መጋቢት መድኃኔ ዓለም ጥንተ ስቅለት ነው ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርአያ እና ለቤዛ ሰው ሁኖ ሥጋ ለብሶ መጣ ። ሠላሳ ሦስት ዓመት በዚህ ዓለም ላይ ቆየ ። በቅዱስ ወንጌል የተጻፈልን ዜና እንደሚያስረዳን የኢየሱስ ክርስቶስ ዜና የተጻፈው ከልደቱ አሥራ ሁለት ዓመት እስኪሆነው ድረስ ያለው እና (ያውም በከፊል እና በአጭሩ ነው) ከዚያም አልፎ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ያሉት ሦስት ዓመታት እና ሦስት ወራት አገልግሎቱ በከፊል ነው ።
ቤተ ክርስቲያን በዓለ ስቅለት ሁልጊዜ ዓርብ ቀን እንዲውል ፣ ትንሣኤም እሑድ ቀን እንዲውል እና ሌሎችም ዕርገት ከሐሙስ ፣ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ እንዳይወጣ ለማድረግ በቀመር ትምህርቷ ስላስተካከለች ፥ የትንሣኤውን እና የስቅለቱን በዓል በልዩ ልዩ ወራት “ኢየዓርግ እና ኢይወርዱ” እንደ ተጠበቀ ሁኖ ይከበር እንጂ የመጀመሪያው ታሪካዊና መንፈሳዊ ዕለት /ጥንተ ስቅለቱ/ መጋቢት 27 ትንሣኤውም መጋቢት 29 ነበር ። ስለዚህ አሁን በዚህ ዕለት ስለ ስቅለቱ “መድኃኒት በቀራንዮ” በሚል ርእስ እንማራለን ።
በዐራቱ ወንጌላት እንደምናነበው ያልበደለው ጌታ ስለ እኛ የበደለኛነት ብያኔ ተበይኖበት ፣ ካህናት ፥ የአገር ሽማግሌዎች ፥ የሃያማኖት መሪዎችና የአገር መሪዎች ተስማምተው እንዲሞት ዓርብ ጧት መጋቢት 27 ቀን ተወሰነ ። ውሳኔው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርፋት ባለቀ አካሉ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ እንዲሄድ ተደረገ ። ከእርሱ ጋር አብረው የሚሰቀሉ ሁለት ወንበዴዎችም ነበሩ ። የብሉይ ኪዳን ካህናት የተረገመ ነው ብለው ከኢየሩሳሌም ከተማ እንዲወጣ አደረጉት ። ቅዱስ ጳውሎስ “ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ” እንዳለ ። ዕብ 13 ፥ 12 ።
በብሉይ ኪዳን የኃጢአት መሥዋዕት የሚሆን በግ ከከተማ መውጣት እንደ ነበረበት ፣ ክርስቶስም የኛን በደል ተሸክሞ ይሰቀል ዘንድ ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ወደ ቀራንዮ ኮረብታ መስቀሉን ተሸክሞ ተጓዘ ። ዘሌ 16 ፥ 27 ።
መሲሑ ሲለያት ያንጊዜ ኢየሩሳሌም ክብሯን አጣች ። ያንገላቱት አይሁድ ለመስቀል ሳይበቃ በመንገድ ላይ ሕይወቱ ሊያልፍ እንደሚችል ስለ ገመቱ ፣ ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው መስቀሉን በመሸከም እንዲያግዝ አስገደዱት ። ይህ ሰው ሳያስበው የበረከተ መስቀሉ ተሳታፊ ሁኗል ። ማር 15 ፥ 21 ።
በዚህ አድካሚ ጉዞ ላይ የክርስቶስን መከራ እየተከታተሉ የነበሩ የዐይን ምስክሮች የሆኑት የክርስቶስ ተከታዮች ብዙዎች አልነበሩም ። ከሐዋርያት አንድ ሰው ብቻ ነበር ፥ ይህም ዮሐንስ ነበር ። ሌሎችም ሴቶች ነበሩ ። ሴቶቹም በጽኑ ያለቅሱለት ስለ ነበረ መድኃኒታችን “በዝ ዕፅ ርጡብ ከመዝ ዘገብሩ እፎኑመ በይቡስ = በዚህ እርጥብ እንጨት እንደዚህ ያደረጉ በደረቁ እንዴት ሊያደርጉ ነው ? አለ ። ሉቃ 23 ፥ 3 ።
