ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ሲሆን ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ጥቂት ኪ.ሜ ራቅ ብሎ የሚገኝ ተራራ ነው ።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ የደብረ ዘይትን አቀበት እንደ ወጣ እናነብባለን (2ሳሙ 15 ፥ 30) ።
ዘሩባቤል ከሠራው ቤተ መቅደስ አደባባይ ደብረ ዘይት ሰባ አምስት ሜትር ገደማ ከፍ ብሎ ይገኛል ። ቤተ ፋጌና ቢታንያ የሚባሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ ። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆሣዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ገባ እናነብባለን ። ማር 1 ፥ 11 ።
ጌታችን የጸለየበት ጌቴሴማኒ የሚባለው ቦታም ከደብረ ዘይት ሥር ይገኛል ። ማቴ 26 ፥ 30-36 ።
ጌታችን ወደ ሰማይ ያረገው በደብረ ዘይት ላይ ነው ። (ሉቃ 24 ፥52 ። ሐዋ 1 ፥ 12)
መድኃኒታችን በደብረ ዘይት ተራራ በዓለም ፍጻሜ ዓለሙን ለማሳለፍ እንንደሚመጣ ተተንብዮአል ። (ዘካ 14 ፥ 4) መድኃኒታችንም ነገረ ምጽአቱን (ዳግም ምጽአቱን) በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በሰፊው አስተምሯል ። (ማር 13 ፥ 3) ።
በመሆኑም 5ኛው የዓቢይ ጾም ሰንበት የክርስቶስ ነገረ ምጽአት የሚታሰብበት ፥ የሚሰበክበት ፥ የሚዘመርበት፣ ዕለት ስለ ሆነ በደብረ ዘይት ተሰይሟል ። ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ነው በዚህ ዕለት የሚነበበው የወንጌል ክፍል (ማቴ 24 ፥ 1-36) ነው ።
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት በሄደበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነጸውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ሳለ ‹‹እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም›› አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስ የእርሱን ዳግም መምጣት አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ አስተማራቸው ።
የዓለምመጨረሻየኢየሱስክርስቶስመምጫምልክቶች
- ብዙዎች እኔ ክርስቶ ነኝ እያሉ በክርስቶ ስም ብዙዎችን ያስታሉ ። ማቴ 24 ፥4-5 ።
- የጦርነት ወሬ የዓለምን የዜና ጊዜ ያጣብባል በዓለም ዙሪያም ሰፊ ጦርነት ይደረጋል ፣ የጦርነትም ወሬ ፍጥረት ሁሉ ይሰማ ዘንድ ግድ ነው ፣ ክርስቲያኖች ግን ቢዚህ ጊዜ የክርስቶስን መምጣት ሊጠብቁ እንጂ ሊደነግጡ አይገባም (ማቴ 24 ፥ 6) ።
- ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል ሕዝብ እርስ በርሱ ይለያያል ። አንዱ መንግሥትም ሌላውን መንግሥት ሊያምነው አይችልም ። ማቴ 24 ፥ 7 ።
- ረኃብ ፥ ድርቅ ፥ ቸነፈር ፥ የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል ። እነዚህ ሁሉ የምጥ መጀመሪያ ናቸው ማቴ 24 ፥ 8 ።
- በዚያን ጊዜ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ለመከራ አልፈው ይሰጣሉ ይገደላሉ፣ ስለ ስሙም በአሕዛብ ሁሉ የተጠሉ ይሆናሉ ። ማቴ 24 ፥ 9 ።
- በዚያ ጊዜ ሰዎች ይሰናከላሉ ፣ እርስ በርሳቸው አሳልፈው ይሰጣጣሉ ፣ ይጣላሉ ። ማቴ 24 ፥ 10 ።
- ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት መምህራን ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ ዓመፅ ይበዛል የብዙዎችም ፍቅር ይቀዘቅዛል በዚያ ጊዜ እስከ መጨረሻው የጸና ብቻ ይድናል ፣ ትዕግሥትን ያዘወተረ ይድናል ። ማቴ 24 ፥11-13 ።
- ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊው ንጉሥ ፊት ያለምክንያት ፣ ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት ወንጌል በእስላም ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል ።ማቴ 24 ፥ 14 ።
- በዚያ ሰዓት በነቢዩ በዳንኤል እንደ ተባለው የጥፋት ሰው በጽድቅ ሥፍራ ፥ የርኩሰት ሰው በተቀደሰው ሥፍራ ቁሞ ይታያል ። ክፉ ዲያብሎስ በሐሳዊ መሲሕ (በአውሬው ሰው) አድሮ የተቀደሰውን ያረክሳል ፥ የታነጸውን ያፈርሳል ። ማቴ 24 ፥ 15 ።
- በዚያ ሰዓት በከተማ ያሉት ወደተራራዎች ይሸሻሉ በሰነገት ላይ ያለው ደግሞ ከምድር ቤት ያለውን ሊወስድ ሊወርድ አይችልም ፣ በእርሻ ላይ የተሰማራው ገበሬም ወደ ቤቱ ተመልሶ ልብሱን ሊወስድ ጊዜ አያገኝም ። በዚያ ወራት ኃጢአትን ለፀነሱ በደልንም ወልደው ለሚያሳድጉ ወዮታ አለባቸው ። ሁላችንም ሽሽታችን በክረምት ወይም በሰንበት እዳይሆን ማለትም ያለ ፍሬ ገና በቅጠል ሳለን ፣ እናርፍባታለን ባልናት በዕለተ ሰንበት እዳይሆን አጥብቀን ልንጸልይ ይገባል ። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ደግሞ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና ። ያ የፈተና ጊዜ እግዚአብሔርን ስለሚወዱ ምርጦቹ ባያጥር ኑሮ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በሕይወት ባልተገኘም ነበር ። ማቴ 24 ፥ 17-28 ።
- የበለስ ቅጠል መለምለም ማለት የጠፋችው እስራኤል መንግሥት መመሥረት የመድኃኒታችን መምጣት አሥራ አንደኛ ምልክት ነው ። ማቴ 24 ፥ 32 ።
ከዚያ በኋላ እኛ በማናውቀው ጊዜና ሰዓት እግዚአብሔር ወልድ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በአካላዊ መጠን) ከቅዱሳን መላእክት ጋር ከደመና ጋር ይመጣል ። ዓይን ሁሉ የወጉትም ያዩታሉ ፣ የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ የሚል የኃዘን ድምፅ ያሰማሉ ። ራዕ 1 ፥ 6-8 ።
ኃጥአንን በግራው ጻድቃንን በቀኙ ያቆማል ። ጥንቱን የሚያስነሣቸውም በሁለት አይነት ትንሣኤ ነው ። ኃጥአን ለፍርድ ጻድቃን ደግሞ ለሕይወት ትንሣኤ ይነሣሉ ። ዮሐ 5 ፥29 ። ማቴ 25 ፥ 31-46 ።
ኃጥአንን ይወቅሳል ጻድቃንን ያወድሳል ። ኃጥአንን እናንተ ርጉማን ከዚህ ወደ ዘለዓለም ፍርድ ሂዱ ብሎ ያሰናብታል ፣ ጻድቃንን ደግሞ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን የአባቴን መንግሥት ውረሱ ብሎ የእሱን መንግሥት ያወርሳቸዋል ።
ቅዱሳንሰዎችከተነሡበኋላእግዚአብሔርየሚሰጣቸውዋጋዎች
=የልቅሶና የመከራ ዘመን ያበቃላቸዋል ፣ በኃዘን የተያዘው የዚህ ዓለም ሥርዓት ይሻርላቸዋል ። ራእ 7 ፥ 15 -17 ። 21 ፥ 4 ።
=ባለመበስበስ ፥ በክብር ፥ በኃይል ፥ በመንፈሳዊ አካል ተነሥተው ሞትን ይዘብቱበታል ። 1ኛ ቆሮ 15 ፥ 42-45 ።
= የመጣውን ጌታ ለመቀበል ወደ ሰማይ በክብሩ ደመና ይነጠቃሉ ።1ተሰ 4 ፥ 16-17 ።
= ጌታቸውን ፊት ለፊት ያዩታል ።1ቆሮ 13 ፥ 12 ። ራእ 1 ፥ 7 ።ራእ 22 ፥ 4 ።
