Skip to main content Scroll Top

አዲስ ሥርዓት ለአዲስ ኪዳን

ነሐሴ 16
በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን በጊዜ ቅዳሴ ለትምህርት የሚነበበው ወንጌል ከዚህ የሚከተለውን የሐዲስ ኪዳን አዋጅ የያዘ ነው ። «ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና ። እንካችሁ ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው ። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ ። በዚያ ጊዜ ኢየሱስ ። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው» የክብር ጌታ በሐሙስ ማታ የአይሁድን ፋሲካ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲያከብር በበግ ሥጋ ሳይሆን በሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት የነጻነት በዐል ፋሲካን ምእመናን የሚያከብሩበትን ጊዜ አበሰረ ። በበግ ሥጋ ፋሲካን ሲያከብሩ ለለመዱት እውነተኛው ነጻነት የሚገኘው በእኔ ሞት ነው ፤ ይህን ኅብስት አሁን ቆርሼ እንደ ሰጠኋችሁ ነገ ሥጋየ በመስቀል ላይ ስለ ዓለም ደኅንነት ይቆረሳል ሲል «እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው» እንዲሁም ለፋሲካው በዓል ክብር የቀረበውን ወይን አንሥቶ ባርኮና ቀድሶ አባቶቻችን በቤታቸው መቃንና መድረክ ላይ በቀቡት በግ ደም ሳይሆን ከዲያብሎስ ግዛት ነጻ የሚወጣው የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ ሰው በሆንኩት «በእግዚአብሔር በግ» በእኔ ነው ሲል «ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው ። » ብሎ ጽዋውን ይጠጡ ዘንድ ሰጣቸው ። ይህም የሐዲስ ኪዳን ደም ኃጢአትን ይቅር ለማለት በደልን ሁሉ ለመደምሰስ አዲሱን ውል አዲስ ኪዳንን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለማጽናት ነገ ዓርብ በመስቀል ላይ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው በማለት አብራቶ ገለጸለቸው ። ሥርዓተ ኦሪትን ሽሮ ሥርዓተ ወንጌልን ሾመላቸው ። ሐዲስ ኪዳንም እንደ ብሉይ ኪዳን በበግና በላም ደም ሳይሆን ከኃጢአት ሁሉ በሚያነጻው በራሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም መመሥረቱንና መጽናቱን አስተማራቸው ። የፋሲካው በግ እርሱ መሆኑን፣ በጽዋ የሚቀዳው ወይንም በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደሙ መሆኑን ገለጠላቸው ። የሐዲስ ኪዳኑ የቅዱስ ቊርባን ስርና መሠረት ይህ የወንጌል ቃል ነው ።
ከዚያም አይይዞ «ነገር ግን እላችኋለሁ ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም» ይህም የበጉን ሰርግ እራትና ምስሐ ደብረ ጽዮንን ያመለክታል ። አብሮ መብላትና መጠጣት የአንድነት ምልክት መሆኑ ይታወቃል ። የዚህ አገልግሎት ፍሬ በሚገለጥበት እናንተም የሕይወትን ማዕድ በምትሳተፉበት በመንግሥቴ እስክንገናኝ ድረስ ከአሁን በኋላ ይህንን ሥራት መፈጸምና ማስፈጸም የእናንተ አደራ ነው ። በሰማያዊው የሕይወት ማዕድ በኋላ እንገኛለን ማለት ነው ። በሉቃስ «ይህን ለመታሰቢያየ አድርጉትአለ» ይላል ። ሉቃ 22 ፥ 19 ።
ይህም ማለት «ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ ፥ ነአምን እርገተከ ወዳግመ ምጽአተከ» እያልን ፣ በጸሎተ ቅዳሴና በሥርዓተ ቊርባን ጊዜ ሥጋውን እየበላን ደሙን እየጠጣን ፥ የክርስቶስን ሞትና ትናሣኤ የምናስበበት መሆኑን ያሳያል ። ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ የሐዲስ ኪዳን ማዕድ ክቡርነት ፣ ምን እንደ ሆነ ፣ እንዴትና ለምን እንደምንቀበለው አብራርቶ እንደሚከተለው አስተምሮአል። «ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና። ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት ። ሰው ግን ራሱን ይፈትን ፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና ። ስለዚህ በእናንተ ዘንድ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች አሉ አያሌዎችም አንቀላፍተዋል ። ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር ፤ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን ። ስለዚህ ፥ ወንድሞቼ ሆይ ፥ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ ። ማንም የራበው ቢኖር ለፍርድ እንዳትሰበሰቡ በቤቱ ይብላ ። የቀረውንም ነገር በመጣሁ ጊዜ እደነግጋለሁ » 1ቆሮ11 ፥ 26-34 ።
ከላይ በተገለጠው ቃል መሠረት በእውነትና በመንፈስ ከቅዱሱ ማዕድ ከሥጋውና ከደሙ ልናሳተፍ ይገባል ፤ ለቅጣት ሳይሆን ለሕይወት እንቀበለው ፤ በድፍረት ሳይሆን በንስሐ ተዘጋጅተን እንቀበለው ፤ ሞቱን ትንሣኤውን እያሰብን እንቀበለው ። በፍቅርና በጉጉት እንቀበለው ፤ እየዘመርን እንቀበለው ፤ እያለቀስንም እንቀበለው ። ለዘለዓለም ሕይወት የሚያበቃውን የሕይወት ባለቤት ክርስቶስን ነውና ወደ ሕይወታችን የምንጋብዘው ራሳችንን አንጽተን እንቀበለው ። በመስቀልላይ ለተሠዋው መሢህ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይሁን ። አሜን ።

Leave a comment