አዲስ ነገር በማንኛውም መንገድ አስደሳችና ውድ ዋጋም አለው። አዲስ ነገር ልብስም ከሆነ ሲለብሱት፣ መኪናም ከሆነ ሲነዱት፣ ቤትም ከሆነ ሲገቡበት፣ አዲስ መጽሐፍ ሲያነቡት፣ አዲስ አገር ሲጎበኙት ደስ ይላል። አዲስ ነገር ጥንቃቄ ያሻዋል። አዲስ አመት/ ዘመን በአዲስ በጀት፣ በአዲስ እቅድ አዲስ ሥራ የሚሰራበት ወቅት ነው። በአዲስ ዓመት ብዙ ነገር ይለወጣል። ተማሪዎች ከከፍል ወደክፍል ይዛወራሉ፣ በከፍተኛ ተቋም የሚማሩም ተማሪዎች የጨረሱት ወደ ስራ ዓለም ሲሰማሩ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ደግሞ ኮሌጆችን እናዩኒቨርስቲዎችን ይሞላሉ። ሁሉም ያድጋል። በአንጻሩ ባለፈው አመት የነበሩ ብዙ ሰዎች በሞት ሲወሰዱ፣ ልጆች የነበሩት ደግሞ በእድሜ፣ በዕውቀት፣ በአመለካከት በመላቅ የአበውን ስፍራ ይወስዳሉ። ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ ሙሉ ሰዎች ይሸመግላሉ። ወጣቶች ሙሉ ሰው ወደመሆነ ያድጋሉ፣ ልጆች የነበሩት ደግሞ ይጎለምሳሉ። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ የዕድሜአችን መጠን ይጨምራል። ምናልባትም ብዙ ሰዋች የመጨረሻ ዓመታቸውን አንድ ሊሉ ይችላሉ። በመንግስት ደረጃም ፖሊሲዎች ይወጣሉ። አዳዲስ መመሪያውች ይወጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አመት ሲጀመር የፖለቲካ ለውጥም በዚያ አመት ሊካሄድ ይችላል። አዲስ አመት በራሱ ያልታወቀ አጀንዳ አለው። በዚያ አመት በእግዚአብሔር ኃይልና በተፈጥሮ ህግ የሚከናወኑ ለውጦች ከመከናወናቸው ቀድመው ምን እንደሚመስሉ ስለማናውቅ ታሪካዊ ክብርም ወደፊት በአዲስ ዓመት ይገለጻል። በአገራችን አዲስ አመት ልዩ ትርጉም አለው። ሰው ብቻ ሳይሆን ተራራውም፣ጋራውም ፣ ሜዳውም፣ ሸለቆውም ልብስ ይቀይራሉ። በልምላሜ በአበባ ያጌጣሉ። ወንዞችም ድፍርስነታቸውን ጠርገው ጥለው/ሽረው ኩልል ብለው ጠርተው ጥሩ ውሃ ይሆናሉ። በደመና ተጋርዶ ፊቱ ጠቁሮ የነበረው ሰማይም ጠርቶ በከዋክብት አጊጦ ይታያል። ይህ ሁሉ ነገር ለኛ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ውብ የተፈጥሮ ሥርዐት ነው። የምድር አፈር እና ቆሻሻ ጠርጎ በመውሰድ ጎሽቶ ደፍርሶ የነበረው ወንዝ ሲጠራ፣ የሰው ልብ እንደደፈረሰ ከዓመት ወደ ሌላ ዓመት መሸጋገር የለበትም። ተራሮች ሲለመልሙ እና ሲያብቡ የሰው ልጅ ግን እንደደረቀ እና እንደጠወለገ በቃሉ ሳይርስ እና ሳያብብ ሳያፈራ ከዓመት ወደ ዓመት መሸጋገር የለበትም። ሰማይ ሲጠራ የሰው ልብ እንደጨለመና ፊቱም በወንድሙ ላይ እንደጠቆረ (እንደዳመነ) መቀጠል የለበትም። ድፍርስ ልብ ይጥራ፣ የከፋውም ልብ ይብራ፣ የጠቆረ ሕይወት ይጥራ፣ ደረቁም ይለምልም፣ ያልጸናውም ሕይወት ይጽና ። “አዲስ” የሚለው ቃል በአመት አንድ ጊዜ ብቻ የምናስታውሰው፣ በአንድ ወቅት ታይቶ የሚጠፋ የአደይ አበባ ሳይሆን ሁልጊዜ በቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩት ለዕለታዊ እና ዘላለማዊ ህይወት የሚጠቅም የሕይወት መልእክት አለው።
