የእመቤታችን ዜና ዕረፍት እና ክብር
«ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር»
መግቢያ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአከ ሞት ያስደነገጣቸው፣ የጨለማውም ገዥ የዛተባቸው፥ መትና መቃብር ተስፋ ያስቆረጣቸውን የአባቶቿንና የእናቶቿን ፍርሐት የሻረው ጌታ እናት በመሆኗ እመቤታችን ትባላለች። ለሰው ልጆች ሁሉ ሞትንና መቃብርን ድል የነሣውንና በእባቡ ራስ ላይ የቆመውን መሲህ በመውለድ የልባቸው እንዲደርስ ምክንያት ሁናለች፤ የተስፋውንም ዘር ወልድን በዚህ ዓለም ላይ አስተናግዳለች።
ድንግል በልደቷ ጊዜና በልጅነቷ የወላጆቿን ሐዘን አስረስታለች፤ የዓለምን ድኅንነት ጊዜ መቃረቡን አብሥራለች። ድንግል በሄዋን የተዘጋውን አስከፍታለች፤ ድንግል ሰማይና ምድር የተገናኙበት መሰላል ለመሆን በቅታለች። ያም ማለት ሰውና እግዜር ፣ሰውና መላእክት፣ በእርስዋ ሕይወት በተከናወነው ምሥጢረ ሥጋዌ ወይም የአካለ ቃልና ትስብዕት ተሕዶ አንድ ሁነዋል ማለት ነው። ሕያውን በመውለድ የሕይዋን እናት የተባለችውንና የሄዋንን ስም በተግባር ተረጉማዋለች፤ እርስዋም የሕያዋን እናት ተባለች። ድንግል የመልአከ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤልን ዜና በመቀበል፣ በሄዋን ጀሮ የተሰማውን የመልአከ ጽልመትን የሐሰት ዜና ሽራለች፤ ድንግል ጠላት ለጥፋትና ለመሳለቂያ /ፍና ተሳልቆ/ «አምላክ እንድት ሆኑ» ብሎ የቀለደበትን እና ያታለለበትን ቃል፣ ለአምላክ ማደርያ ለመሆን በፍቀድዋ፣ የተዘበተበት የሰው ልጅ ባሕርይ በተዋሕዶ ስለከበረ የሰውን ባሕርይ አምላክ ለመባል እንዲበቃ ምክንያት ሁናለች። በመሆኑም ሊቁ ቅ/ያሬድ እንዳለው«ትምክህተ ዘመድነ በወሊዶተ ዚአከ፤ አናተን በመውለዷ የባህርያችን መመኪያ ናት» እያልን እናከብራታለን።
ድንግል በሃይማኖት «እንደ ቃልህ ይሁንልኝ» በማለቷ የማይቻለውን ቻላለች፤ የማይወሰነውን ወሰናለች፣ ማሕደረ ቃለ አብ ሁናለች። በመታዘዟም አብ ለተወክፎተ ቃለ እግዚአብሔር እንትበቃ አጽንቷታል፤ መንፈስቅዱስም ጸልሏታል/ ቅድሷታል/፤ ወልድም ሥጋዋንና ነፍሷን ነሥቷል።
ድንግል ከመላኩ የተነገረውን የምሥጋና ቃል በጉጉት ሳይሆን በሃይማኖት አጣርታ በመቀበሏ በቀላሉ የተታለለችውን እናቷንና የሌሎችን የሌሎች ሴቶች ብሕርይ ሁለተኛ በውዳሴ ከንቱ እንዳይጠለፍ ምሳሌ ሁናለች።