= የሚያዩትም ጌታቸውን ወደመምሰል ይለወጣሉ ።1ዮሐ 3 ፥ 2 ።
= በቅድስና በጽድቅ ሥራ አጊጠው ወደ በጉ ሰርግ ይሄዳሉ ። ራእ 19 ፥ 8-9 ።
= ዘላለማዊት መንግሥቱን ይወርሳሉ ። ማቴ 25 ፥ 34 ።
= በአዲሲቷ ኢየሩሳሌም በደስታ ይኖራሉ ። ራእ 21 ፥ 2-3 ።
= ሽልማታቸውን ይቀበላሉ ። ራእ 22 ፥ 12 ። ዳን 12 ፥ 3 ። 2ጢሞ 4 ፥ 2-3 ። 1ቆሮ 9 ፥ 25 ። 1ጴጥ 5 ፥ 4 ። ፊል 4 ፥ 1። 1ተሰ 2 ፥ 19 ።
= በእጅ ባልተሠራ ቤት ውስጥ ይኖራሉ ። 2ቆሮ 5 ፥ 1-2 ። ዮሐ 14 ፥ 2-3 ።
= ሁሉም አዲስ ይሆንላቸዋል ። ራእ 22 ፥ 5 ።
= በግንባራቸው አዳኝ የሆነው ስሙ ይጻፍባቸዋል ። ራእ 14 ፥ 1 ።ራእ 22 ፥ 4 ።
= እግዚአብሔር ለዘለዓለም አምላክና አባት ይሆንላቸዋል፣ እነርሱም ልጆቹ ይሆናሉ (ራዕ 21፤3-9)
= ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይሆንም ጌታ አምላክም በእነሱ ላይ ያበራላቸዋል ፣ የመብራት ብርሃን የፀይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም ፣ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ ። ራእ 22 ፥ 5 ።
መልእክት
‹‹በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል። አንድ ጊዜ ከተሠዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል›› (ዕብ 9 ፥26-28)
ሐዋርያው ከዚህ በላይ በተመለከትነው መልእክቱ መድኒታችን ለሁለት የተቀደሱ ዓላማዎች ወደ ዓለማችን ሁለት ታላላቅ ምጽአቶችን እንዳደረገና እንሚያደርግ ያስገነዝበናል ።
የመጀመሪያውምጽአቱ፡– ሥጋ በመልበስ ለሰው መሥዋዕት ሁኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትሕትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ በበረት በመወለድ በሥጋ ማርያም መጣ ። በሚሞት በሚሰደድ በሚደክም በሚበረታ በሚራብ በሚጠማ በሚዝል በሚወድቅ ባሕርየ ሰብእ (የሰው ባሕርይ) መጣ ። እንደ አንድ ኃጥእ ሞት እስኪፈረድበት ድረስ ፥ ራሱን ዝቅ አድርጎ መጣ ። ወንጌለ መንግሥቱን ሊሰብክልን ከሞት ወደ ሕይወት ሊያሻግረን በሥጋ ማርያም መጣ ። ከአይሁድ ስድብን ታገሠ ፣ ኃጥአንን በሽተኞችን ሊያድን በምድር ላይ ተመላለሰ ፣ ስለኛ ተገረፈ ፥ ተገፈፈ ፥ ተሰቀለ ፥ ሞተ ያውም መራራ ለሆነ የመስቀል ሞት ታዘዘ ፥ መርገማችንን ተሸከመ ሙቶ በሦስተኛው ቀን ተነሣ ፣ ወደ ሰማይ ዐረገ በየማነ አብ ተቀመጠ ፣ የመጀመሪው ምጽአቱ መከራን ለመቀበል እኛን ለማዳን ነበር ።
ዳግማዊምጽአቱ፡– በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍጹም ጌትነት በኃጥአን (የመጀመሪውን ምጽአቱን ባልተቀበሉት ላይ) ሞትን ሊፈርድ ዓይን ሁሉ እየተመለከተው በገሃድ ይመጣል ። ለምእመናን የሚሆነው ክብርም ያን ጊዜ ይገለጣል ፣ ኃጥእ ያፍራል ጻድቅ ይከብራል ፣ ሞት ይሻራል ሕይወት ይነግሣል ። ሰው (ጻድቅ) ሁለተኛ ላይሞት ይነሣል ፣ የምድር ሥርዓት ይሻራል ፣ ፍጥረት ሁሉ አንድ መንጋ ይሆናል ፣ በአንድ እረኛ ይሰማራል ።
ወገኖቼክርስቲያኖችሆይ ! የመድኃኒታችን ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን ? ለዘለዓለማዊ ሕይወት ወይስ ለዘለዓለም ሞት ።
ጌታ እግዚአብሔር ከሞት ያድነን ፣ በሞት የማይሻረውን ሕይወት ይስጠን ። አሜን ።
ምንጭ
ከሥርዐተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መጽሐፍ የተወሰደ።