አዲስ ነገር በክርስቶስ ፦ በአለፈው አመት በብሉይ ኪዳን ዘመን አዲስ አመት ሐዲስ ኪዳን እንደሚመጣና ሁሉም አዲስ እንደሚሆን ተነግሮ ነበር። እንዲህ ተብሎ “እነሆ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ” ኢሳ 43፥ 18-19። ይህ አዲስ ነገር ምንድነው እያልን እንደሆነ በብዙ መንገድ የአዲሱን ነገር ሁኔታ መጽሐፈ ጥበብ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል።
- አዲስ ነገር ከህግ ወይንም ከውል አንፃር ሲታይ “ሐዲስ ኪዳን” ነው። ስለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት ተባርከው ይመሰክራሉ። የኃዘን እና የዕንባ ሰው ኤርሚያስ “እነሆ አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል እግዚአብሔር” ብሎ ተናገረ ኤር 31፥ 31-34። ይህንን የተስፋ ቃልም ሀዋሪያው በዕብራውያን መልዕክቱ አብራርቶ ጽፎታል። ዕብ 8፥7-13 ይመልከቱ። “አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል” በሎ አጠቃሎታል። በነቢያት የሚነገረው ተስፋ የሚፈጸምበት ብሉዩ ውል በአዲስ የሚተካበት፣ አሮጌው የሞት አመት (ዓመተ ኩነኔ) አልፎ ዓመተ ምህረት የሚተካበት ዕለት ሲደርስ መድሀኒታችን የአዲሱን ዓመተ ምህረት ውል እና የሕይወትሰነድ ሲያጸድቅ “ይህ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” በማለት የታተመ የህይወት አዋጅ በአዲሱ ዓመተ ምህረት መታወጁን ገለጸ። ማቴ 26፥28-29። ቀደም ሲል ስለአዲስ ዓመት ስለ ዓመተ ምህረት (ዓመተ እግዚእ) ለድሆች ወንጌልን፣ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለዕውሮች ማየትን፣ ለተጠቁት ነጻነትን የሚሰብክበትና የሰበከበትን ዓመተ ምህረት ሊያውጅ መምጣቱን “የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” ብሎ አስተምሮ ነበር። ሉቃ 4፥17-19
- አዲስ የሚለው ቃል ከሕይወት አንጻር ሲታይ “አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።
ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው። አሮጌው ነገር አልፎአል። እነሆ ሁሉም ነገር አዲስ ሆኖአል” (2 ቆሮ 5፥17) ብሎአል። በዔፌሶን መልዕክቱም “በአዋጅ የተነገሩትንም የትዕዛዝ ህግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥልግድግዳ በስጋው ያፈረሰ ይህም ከሁለታቸው አንድ አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምን ያደርግ ዘንድ ጥልንበመስቀሉ ገድሎ…” ብሎአል። (ምዕ 2፥15-17)
- ከሰባዊነት አንጻር ሲታይ ደግሞ “አዲስ ሰው መሆን” ነው።
በአዳም ኃጢያት ብልየት (እርጅና) የገኘው ህይወቱን «ሞት ነው እርጅና? ምክንያቱም ሲያረጅ የህይወትን ዛፍ እየበላ እየታደሰ እንዲኖር ነበር የሚል አስተምሮ አስታውሳለሁ እና ትንሽ ግራ ገባኝ» በወንጌል እና በክርስቶስ ደም ቀድሶ ጠላት ሁለተኛ የማይዘው አዲስ ሰው መሆን ማለት ነው። ስለዚህም ሐዋሪያውም ለቆላስይስ ቤተክርስቲያን “እርስ በእርሳችሁ በውሸት አትነጋገሩ። አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና የተፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል ዕውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታልና” (“ቆላ 3፥8-11) አለ። ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን ሲጽፍ “አሮጌው ሰው (አዳማዊው ጠባይ) አስወግዱ በአእምሮአችሁ መንፈስ ታደሱ። ለእውነትም የሚሆን ጽድቅና ቅድስና እንደእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” በማለት በደል የነገሰበትን ጥል ክርክር የበዛበት የሞት ጥላ ያረፈበት የድካምና ጭንቀት ያየለበት በኃጢያት የደነዘዘና የገረዘዘ፣ ያረጀና ያፈጀው መንፈሳዊና ሥጋዊ አካላችን በክርስቶስ ታድሶ፣ ተቀድሶ፣ልቆ፣ ከብሮ እንዲኖር አስተምሮናል።
- ከባሕርይ ለውጥ አንጻር ሲታይ ደግሞ “አዲስ ልብ ማግኘት” ማለት ነው።
እግዚአብሔር አስቀድሞ በቃሉ አገልጋዮች በነቢያት በኩል በሕገ እግዚአብሔር ላይ የማያምጽ ሕጉ የተሳለበት፣ መሲህ የነገሰበት የጽድቅንና ሰላምን የሚያስብ ተወዳጅና ሌላውን ወዳጅ፣ ቅን ልብ ለህዝቡ እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር። ትንቢቱም ፍጻሜውም በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎአል። ትንቢቱን ከነቢያት ትንቢት እናነባለን። ሕዝ 11፥19-21፤ ሕዝ 18፥31 ሕዝ 36፥26
በሐዲስ ኪዳን አዲስ የተሰበረ ልብ እንደሚኖረን ያስተምረናል። “በልባቸው መታደስ ተለወጡ” ሮሜ 12፥2። “የክርስቶስ ልብ አለን” 1ቆሮ 2፥16። “ህያው እግዚአብሔርን የሚያስከዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ ከእያንዳዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ… ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ” ዕብ 3፥12-18 ተብሎ ተጽፎአል። አዲስ ውል ከአምላኩ ጋር የተስማማ የሐዲስ ኪዳን ሰው በክርስቶስ በሐዲስ ተፈጥሮ የተፈጠረና አዲስ ልብ ያለው፣ የአዲስ ዘመን ሰው አዲስ ሰው ነው። መነሆኑም
- በአዲስ መንገድ ይጓዛል (ይሄዳል)
ከሞት አቅጣጫ ይመለሳል፣ አረማመዱን ያቀናል። ክርስቶስ በደሙ በመረቀው እና በተከፈተው አዲስ የሕይወት ጎዳና ይጓዛል። ዕብ 10፥19፤ ዮሐ 14፥6
- በአዲስ ሕይወት ይመላለሳል
የተጣለውንና ተስፋ የቆረጠውን ደካማ ሕይወት በክርስቶስ አዲስ ሕይወት ይተካዋል። “ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው” ሰቆ ኤር 3፥23 በተባለው በእግዚአብሔር ምህረት ጸንቶ ይኖራል። የአመታት፣ የዕለታት መለዋወጥ አይሽረውም። ሮሜ 6፥4 ፤ ኤፌ 4፥17
አንባቢ ሆይ! በእግዚአብሔር ቸርነት ለአዲሱ ዘመን ብንበቃም ዘመኑ ሊለውጠን እንደማይችል እንደአምናና ዘንድሮም ዓመቱ እንደሚያልፍ ልብ ማለት ጊዜና ወቅት እንደማይለውጠው የሕይወት ለውጥ፣ ቅድስና ለመጐናጸፍ ምን ያክል ተዘጋጅተዋል? ይበሉ አዲስ ዘመንዎን ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖሩበት፣ የሕይወት ዓመት ይሁንልዎ ዘንድ ይትጉ። አመት በተለወጠ ቁጥር በማስታወሻ ወረቀታጭን እራስጌ ላይ የሚቀያየረውን ዓመተ ምህረት ቀን እንደምንጽፍ ሁሉ ሕይወታችንንም በእድገት ሊለወጥ ይገባዋል። አሮጌ ባሕርይዎን ያስወግዱ።
መጋቤ ሐዲስ ምምህር ልዑለቃል አካሉ
ክብረ ቅዱሳን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያትል ዋሽንግተን !


