ድንግል ማርያም በ በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት
ጋብቻ በሁሉ ዘንድ የከበረ መኝታውም ንጹሕ እንደ ሆነ ጌታ በጳውሎስ አድሮ እንዳስተማረ ። ሰዎችን ከመጀመሪያው ይበዙ ይባዙ ምድርንም ይሞሏት ዘንድ በጋብቻ በረከት ባረከ። (ዘፍ 1 ፣ 27-28። ዕብ 13 ፥ 3-7) ።
ክቡር የሆነውን ጋብቻም በእርሱ እና በአማኞቹ መካከል ያለውን ግንኙነት በጋብቻ መስሎ ተናገረ (ሆሴ 2 ፥ 4-18 ። ኤፌ 5 ፥ 25) መድኃኒታችንም እሱና ደቀ መዛሙርቱ ከታደሙበት እናቱ ድንግል ማርያምም ከተጠራችበት ከወዳጆቹ ሰርግ ቤት ተገኝቶ በጠላት ዲያብሎስ በዔድን ገነት የተበላሸውን ሰርግ በመባረክና የጎደለውን በመሙላት የሥራው መጀመሪያ የሆነውን ተአምራቱን አደረገ ። ሰርግ አስደሳች ነገር ነው ፣ የወይን ጠጅ ደግሞ የልቦና ደስታ ነው (መዝ 103 ፥ 15) ።
መድኃኒታችን ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ ። የዓለም ደስታ የዓለም ሕይወት ወደ ደስታ ቦታ የወይን ጠጅ ወደሚቀዳበት ቤት ተጠራ ። በቃና ዘገሊላ ለተደረገው ተአምር ምክንያት የሆነችው በሥጋ የወለደችው እናቱ ድንግል ማርያም ናት ፣ በዘመን ሁሉ ነፍሳችንን የሚያነሣሣ ይህ አማላጅነትዋ ነው ። የሰርጉ የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ ስለ እንግዶቹ ድንግል ማርያም አሰበች ፣ አሳዳሪው ማሰብ ያልቻለውን ነገር እርሷ አሰበች ፣ በምሕረቱ በመተማመን ወደ ልጇ ቀርባ የጠበቀ ልመና አሰማች ። (ዮሐ 2 ፥ 4)
ልመዋም ስለ ራሷ ሳይሆን በአማላጅነትዋ ልትጠቅማቸው ስላሰበችላቸው ሰዎች ነበር ። መድኃኒታችንም ‹‹አንቺ ሴት ከአንአቺ ጋር ምን አለኝ ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አላት ። ምን ማለቱ ይሆን ?
አንቺ ሴት ሲል መድኃኒታችን የስድብ ቃልን እንደ ሰነዘረ የሚገምቱ አልጠፉም ፣ ነገሩ ግን ምሥጢር እንጂ ስድብ አልነበረም ። አዳም ከኤደን ገነት በተባረረበት ወቅት የሰማው የተስፋ ቃል ‹‹ከሴቲቱ የሚወለደው የእባቡን ራስ ይቀጠቅጣል›› የሚል ነበር (ዘፍ 3 ፥ 15) ።
የተስፋው ጊዜም በተፈጸመ ጊዜ መሲሁ ከሴት ተወለደ ‹፣ወአመ በጽሐ ጊዜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እም ብእሲት›› ብሎ ሐዋርያው እንደ ተናገረ (ገላ 4 ፥ 4) ። በመስቀል ላይም የእባቡን ራስ መሲሑ ሲቀጠቅጥ የሴቲቱ ልጅ መሲሑም በእባቡ መርዝ እግሩ ሲነደፍ ትንቢቱ ሲፈጸም ‹‹አንቺ ሴት›› በማለት ነበር የጠራት በዚህ ሁሉ ‘ሴት’ እያለ ሲጠራት ፣ የተስፋውን ዘር ያስገኘች የሰዎች ሁሉ እናት መሆኗን ፥ በሔዋን የተበላሸው የሰው ሁሉ ሕይወት የሚለወጥበት የሁለተኛው አዳም ጠላትን የተበቀለው ወንድ ልጅ እናት መሆኗን ለመግለጽ ‹‹አንቺ ሴት›› አላት ። ሴት ማለት ወንድ እንደሚለው ስም የጾታም ስም መለያ እንጂ የስድብ ቃል ፣ የደካማነት ምልክት አይደለም ። ‹‹እናትና አባትህን አክብር›› ብሎ ሕግ የሠራ ጌታ (ዘጸ 20) ቅድስት እናቱን አቃለለ ማለት ድንግልንና የድንግልን ልመና ከማቃለል አልፎ ጌታን መሳደብ ነው ።
‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› በባሕርየ መለኮቱ ተአዝዞ ፣ አገብሮ የሌለበት ጌታ በሥጋ ታዛዥ ሁኖ ቢገለጥም የራሱ የሆነ የሥራ ጊዜ ነበረው ። በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ እንደ ተጻፈልን ‹‹ጊዜ›› እያለ ጌታ የሚናገረው የሞቱን የስቅለቱን ጊዜ ነበር ። ድንግል ማርያም ስለ ወይን ጠጅ ስትጠይቀው እርሱ ግን በዕለተ ዓርብ ስቴ ሕይወት ፣ ስቴ መድኃኒት ሁኖ ስለሚፈሰው ደሙ ይናገር ነበር ። ድንግል ስለ ሙሽራው ድግስና እንዲሁም የሙራሽው ጐደሎ የሚሞላበትን ሁኔታ ስትጠይቀው እርሱ ደግሞ በምክንያቱ አባቱ ስላዘጋጀው ሰማያዊ ሠርግና (የበጉ ሠርግ) የዓለምን ጎደሎ ስለሚሞላው ደሙ ተናገረ ። ጌታ በየአጋጣሚው ‹‹ጊዜዬ›› በማለት ስለ ዕለተ ሞቱ መናገሩን በሚከተሉት ጥቅሶች ልብ እንበል (ዮሐ 2 ፥ 4 ። ዮሐ 7 ፥ 6 ። ዮሐ 7 ፥ 30 ። ዮሐ 8 ፥ 20 ። ዮሐ 12 ፥ 23-27 ። ዮሐ 13 ፥ 1 ። ዮሐ 16 ፥ 32 ። ዮሐ 17 ፥ 1-2 ። ማቴ 26 ፥ 18) ።
በጌቴ ሴማኒ የአባቱን ፈቃድ ያስቀደመ ጌታ (ሉቃ 22 ፥ 42) በቃና ዘገሊላ የእናቱን ጥያቄ መለሰ ‹‹በቃና መታዘዝ አሸነፈ›› በቃና ዘገሊላ በድንገል ማርያም ፈቃድና አማላጅነት ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለወጠ ፣ በቀራንዮ ደግሞ በአባቱ ፈቃድ ደሙን የወይን ጠጅ አድርጎ አቀረበ ፣ አብ በደብረ ታቦር የሚለውን እንሰማ ዘንድ ‹‹ወሎቱ ስምዕዎ- እርሱን ስሙት›› እንዳለ ድንግልም የሚላችሁን አድርጉ በማለት የእናትነቷን ምክር ገለጠች ። መድኃኒታችን በቃና ‹‹አንቺ ሴት›› ያላትን ድንግል እናቱን በመስቀል ላይም አንቺ ሴት በማለት ጠራት ፣ ከመስቀል በኋላ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ በልጇ መስቀል ማኅፀንነት የብዙዎች እናት ሆነች ። አዲሱ ሰው አዳም የዳነው ሰው አባት ሲሆን ፥ አዲሲቱ ሔዋን ድንግል ማርያም ደግሞ የዳነው ሕዝብ እናት ሁናለች ።
የእግዚአብሔር ሥራ በሁለተኛው አዳም እስከተገለጠበት ጊዜ ድረስ ፣ በነቢያት ፥ በካህናተ-ኦሪት ፥ በመሳፍንት ፥ በአብርሃም ፥ በይስሐቅ ፥ በያዕቆብ ፥ በሙሴ ፥ በኢያሱ የተገለጠው አገልግሎ ድኅተ ነፍስን ያላመጣ ፍጹምነት የሌለው ፥ ከመርገመ ኃጢአት የማያነጻ መናኛ የወይን ጠጅ ነበር ። ማለፊያው የወይን ጠጅ ግን ከእውነተኛው የወይን ሐረግ ከክርስቶ በክርስቶስ ተዘጋጀ ። ሔዋን በድንግል ማርያም ተተካች ፣ አዳም በሁለተኛው አዳም ተተካ ፣ ስለ ሆነም ቤተ ክርስቲያን «ወኀደግነ አበ ቀዳማየ ዘውእቱ አዳም ዘቦቱ ማሰነ = ለጥፋት የተጋለጥንበትን ቀዳማዊ አዳምን ተውን» አለች ።
አገልጋዮች ሐዋርያትም በፈዘዙት የድንጋይ ጋኖች ውኃን (ቃሉን) ሞሉ፣ ጌታችንም በፈዘዙት የድንጋይ ጋኖች ውስጥ (በመርገመ አዳም በምክረ ሰይጣን) በተያዙት ሰዎች ሕይወት ውስጥ ጣዕም ያለው ሕይወት እንዲኖር በከሃሊነቱ አደረገ። ጌትነቱም በሁላችን ተገለጠ ።ክብሩ ይስፋ ። አሜን ።
ምንጭ ሥርዓተ አምልኮ
በመጋቤ ሐዲስ ልዑለቃል አካሉ

