እንኳን ለጥር ማርያም በሰላም በጤና እግዜር አደረሳችሁ።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞት ያስደነገጣቸው ፣ የጨለማውም ገዥ የዛተባቸው ፥ ሞትና መቃብር ተስፋ ያስቆረጣቸው የአባቶቿንና የእናቶቿን ፍርሃት የሻረው ጌታ እናት በመሆኗ እመቤታችን ትባላለች ። ለሰው ልጆች ሁሉ ሞትንና መቃብርን ድል የነሣውንና በእባቡ ራስ ላይ የቆመውን መሲሕ በመውለድ የልባቸው እንዲደርስ ምክንያት ሁናለች ፤ የተስፋውንም ዘር ወልድን በዚህ ዓለም ላይ አስተናግዳለች ።
ድንግል በልደቷ ጊዜና በልጅነቷ የወላጆቿን ኀዘን አስረስታለች ፤ የዓለም የድኅነት ጊዜ መቃረቡን አብሥራለች ። ድንግል በሔዋን የተዘጋውን የገነት በር አስከፍታለች ፤ ድንግል ሰማይና ምድር የተገናኙበት መሰላል ለመሆን በቅታለች ። ያም ማለት ሰውና እግዚአብሔር ፣ ሰውና መላእክት ፣ በእርስዋ ሕይወት በተከናወነው በምሥጢረ ሥጋዌ ወይም በአካለ ቃልና ትስብእት ተዋሕዶ ምክንያት አንድ ሁነዋል ማለት ነው ። ሕያውን በመውለድ የሕያዋን እናት የተባለችውን የሔዋንን ስም በተግባር ተረጉማዋለች ። እርስዋም የሕያዋን እናት ተባለች ። ድንግል የመልአከ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤልን ዜና በመቀበል ፣ በሔዋን ጀሮ የተሰማውን የመልአከ ጽልመትን የሐሰት ዜና ሽራለች ፤ ድንግል ጠላት ለጥፋትና ለመሳለቂያ /ፍና ተሳልቆ/ «አምላክ እንድትሆኑ» ብሎ የቀለደበትን እና ያታለለበትን ቃል ፣ ለአምላክ ማደርያ ለመሆን በመፍቀድዋ ፣ የተዘበተበት የሰው ልጅ ባሕርይ በተዋሕዶ ስለ ከበረ ፣ የሰው ባሕርይ አምላክ ለመባል እንዲበቃ ምክንያት ሁናለች ። በመሆኑም ሊቁ ቅ/ያሬድ እንዳለው «ትምክህተ ዘመድነ በወሊዶተ ዚአከ ፤ አንተን በመውለዷ የባሕርያችን መመኪያ ናት» እያልን እናከብራታለን ።
ድንግል በሃይማኖት «እንደ ቃልህ ይሁንልኝ» በማለቷ የማይቻለውን ችላለች ፤ የማይወሰነውን ወስናለች ፣ ማኅደረ ቃለ አብ ሁናለች ። በመታዘዟም አብ ለተወክፎተ ቃለ እግዚአብሔር እንድትበቃ አጽንቷታል ፤ መንፈስ ቅዱስም ጸልሏታል /ቀድሷታል/ ወልድም ሥጋዋንና ነፍሷን ነሥቷል ።
ድንግል ከመልአኩ የተነገረውን የምስጋና ቃል በጉጉት ሳይሆን በሃይማኖት አጣርታ በመቀበሏ በቀላሉ የተታለለችውን እናቷንና የሌሎችን ሴቶች ባሕርይ ሁለተኛ በውዳሴ ከንቱ እንዳይጠለፍ ምሳሌ ሁናለች ።
ድንግል የተጠላው ባሕርየ ሰብእ የተወደባት ፣ የተጣለው የሰው ልጅ የተነሣባት ፣ የረከሰው የተቀደሰባት የተሰደደው ሰው ወደ ርስቱ የተመለሰባት ፣ የሰው ልጅ ሁሉ የባሕርይ መመኪያ ናት ። ድንግል ተስፋ አበው በእርሷ ስለ ተፈጸመ ክብሯ ትልቅ ነው ። ይሁን እንጂ የወልደ እግዚአንሔር እናት በመሆኗ በዚህ ዓለም በሰላም የኖረች አይደለችም ። ብዙ ዋጋ ከፍላ ፣ አውሬ ፥ ዘንዶ ፥እባብ የተባለውን ዲያብሎስን ተዋግታ ፣ በማኅፀኗ ፍሬ ድል ነሽነት ከብራ አስከብራናለች ፤ በልጇ ላይ በደረሰው ሥቃይ ምክንያት በልቧ የኀዘን ሰይፍ ቢያልፍም መከራውንና ልቅሶውን ታግሣ የድልና የክብር እመቤት ሁና በንጉሡ በልጇ ቀኝ ተቀምጣለች ።