ይህም ማለት ከንግግሬ ሐሰት ከሥራየ ስሕተት የሌለብኝ በሆንኩት በእኔ እንዲህ ያደረጉ በሩቅ ብእሲ ሰው ላይ እንዴት ያለ መከራ ያደርሱበት ይሆን ? ማለት ነው ። ሴቶችን ግን ስለ እኔ አታልቅሱ ስለ እናንተ ስለ ራሳችሁ አልቅሱ አላቸው ። በዚህም አጋጣሚ በኢየሩሳሌም ጥፋት ጊዜ ምን ያክል መከራ እንደሚመጣ አመለከታቸው ። ሉቃ 23 ፥ 28 ።
ዛሬም ማልቀስ ያለብን ስለ ኃጢአታችን ነው ። ክርስቶስን ለሞት ያበቃው የእኛ ኃጢአት ዛሬም እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ሁኖ በእኛ ላይ ነግሦአልና ። እንባ ለክርስቶስ አስፈላጊ አልነበረም ። አስፈላጊ የሆነው ለእኛ እና ለምንኖርበት ምድር ነው ።
ቀራንዮ ላይ ክርስቶስ ከወንበዴዎች ጋር የሚሰቀልበት ጊዜ ሲደርስ ልብሱን ገፈፉት ። በዚህ ጊዜ ሰውነቱ በሙሉ ቆሰለ ፥ ልብሱም ከቁስሉ ጋር ተያይዞ ስለ ነበር ልብሱ ብቻ ሳይሆን አካሉ እንዴት እንደ ተገፈፈ በዓይነ ሕሊና ማየት ይቻላል ። ሰውነቱም እንደ ገና ቆስሎ ደሙ እንደ ውኃ ፈሰሰ ። ልብሱን ወታደሮች ዕጣ ተጣጣሉበት ፤ እርሱም ዕርቃኑን በመስቀል ላይ ተሰቀለ ። በዚህ ጊዜ ነበር የእኛ ኃፍረት የተጋረደው ። ከገነት ዕርቃናችን እንደ ወጣን እንኖር ነበር ። ነገር ግን ክርስቶስ ሐዋርያው “ወመነና ለኃፍረት = ኃፍረትን ናቃት” እንዳለ ። ዕብ 12 ፥ 2)
የእኛን ነውር ለመጋረድ ዕርቃኑን በመስቀል ላይ ዋለና ነውራችንን ሁሉ ጋረደ ። በወቅቱ ብዙ ተናጋሪ በነበራቸው ሦስት ቋንቋዎች በዕብራይስጥ ፥ በአራማይክ ፥ በግሪክ “ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ” ተብሎ ተሰቅሎ እንዲሞት የተፈረደበት ወንጄሉ ተጻፈ ። ያም የሆነበት ምክንያት በዚያ ዘመን በነበረው ልማድ መሠረት የተሰቀለው ሰው ሙሉ ስም እና የሠራው ወንጀል በመስቀል ላይ ይጻፍ ስለ ነበረ ነው ። በቀኝ እና በግራ እንደ ተሰቀሉት ሰዎች ወንጀሉ ይህ ነው ብለው የሚጽፉት ስላልነበር ጲላጦስ ስሙን ከነመዓርጉ እንዲጻፍ አደረገ ። ሲሰልሉ ኑረው በዚህ ምክንያት ተሰቀለ የሚያሰኝ አንድም ወንጀል አላገኙበትም ነበርና ። «የዚህ ዓለም ገዥ ወደ እኔ ይመጣልና በእኔ ላይም አንዳች የለውም» ብሎ ጌታ እንደ ተናገረ ። ዮሐ 14 ፥ 30 ።
ጌታችን ምንም በደል አልተገኘበትምና ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ ከዘመናት በፊት «ወኢተረክበ ሀሰት ውስተ አፉሁ = ሀሰት በአንደበቱ አልተገኘም» ያለው ቃል ደረሰ ተጸመ ። ኢሳ 53 ፥ ። 1ጴጥ 2 ፥ 22 ።
ከዚህ በኋላ ዳዊት በመዝሙሩ “ቀነዉኒ እደውየ ወእገርየ = እጆቼን እና እግሮቼን ቸነከሩኝ” እንዳለ ። መዝ 21 ፥ 16 ።
አዳምን የፈጠሩ እጆቹ ሲቸነከሩ ፥ እኛን ለመፈለግ በምድር ላይ የተመላለሱት እግሮቹ በምስማር ሲመቱ ተፈጸመ ።
ተጠማሁ ባለ ጊዜም የመስቀል ቅጣት ከልክ በላይ ተቀጩን መከራ ስለሚያበዛበት ሆምጣጤ በመስጠት ሰውነቱ እንዲዝል እና የመከራውን ስሜት እንዲቀንስለት የሚያደርግ መጠጥ ይሰጥ ነበር ። ክርስቶስ ግን አልጠጣውም ፤ ስቃያችን በሙሉ ሊቀበል ስለ ወደደ ስለ እኛ እንዲሁ ተሰቃየ ። በልደቱ ከተገበሩለት ስጦታዎች አንዱ የሆነውን ከርቤን ተቀብሎ ነበር ፤ አሁን ግን አልተቀበለውም ። ማቴ 27 ፥ 34 ።