ድንግል የተጠላው ብሕርየ ሰብእ የተወደባት፣የተጣለው የሰው ልጅ የተነሣባት፣ የረከሰው የተቀደሰባት የተሰደደው ሰው ወደ ዕርስቱ የተመለሰባት፣ የሰው ልጅ ሁሉ የባሕርይ መመኪያ ናት። ድንግል ተስፋ አበው በእርሷ ስለተፈጸመ ክብሯ ትልቅ ነው። ይሁን እንጅ የወልደ እግዚአንሔር እናት በመሆኗ በዚህ ዓለም በሰላም የኖረች አይደለችም። ብዙ ዋጋ ከፍላ፣ አውሬውን ተዋግታ፣ በማሕጸኗ ፍሬም ድል ነሽነት ከብራ አስከብራናለች፤ በልጇ ላይ በደረሰው ሥቃይ ምክንያት በልቧ የሐዘን ሰይፍ ቢያልፍም መከራውንና ልቅሶውን ታግሳ የድልና የክብር እመቤት ሁና በንጉሡ ቀኝ ተምጣለች።
ዜና ዕረፍቷን ለማስታወስ ከክርስቶስ የመስቀል አደራ ቃል ብንነሳ መልካም ነው። በዮሐ 19፥25-26 ላይ እንደምናነበው የበጉ እናት ቅድስት ማርያም ለዮሐንስ አደራ ተሰጥታ ነበር። መድኃኒታችን በዚያች ከባድ ሰዓት በመስቀል ላይ ሁኖ ከተናገራቸው ቃላት መካከል እናቱን በተመለከተ« እነኋት እናትህ» የሚለውና ዮሐንስንም « እነሆ ልጅሽ» ያለው ይገኙበታል። መከራው በጸናበት ጊዜ እናቱን አልረሳታም ነበር። ችንካሩ የማያንቀሳቅስ ቢሆንም አንገቱን ወደእናቱ ዘምበል አድርጎ ደም በጋረዳቸው ዐይኖቹ እናቱን በፍቅር ዐየ። «አንች ሴት» በማለት የአውሬውን ራስ መመታት አበሰረ ፤ ከሴቲቱ የሚወለደው የእባቡን ራስ ይመታል ተብሎ ተነግሮ ነበርና። ከመስቀሉ ስር ለነበረው ዮሐንስ አደራ ብሎ እናቱን ሰጠው። ዮሐንስም ወደ ቤቱ ወሰዳት፤ ካዚያ በኋላ እመቤታችን 15 ዓመታት ብቻ እንደኖረች የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይገልጻል። ጠቅላላ ዕድሜዋ 64 ዓመት ነው። በዜና እረፍቷ ላይ ቤ/ክ ያቀየችልን ታሪክ እንዲህ ይላል። «በተወለደች በ64 ዓመቷ በዘመነ ሉቃስ ጥር 21 እሁድ ቀን አርፋለች።» ይህም ሊሆን የቻለው ከእናት ከባቷ ጋር 3 ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመታት፣ በቤተ ዮሴፍ ዘጠኝ ወር፣ ከጌታ ጋር 33 ዓመት በቤተ ዮሐንስ 15 ዓመት ድምር 64 ዓመት ያለው ይህነው። የዕረፍቷም ጊዜ ካሳ ከተፈጸመ ፣ ፀሐየ ፍድቅ ወንጌል ካበራች፣ ምድራችን ለፍሬ ወንጌል ከበቃች፣ የጨላማውና የጭጋጉ ዘመን ካለፈ፣ ጉሙ ደመናው ከተገፈፈ፣ ክረምተ ኦሪት ካለፈ፣ መሐሩ ጸጋ ወንጌል ከተትረፈረፈ በኋላ ነበር። ስለዚህ «የቅርቤ መልካሟ ርግቤ ውድዬ ነይ አሁን ክረምቱ አልፋልና፤ ዝናሙም ወደኋላ ተመልሷልና፤ በምድራችን አበባ ታይቷል የመከርም ጊዜ ደርሷል፤ በለስ ለምልሟል ወይኖች አብበዋል፤ አበቦች መዓዛቸውን ሰጥተዋል» ብሎ አባቷ ሰሎሞን የተናገረውን ያስተረጉማል/መኃ 2፥10-14/።