ዜና ዕረፍቷን ለማስታወስ ከክርስቶስ የመስቀል አደራ ቃል ብንነሣ መልካም ነው ። ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንደ ጻፈው ። የበጉ እናት ቅድስት ማርያም ለዮሐንስ አደራ ተሰጥታ ነበር ። በዚያች ከባድ ሰዓት በመስቀል ላይ ሁኖ ከተናገራቸው ቃላት መካከል እናቱን በተመለከተ «እነኋት እናትህ» የሚለውና ዮሐንስንም «እነሆ ልጅሽ» ያለው ይገኙበታል ። ዮሐ 19 ፥ 25-26 ።
መከራው በጸናበት ጊዜ እናቱን አልረሳታም ነበር ። ችንካሩ የማያንቀሳቅስ ቢሆንም አንገቱን ወደ እናቱ ዘምበል አድርጎ ደም በጋረዳቸው ዐይኖቹ እናቱን በፍቅር ዐየ ። «አንቺ ሴት» በማለት የአውሬውን ራስ መቀጥቀጥ አበሰረ ፤ ከሴቲቱ የሚወለደው የእባቡን ራስ ይቀጠቅጣል ተብሎ ተነግሮ ነበርና ። ከመስቀሉ ሥር ለነበረው ዮሐንስ አደራ ብሎ እናቱን ሰጠው ። ዮሐንስም ወደ ቤቱ ወሰዳት ፤ ከዚያ በኋላ እመቤታችን አሥራ አምስት ዓመታት ብቻ እንደ ኖረች የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይገልጻል ። ጠቅላላ ዕድሜዋ 64 ዓመት ነው ። በዜና ዕረፍቷ ላይ ቤ/ክ ያቆየችልን ታሪክ እንዲህ ይላል ። «በተወለደች በ64 ዓመቷ በዘመነ ሉቃስ ጥር 21 እሑድ ቀን ዐርፋለች» ይህም ሊሆን የቻለው ከእናት ከአባቷ ጋር 3 ዓመት ፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት ፣ በቤተ ዮሴፍ ዘጠኝ ወር ፣ ከጌታ ጋር 33 ዓመት ፣ በቤተ ዮሐንስ 15 ዓመት ፣ ድምር 64 ዓመት ያለው ይህ ነው ። የዕረፍቷም ጊዜ ካሳ ከተፈጸመ ፣ ፀሐየ ጽድቅ ወንጌል ካበራች፣ ምድራችን ለፍሬ ወንጌል ከበቃች ፣ የጨለማውና የጭጋጉ ዘመን ካለፈ ፣ ጉሙ ደመናው ከተገፈፈ ፣ ክረምተ ኦሪት ካለፈ ፣ መከሩ ጸጋ ወንጌል ከተትረፈረፈ በኋላ ነበር ።
ስለዚህ «ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ ፦ ወዳጄ ሆይ ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ ፥ ነዪ ። እነሆ ፥ ክረምት አለፈ ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ ፤ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ ። በለሱ ጐመራ ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ» ብሎ አባቷ ንጉሥ ሰሎሞን የተናገረውን ያስተረጉማል ። መኃ 2 ፥ 10-14 ።