በመጨረሻ ግን ሁሉንም መከራዎች ከፈጸመ በኋላ ሆምጣጤውን ቀምሶ ተፈጸመ እንዳለ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ ጽፎአል ። «ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ፦ ተፈጸመ አለ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ» ዮሐ 19 ፥ 30 ።
በመድኃኒታችን መስቀል ዙሪያ የነበሩት ወዳጆቹ ጥቂቶች ነበሩ ። ሐዋርያው ዮሐንስ ፣ መግደላዊት ማርያም ፣ እናቱ ቅድስት ማርያም እና ሌሎችም ነበሩ ። ዮሐ 19 ፥ 25 ።
መድኃኒታችንም በመስቀል ላይ ሳለ በሰማይም በምድርም ብዙ ተአምራት ተደርገዋል ። ፀሐይ ጨልሟል ፥ ጨረቃ ደም ሁኖአል ከዋክብት ረግፈዋል ፥ ። ቀኑ ጨልሟል ፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀዷል ፤ ምድርም ተናውጣለች ፥ አዕባን ተፈትተዋል ፥ መቃብራት ተከፍተዋል ፥ ሙታን ተነሥተዋል ። ማቴ 27 ፥ 45-53 ።
ሰብዓቱ አጽርሐ መስቀል
መድኃኒታችን በመስቀል ላይ ሳለ ሰባት ጊዜ ተናግሯል ። እነዚህ ሰባት ቃላት “ሰብዓቱ አጽርሐ መስቀል” ተብለው ይታወቃሉ ። የተሰቀሉ ሰዎች ከስቃያቸው ጽናት የተነሣ እንደሚጮሁት ያለ ከንቱ ጩኸት ሳይሆን ፣ ጌታችን በመስቀል ላይ የተናገራቸው ቃላት ሰዎች ሁሉ ከዚያም አልፎ በዚያች ቅጽበት ለሚሰቃዩት ሁሉ እንኳ ታላቅ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ጩኸት ነበር ።
1/ «አባ ስረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ = አባት ሆይ ! የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» ሉቃ 23 ፥ 34 ።
በዚህ ጩኸቱ አንደኛ ጌታ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” ብሎ ያስተማረውን ወንጌል በመስቀል ላይ በሥራ ላይ በማዋል ለእግዚአብሔር ቃል ታማኞች መሆን እንዳለብን አስተምሮናል ።
ሁለተኛ ለጠላቶቹ ምሕረት ለምኖላቸዋል ። ባለማወቅ እንደ በደሉ በመናገር ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠየቀ ። በእርግጥም አውቀውት ቢሆን የክብርን ንጉሥ ባልሰቀሉትም ነበርና ። 1ቆሮ 2 ፥ 8 ።
ይህ ቃል ተስፋ የመቁረጥ ፣ ሞትን የመፍራትና ሰቃዮችን የማውገዝ መልእክት የያዘ ሳይሆን ፥ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ሁኖ ሰላምን ለምድር ለማውረድ ሰው የሆነው የዓለም ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን መሠዊያ ፥ እራሱን መሥዋዕት ፥ ራሱም ሊቀ ካህናት ሁኖ የማስታረቅ አገልግሎትን በራሱ ደም ሲመሠርት እናያለን ። እርሱ እራሱ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ሊቀ ካህናት ነውና ። 2 ቆሮ 5 ፥ 19 ። ዕብ 9 ፥ 15 ፤ ዕብ 5 ፥ 7 ።
የሚያደርጉትን አይውቁም የተባሉት የሰቀሉት ብቻ አልነበሩም ፤ የሰው ልጆችን ሁሉ ነው እንጂ ። በመሆኑም የሊቀ ካህናቱ ጸሎት የሰውን ልጅ ባሕርይ ሁሉ የሚመለከት ነበር ። ዛሬም ከዚህ ከመድኃኒታችን ቃል ርኅራኄን ልንማር ይገባናል ።
