ስምዖንን ያደሰው ራዕይ!
የዕለቱ ወንጌል ንባብ /ሉቃ 2 ፣ 24-38/
የእስራኤልን መጽናናት ይጠብቅ የነበረ ጻድቅና ቅዱስ ሰው ነበር፣ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰው ነበረ፡፡ መሲሕ ክርስቶስንም ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱ ገልጦለት ነበር፡፡ እመቤታችንና ዮሴፍም ሕፃኑን እንደ ኦሪቱ ሥርዐት በ40 ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት ሲሄዱ ስምዖን በቤተ መቅደስ ሕፃኑን ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ ‹፣ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ አይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው፡፡››
ዮሴፍና ድንግል እናቱ እስኪደነቁ ድረስ ስለ ክርስቶስ ብዙ ትንቢት ተናረገ፡፡ ስምዖንም ዮሴፍና ድንግል ማርያምን ከባረካቸው በኋላ ስለ ክርስቶ ኃይልና መስቀል በእመቤታችንም ስለሚፈጠረው የኃዘን ስሜት የተናገረውን ቅ/ሉቃስ እንዲህ ጽፎታል ‹‹ስምዖንም ባረካቸው እናቱ ማርያምንም እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ በእስራኤል ላሉ ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ድልው፣ ንቡር፣ ዝግጁ ነው፤ በአንቺም ደግሞ ልብሽን የሚከፍል የኃዘን ሰይፍ ያልፋል አላት፡፡››
አንባቢ ሆይ፡- አረጋዊው ስምዖን መሲሁን ካየ በኋላ እንግዲህ በምድር በሥጋ መኖር ይበቃኛል አንተ በሞት አሰናብተኝ አይኖቼም ማዳንህን አይተዋልና አለ፡፡ አዎ የራእይ ሁሉ ፍጻሜ ክርስቶስ ነው፡፡ አረጋዊው ስምዖን የእግዚአብሔርን ማዳን ክርስቶን ባየበት ዐይን ሌላ ሊያይበት አልፈቀደም ፣ የአዳምና የሔዋን ዐይን ኃፍረታቸውን ለማየት ተልጦ ነበር፡፡ ያም ዐይን ጉድ በማየት ይኖር ነበር፡፡ ዛሬ ግን የኛ ዐይን እንደ ሽግሌው በክርስቶስ ሰው መሆን ምክንያት ክብርን አየ፣ ብዙዎች ሊያዩት የወደዱትን፣ ነገር ግን ዐረፍተ-ዘመን ገቷቸው ያላዩትን አየን (ማቴ 13፤16-17)፤ አንባቢ ሆይ ስለ ኃጢአታችን የተሠዋው ኢየሱስን ይመልከቱ የናሱን እባብ ያዩት ሁሉ እንደ ዳኑ (ዘሌ 21፤8-9) እርስዎም ክርስቶስን በማየት ይድናሉና፡፡ ዘሬ ሰዎች ምን በማየት ነው ጊዜአቸውን የሚያጠፉት። ክርስቶስ ላይ ያላረፉ ዐይኖች በኢንተርኔት፣ በቴሌብዥን፣ በሌሎችም የመገኛ መንገዶች ገዳይ ነገር፣ ርካሽ ነገር በማየት በዓይናቸው በኩል ሞትን ወደ ሕይዎታቸው ይጋብዛሉ። ከንቱ ነገር በማየት ከንቱ ሁነው ይቀራሉ። አሳባቸውን ሁሉ ያሰውራሉ። ኃጢአትን ያዘወትራሉ። እንደ ስምዖን በሃይማኖት ጌታን ያዩ ግን ራዕያቸው ሁሉ ይቀደሳል። ውስጣቸውም ዕለት ዕለት ይታደሳል። እርካታና የነፍስ እረፍትም እንደ ስምዖን ይሰማቸዋል። ጌታ በጎውን ሁሉ ይግለጽልን። አሜን።
ጥቅስ፡- ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይ ወሐዋርያ፣ ብፁዓት አዕይንት ኪያከ ዘርእያ = ነቢይና ሐዋርያ ክርስቶ ሆይ አንተን ያዩ ዐይኖች ብፁዓን ናቸው›› (መልክዓ ኢየሱስ)
ጥቅስ፡- ‹‹የጌታን መንገድ (ልባችሁን) አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ፡፡ አዘቅቱ ይሙላ (ተስፋ ሕይወት የሌለው ልብ ተስፋ ሕይወት ይኑረው) ተራራውና ኮረብታው ዝቅ ይበል (ትዕቢተኛው ጣዖታዊው ልብ በወንጌል ይፍረስ በንስሐ ይታደስ) ሸካራው መንገድ ትክክል ይሁን ሥጋ የለበሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን (ትድግናውን ወልድን) ይይ›› (ሉቃ 3፤3-6)
ጸሎት፦ ኀበነ እግዚኦ አዕይንተ አእምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ፤ ወአእዛንነሂ ቃለ ዘባሕቲትከ ይስምዓ= የአእምሮ አይኖችን ስጠን፤ ዘወትር አንተን ብቻ ያይዩ ዘንድ፤ ጀሮዎቻችንም የአንተን ቃል ብቻ ይሰሙ ዘንድ።» /ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ/