ከዕረፍቷም በኋላ አይሁድ ሐዋርያት ሥጋዋን በክብር እንዳያሳርፉት በመቃወማቸው መላእክት በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እንዳኖሩት በነገረ ማርያም በሰፊው ተነግሯል ። ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ጹመው /ጾመ ፍልሰታን/ ክቡር ሥጋዋን በሱባኤ ከተቀበሉ በኋላ በጌቴ ሴማኒ ቀብረውታል ። በኋላም በቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደ ተገለጸልን ጌታ በክብር አስነሥቷታል ። በዚህም ታሪክ «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦትም» ያለው የዳዊት መዝሙር ተተርጉሞበታል ። መዝ 131 ፥ 8 ።
ዕረፍቷም የእግዚአብሔርን የተስተካከለ ፍትሕ እንደ ሚያመለክት ቅዱስ ያሬድ ይናገራል ። እንዲህ ብሎ «እንበይነ ዝ አእምሩ በውስተ ፍትሕ ከመ ኢያደሉ ፤ ትጥዐም ሞተ እሙ ወእመ ኩሉ አዘዘ ወልድ በርቱዕ ቃሉ» ማለትም «ክርስቶስ በፍርድ እንደማያደላ በዚህ እወቁ ፣ የሁሉ እናት የሆነችው እናቱ እንደ ሁሉ ሞትን ትቀምስ ዘንድ በማይታጠፍ ቃሉ አዝዟልና» ማለት ነው ። ጉዳዩ በሌላ አንጻር ሲታይ ደግሞ በዚህ የሙታንና የሕያዋን ዓለም ላይ እጅግ አስፈሪ ሁኖ ይታይ የነበረው የሞትና የመቃብር ኃይል በውድ ልጅዋ ሞትና ትንሣኤ የተደመሰሰና ግርማው የተገፈፈ በመሆኑ ። ለዚህ ታላቅ ድል የዐይን ምስክር የሆነችው የሕይወት እናት እመቤታችን ድንግል ማርያም ፥ የሞትን ጽዋ እንደ ማንኛውም ሰው ለመቀበል የምትፈራ ቢሆን ኑሮ ፥ እርስዋ የፈራችውን ሞት ያለ ቀቢጸ ተስፋ ደፍሮ ለመቀበል የሚችል ክርስቲያን ማን ሊሆን ይችል ነበር ? ። 1ቆሮ 15 ፥ 51 ። 1ቆሮ 15 ፥ 55 ።
በሌላ መልኩ ደግሞ የሰው ልጅ (እያንዳንዱ ሥጋ ለባሲ) የሞትን መድረክ እየረገጠ እንዲያልፍ የወሰነ አምላክ ፣ እናቱም ሰው እንደ መሆኗ በሞተ ሥጋ እንድታልፍ በማድረግ ፍትሑ ርቱዕ መሆኑን አስተማረ ። ይሁን እንጂ ሞቷ የክብር ሞት ፥ ጻዕር የሌለበት ዕረፍት ነበር ። ዳዊት በመቶ አሥራ አምስተኛው መዝሙር «ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር» ካለ ፥ ቅዱሰ ቅዱሳንን በማኅፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስተ ቀን የተሸከመችው የቅድስት ድንግል ማርያም ዕርፍትማ እንዴት ባለ ክብር ተከናውኖ ይሆን !
ፍልሰታ ለማርያም
ከዚህ በኋላ መላክት በፈቃደ እግአብሔር ከሱባኤ በኋላ ነሐሴ 14 ቀን ቀብረዋት በ16 ጌታ አስነሥቷታል ። በክብርም በቀኙ አስቀምጧታል ። ንግሥቲቱ በቀኙ ለዘለዓለም ትኖራለች ። ያም የክብር ቦታ በሃይማኖት ለመሰላት ፥ በልጇም ለሚያምኑ ምእመናን ሁሉ የተዘጋጀ ዘላለማዊ የክብርና የሕይወት ቦታ ነው ። ምስጋናና ክብር የሰውን ባሕርይ ላከበረ ለእግዚአብሔር ይሁን ።