2/ “ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት = ዛሬ በገነት ከእኔጋር ትኖራለህ ።” ሉቃ 23 ፥ 45 ።
ይህን የምሕረት ቃል የሰማው ፥ ወይም ይህ የሕይወት ቃል የተነገረው ደግሞ በመተላለፍ ኑሮ በኃጢአቱ ተሰቅሎ ለነበረው ፈያታዊ ዘየማን ነው ። መድኃኒታችን ሁለተኛ ሲመጣ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን በግራው እንደሚያቆም በቅዱስ ወንጌል አስተምሮናል ። ማቴ 25 ፥ 31-46 ።
በቀኝ በክርስቶስ ይቅርታ የጸደቀው ፈያታዊ ዘየማን መሰቀል ፣ በግራ ደግሞ ያልጸደቀው ወንበዴ መሰቀል ፣ እና በመካከል የቆመው የክርስቶስ መሰቀል በመጨረሻው የፍርድ ቀን ኃጥአን በግራ ጻድቃን በቀኝ መቆማቸውን ያመለክታል ። ይህን የምሕረት ቃል የሰማው ተነሳሒ ፈያታዊ ዘጸጋም ከጓደኛው ጋር መጀመሪያ ላይ ተመሳሳይ አቋም በተሰቀለው ኢየሱስ ላይ የነበረው ቢሆንም ። በኋላ ግን የክርስቶስን ጌትነት በክርስቶስ ጸሎት እና በተደረጉት ተአምራት አውቆ ። ማቴ 27 ፥ 44 ። ሉቃ 23 ፥ 31 ፣ 34 ።
የእነርሱን እና የኢየሱስን መስቀል ማነጻጸር እንደሌለበት ለማስረዳት “ለነሰ ዘበርቱዕ ረከበን = የኛው የተገባ ነው ፥ በኃጢአታችን ነው ። እርሱ ግን ያለኃጢአቱ ነው እና ለምን እንደዚህ ትናገራለህ?” ብሎ ተናዘዘ ፤ በስተመጨረሻ “ተዘከረኒ እግዚኦ አመ ትመጽእ በመንግሥትከ = በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” በማለቱ “ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት = ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ” የሚለውን ግሩም የምሥራች ሰምቷል ። ራስህን አድን እየተባለ ከወንበዴዎች ጋር የተሰቀለው መድኃኔ ዓለም ሕይወትን ፥ ምሕረትን ፥ ዕረፍትን ለተፈረደባቸው ይሰጥ ነበር ። መስቀሉ ለቤዛ ዓለም እንደ ሆነ አምነን ንስሐ ለምንገባ ሁሉ ይህ ቃል ዛሬም ከመስቀሉ ይሰማል ።
3/ «ነያ እምከ…ነዋ ወልድኪ = እነኋት እናትህ…እነሆ ልጂሽ» ዮሐ 19 ፥ 26 ።
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ እናቱን ለዮሐንስ አደራ ሲሰጥ ፥ ዮሐንስንም ለድንግል ልጅ አድርጎ ሲሰጥ የተናገረው ቃል ነበር ። መድኃኒታችን በመስቀል እየተንገላታ ሳለ እናቱን አልረሳትም ። ለታመነው ደቀ መዝሙሩ “ነያ እምከ = እነኋት እናትህ” በማለት ለዮሐንስ አደራ ሰጥቶት ነበር ። ዮሐንስንም “ነዋ ወልድኪ = እነሆ ልጅሽ” ብሎ ሲሰጣት ለዳኑት እና ከመስቀሉ አጠገብ ለተገኙት እናት እንድትሆን ማድረጉን ተምረናል ። እመቤታችን ዛሬም ዮሐንስን ለመሰልን እናታችን ናት ፤ ዮሐንስንም የመሰሉ ሁሉ ደግሞ ልጆቿ ናቸው ።
4/ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ” ማቴ 27 ፥ 46 ።