ከእረፍቷም በኋላ አይሁድ ሐዋርያት ሥጋዋን በክብር እንዳያሰርፉት በመቃወማቸው መላእክት በገነት በዕፀ ሕይዎት ሥር እንዳኖሩት በነገረ ማርያም በሰፊው ተነግሯል። ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ጹመው/ጾመ ፍልሰታን/ አካሏን በሱባኤ ከተቀበሉ በኋላ በጌቴ ሴማኒ ቀብረውታል። በኋላም በቤ ተ ክርስቲያን ትውፊት እደተገለጸልን ጌታ በክብር አስነሥቷታል። በዚህም ታሪክ «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወእረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦትም »/መዝ 131፥8/ ያለው የዳዊት መዝሙር ተተርጉሞበታል ።
ዕረፍቷም የእግዚአብሔርን የተስተካከለ ፍትህ እንደ ሚያመለክት ቅዱስ ያሬድ ይናገራል። እንዲህ ብሎ «እንበይነ ዝ አእምሩ በውስተ ፍትህ ከመ ኢያደሉ፤ ትጥአም ሞተ እሙ ወእመ ኩሉ አዘዘ ወልድ በርቱዕ ቃሉ » ማለትም «ክርስቶስ በፍርድ እንደማያደላ በዚህ እወቁ፣ የሁሉ እናት የሆነችው እናቱ እንደሁሉ ሞትን ትቀምስ ዘንድ በማይታጠፍ ቃሉ አዝዟልና።» ማለት ነው። ጉዳዩ በሌላ አንጻር ሲታይ ደግሞ በዚህ የሙታንና የሕያዋን ዓለም ላይ እጅግ አስፈሪ ሁኖ ይታይ የነበረው የሞትና የመቃብር ኃይል በውድ ልጅዋ ሞትና ትንሣኤ የተደመሰሰና ግርማው የተገፈፈ እንደ መሆኑ መጠን/1ቆሮ15፥55/ ለዚህ ታላቅ ድል የዐይን ምስክር የሆነችው የሕይወት እናት ማርያም የሞትን ጽዋ እንደ ማንናውም ሰው ለመቀበል የምትፈራ ቢሆን ኑሮ እርስዋ የፈራችውን ሞት ያለ ቀቢጸ ተስፋ ደፍሮ ለመቀበል የሚችል ክርስቲያን ማን ሊሆን ይችል ነበር? በሌላመልኩ ደግሞ የሰው ልጅ ሁሉ /1ቆሮ15፦51/ (እያንዳንዱ ሥጋ ለባሲ) የሞትን መድረክ እየረገጠ እንዲያልፍ የወሰነ አምላክ፣ እናቱም ሰው እንደመሆኗ በሞተ ሥጋ እንድታልፍ በማድረግ ፍትሁ ርቱዕ መሆኑን አስተማረ። ይሁን እንጅ ሞቷ የክብር ሞት ጻዕር የሌለበት ዕረፍት ነብር። ዳዊት በመቶ አሥራምስተኛው መዝሙር« ክቡር ሞቱ ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር » ካለ ቅዱሰ ቅዱሳንን በአካሏ ያስተናገደቸው የቅድስት ድንግል ማርያም እርፍትማ እንዴት ባለ ክብር ተከናውኖ ይሆን!
ፍልሰታ ለማርያም
ከዚህ በኋላ መላክት በፈቃደ እግአብሔር ከሱባኤ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን አብረዋት በ16 ጌታ አስነስቷታል። በክብርም በቀኙ አኑራታል። ንግሥቲቱ በቀኙ ለዘለዓለም ትኖራለች። ያም የክብር ቦታ በሃይማት ለመሰላት በልጇም ለመኑ ምዕመንን ሁሉ የተዘጋጀ የክብርና የሕይዎት ቦታ ነው። በቤተ
ምስጋናና ክብር የሰውን ባህርይ ላከበረ ለእግዚአብሔር ይሁን። www.kidusyared.org
ምንጭ
-ሥርዐተ አምልኮ ክፍል ሁለት በምምህር ልዑለቃል አካሉ /ያልታተመ/
-ሥርOተ አምልኮ ክፍል አንድ
-ቃለ ጽድቅ ኦርቶዶክሳዊ
-ማዕዶት መጽሄት 1976 ዓም ሰዓሊ ለነ ቅድስት
-ትርጓሜ ውዳሴ ማርያም ምልክት /ያልታተመ/

