ምነው አሁን ክብሩን ባዩ ! ጌታችን ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን ያመጣቸው ሙሴ ክብርህን አሳየኝ ብሎት ነበረ ። ዘጸ.33 ፥ 17-23 ።
ጌታችን ግን በሕይወተ ሥጋ እያለ እኔን ሊያይ የሚቻለው ማንም የለም ብሎት ነበር ። ሙሴ ሲሞት ጸሎቱ እንዳልተመለሰለት አድርገን ልናይ እንችላለን ። የፍጥረትን ጸሎት የማይዘነጋ እግዚአብሔር ግን የሙሴን ጸሎት ሳይረሳ ልመናውን ፈጸመለት ።
የተወደዳችሁ ክርስቲያን ! ጌታችን በደብረ ታቦር ተራራ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ሰዎችን (ነቢያትንና ሐዋርያትን) አንድ አደረጋቸው ። እርሱ አምላካችን መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ፣ ሠራዔ ብሉይ ወሐዲስ ነውና ። ሌላው ሙሴና ኤልያስ የተጠሩበት ሙሴ ነህ ይላሉ ፥ ኤልያስ ነህ ይላሉ ሲሉ እርሱ አምላከ ሙሴ ፣ አምላከ ኤልያስ መሆኑን ሊያሳይ ነው ።
ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን በዚህ ለእኛ መኖር እንዴት መልካም ነው ዳስ እንሥራ ብሎት ነበር ። ወዲያው ብሩህ ደመና ጋረዳቸው ። ደመና የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ ነው ። እነሆ በደመናው ውስጥ የምወደው የምወልደው ለተዋሕዶ ለመሥዋዕትነት የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ቃል ተሰማ ።
በቀዳማዊው አዳም በደልና ነውር የተዘጋው የሰማይ ደጅ በዳግማዊው አዳም በኢየሱስ ክርስቶስ ተከፈተ ። ሞት ለተፈረደበት ቀዳማዊው አዳም ብርሃን የለበሰ ፥ ጽድቅን የተጐናጸፈ ፥ እንደ ፀሐይ የሚያበራ ፥ ንጹሐ ባሕርይ ፥ ከአእላፍ የተመረጠ እርሱን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንሰማ የባሕርይ አባቱ ተናገረ ።
ክርስቲያን ሆይ ! በደብረ ታቦር ክብሩን አየን ። ዛሬም ያ ክብሩ ሊገለጥብን ያስፈልጋል ። እግዚአብሔር ክብሩን የገለጠበት ያ ተራራ ዛሬ የእኛ አካል ሊሆን ያስፈልጋል ። የእግዚአብሔር ክብርና ጥበቡ የሚገለጥበት ፣ ማዳኑ የሚታይበት የተባረከና የተቀደሰ ሕይወት ሊኖረን ይገባል ።
ብርሃነ መለኮቱን ካዩ በኋላ የነቅዱስ ጴጥሮስ የቃላቸው ትምህርት የእጃቸው ተአምራት ብቻ ሳይሆን የልብሳቸው ቁራጭ ፣ የአካላቸው ጥላ ጋኔን ያወጣ ድውይ ይፈውስ ነበር ።
ሐዋርያት ጌትነቱ የታየባቸው ደብረ ታቦር ሁነዋል ። ቃሉ በሕይወታቸው ተተርጉሞ ነበርና ፣ ዛሬ የክርስቶስን ክብር የሚገልጸው ግዑዙ ደብረ ታቦር ሳይሆን ቅዱስ ሥጋውን የበሉ ክቡር ደሙን የጠጡ ሁሉ የእርሱ ደብረታቦሮች ጌትነቱ የሚታይባቸው ፣ ግርማው የሚነበብባቸው ፣ ጸጋው የተትረፈረፈላቸው አባቶች ካህናት ወንድሞች ዲያቆናት መላው ምእመናን ናቸው ።
ክርስቲያን ሆይ ! ዛሬስ እዚሁ ባለን ምእመናን ሕይወት የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ይሆን ? ማነው የክርስቶስ ክብር በሕይወቱ የተገለጠበት ? የዓለም ውበትና ጌጥ ሳይሆን የክርስቶስ ጌትነት በውስጣችን ሊገለጥ ይገባል ።
ብርሃነ መለኮቱን የገለጸልን አምላክ ስሙ የተመሰገነ ይሁን ። አሜን።

Leave a comment