ከእግዚአብሔር የተለየውን ፣ ረድኤት ያጣውን ፣ በኃጢአቱ ብቸኛ የሆነውን ፣ እንዲሁም የሞት እና የመቃብር ተገዥ የሆነውን የሰውን ልጅ በመወከል እና ለሞት እና ለመቃብር እንዲሁም ለልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ የተሰጠውን ሰው ጩኸት በመስቀል ላይ ሆኖ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” በማለት ጮኸ ። ይህም ጩኸት ስለ እኛ ኃጢአት የካሳ ጩኸት እንጂ የተስፋ መቁረጥ ጩኸት አልነበረም ። ተስፋ የቆረጠ ወደ እግዚአብሔር አይጮህምና ። እግዚአብሔር በኃጢአቱ ምክንያት ለሞትና ለኩነኔ ፣ ለሥቃይና ለረኃብ አሳልፎ የሰጠውን ፣ የተወውን የሰውን ልጅ ያስበው ዘንድ ፥ ያድነው ዘንድ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ «ሥጋከ አንጽሕ ሊተ = ሥጋህን አንጻልኝ» መዝ 39 ፥ 6 ።
መሥዋዕትን አልሻም ባለው አባቱ ፊት የተቀደሰ አካሉን መሥዋዕት በማድረግ የሰው ልጅ በዘለዓለም ሕይወት እንዲታሰብ ጮኸ ። ጩኸቱም ተሰማለት ። ቅዱስ ጳውሎስ «እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት ፤ ምንም ልጅ ቢሆን ፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው» እንዳለ ሁላችንም በእርሱ ዳንን ። ዕብ 5 ፥ 7-9 ።
5/ “ጸማዕኩ = ተጠማሁ” ዮሐ 19 ፥ 28 ።
ከብዙ ደም መፍሰስ የተነሣ ሰውነቱ ተጎድቶ ነበር ። ሰውነቱ በሙሉ በግርፋት ፣ በስቃይና በመስቀል ሸክም አልቋልና መድኃኒታችን በመስቀል ላይ ሁኖ ተጠማሁ አለ ። ባሕርን ፣ ወንዝን ፣ እና ውቅያኖስን የፈጠረ ጌታ ስለ እኛ ተጠማ ። ለእስራኤል ከዓለት ውኃ ያፈለቀው እንዲሁም ሳምራዊቷን ስለ ሕይወት ውኃ ያስተማራት ጌታ ተጠማሁ አለ ። ትንቢተ ነቢያትም በዚህ ተፈጸመ ። መዝ 21 ፥ 15 ፣ መዝ 28 ፥ 20-21) ።
በቃና ውኃውን ለውጦ የወይን ጠጅ ላደረገው ጌታ ተጠማሁ ሲል ሆምጣጤ ሰጡት ። ዮሐ 19 ፥ 28 ።
ጌታችን እኛ እንዳንጠማ ስለ እኛ ተጠማ ። ሉቃ 16:22-25 ።
ውሃ ብቻ አልነበረም የተጠማው ፤ የተጠማው የሰው ፍቅር ጭምር ነበር ። ሳምራዊቷን ለማዳን “ውኃ አጠጭኝ” ብሎ ልቧን ለወንጌል እንድትሰጥ እንደጠየቃት ልጄ ልብህን ስጠኝ /ልብሽን ስጭኝ/ ለማለት ጌታም ተጠማሁ አለ ። ምሳ 23 ፥ 26 ፣ ዮሐ 4 ፥ 7 ።
አምላካችን የኛን ነፍስ መዳን ተጠማሁ አለ ፤ እኛ ለእርሱ የምናቀርብለት ምንድን ነው ? መራራ ሕይወት ወይስ በጎ ሕሊናና መልካም ሕይወት ? ዛሬም ወደሁላችን ዕዝነ ሕሊና ተጠማሁ ሲል ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ለዓለመ ዓለም እያልን ፍቅራችንንና እምነታችንን በመግለጥ ልንገዛለት ይገባል ።
6/ “ተፈጸመ” ዮሐ 19 ፥ 30 ።
ድኅነተ ዓለምን ለመፈጸም ወደዚህ ዓለም ለአገልግሎት የመጣው ጌታ በመስቀል ላይ ተፈጸመ አለ ። ትንቢተ ነቢያትን ፈጸመ ፣ በየጥቂቱ አድጎ ፣ በሠላሳ ዘመን በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ፣ በገዳም ጹሞ ፣ ሠላሳ ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተምሮ ፣ ሕማማተ መስቀልን ተቀብሎና ሰዎችን ክሶ ነፍሱ ከሥጋው የምትለይበት ጊዜ በደረሰ ጊዜ “ተፈጸመ” አለ ። በእርግጥም የአበው ተስፋ የተፈጸመው ፣ ድኅነተ ዓለምም የተከናወነው ፣ የነቢያትም ትንቢት የተፈጸመው ያን ጊዜ ነበርና «ተፈጸመ» አለ ።
7/ “አባ አመኀጽን ነፍስየ ውስተ እዴከ = አባት ሆይ! ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ሉቃ 23 ፥ 46 ።
የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት ለሞት ተሰጠ ። ነፍስን መልአከ ሞት ወስዶ በመከራ ያስቀምጣት ሥጋንም በመቃብር ይቀጣ ጀመር ። የሞት ፍርሃትም በሰዎች ላይ ነግሦ ነበር ። ዕብ 2 ፥ 14 ።
ሰውም የሥራውን ዋጋ ሞትን ዕለት ዕለት መቀበል ጀመረ ። ዘፍ 4 ፥ 8 ። 1ቆሮ 15 ፥ 56። ሮሜ 6 ፥ 23 ። ሮሜ 7 ፥ 13 ። ሆሴ 13 ፥ 14 ።
የሞትን ሥልጣን ሊሽር ፣ በአጋንንት እጅ ያሉትን ነፍሳት ነጻ ሊያወጣ የመጣው ጌታ ነፍሱን ከሱ የሚወስዳት ማንም እንደሌለ ሊያኖራትም ሆነ ሊያነሣት ሥልጣን እንዳለው ነግሮን ነበር ። ዮሐ 10 ፥ 18 ።
አሁን በመስቀል ላይ የሕይወት መንገድ በእርሱ ካሳ ስለ ተከፈተ ፥ የመጀመሪያውን አዳም ነፍስ የወሰዱ ፥ አሁን በሁለተኛው አዳም ነፍስ ላይ ሥልጣን እንደሌላቸው አበሰረን ። ይህም ማለት በክርስቶስ ያመኑ ምእመናን ነፍሳት በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ ፣ ጠላትም በነፍሳቸው ላይ ሥልጣን እንደሌለው ነገረን ። ከዚያ በኋላ “በታላቅ ድምጽ ጩሆ ነፍሱን ለአባቱ ሰጠ” ማቴ 27 ፥ 50 ።
መልእክት –
ክቡራን አንባብያን ይህ ዕለት ሁላችን የዳንበት ዕለት ነው ። በዚህ ዕለት መድኃኒታችን ነፍሱን ስለ እኛ በመስቀል ላይ ተወ ፤ ስለ እኛ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ። በሞቱም ተካስን ። የሕይወት በርም በሞቱ ተከፈተልን ። ሞት በእርሱ ሞት ተገደለ፤ እኛም በእርሱ መከራ ከበርን ።
ይህ ዕለት ክርስቶስ ኢየሱስ በገዛ ደሙ ቤተ ክርስቲያኑን የዋጀበት ዕለት ነው ። ይህ ዕለት ሞተ ነፍስ በክርስቶስ ሞት የተገደበት ዕለት ነው ። ይህ ዕለት የሰው ልጆች ነውር በክርስቶስ መስቀል የተጋረደበት ዕለት ነው ። ይህ ዕለት ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻው የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የእግዚአብሔር በግ የተሠዋበት ዕለት ነው ። ይህ ዕለት ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ሁኖ በመስቀል ላይ የዕርቅ አገልግሎትን ያከናወነበት ዕለት ነው ። የመሥዋዕቱ በግ እርሱ ራሱ ነው ። መሥዋዕት አሳራጊውም ካህኑ እርሱ ነው ፤ መሠዊያውም መስቀሉ ነው ። ጸሎቱ በዕዝነ አብ ተሰማለት ። ፍጥረትን ሁሉ እስከ ሞት በመታዘዝ ከሞት አዳነው ። ስለዚህ ሁላችንም ይህን ዕለት ዲብሎስ በመስቀል መመታቱን ፥ ድል መነሣቱን ፥ በሞት ላይ ሞት መፈረዱን ፥ የሰው ልጅ መዳኑን እያሰብን በደስታ እናከብረዋለን ። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ለጌታችን ለመድኃኔ ዓለም ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ይሁን ። አሜን ይሁን ።
ክብረ ቅዱሳን መድኃኔ ዓለም
የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሲያትል ዋሽንግተን ።

