ቸር አገልጋይ ማነው ?
ማቴ 25 ፥ 14-30 ።
በዚህ ዕለት በቅዳሴ ሰዓት የተነበበው ቃለ ወንጌል እንዳመለከተን መድኃኒታችን የወንጌልን አደራ በምሳሌ እንዳስተማረ ተገንዝበናል። ትምህርቱም አንድ ባለጸጋ ሰው ነበር ። ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ባሰበ ጊዜ አገልጋዮቹን ጠርቶ ከመንገዱ እስኪመለስ ድረስ ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ለአንዱ አምስት ፣ ለሁለተኛው ሁለት ፣ ለሦስተኛው አንድ መክሊት (ታለንት) ሰጣቸው ። አምስት መክሊት የተቀበለው ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት መክሊት በማትረፍ አሥር መክሊት አደረገው ። ሁለት መክሊት የተቀበለው ወጥቶ ወርዶ እጥፍ አትርፎ አራት አደረገው ። ባለ አንዱ ግን ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በልቡ ውስጥ ስጋትን ፥ ጥርጥርን ፥ ፍርሃትን ፥ አለማመንን ስላነገሠ ስሠራበት ቢጠፋብኝስ? ቢሰርቁኝስ? ቢቀሙኝስ? እያለ በማሰብ እሠራለሁ ብየ ያለኝን ከማጣ ለምን ደብቄ አስቀምጬ በመቆየት ሲመጣ የሰጠኝን አልመልስም ብሎ መክሊቱን ቆፍሮ ቀበረው ። ጊዜው ሲደርስ ባለንብረቱ መጣና አገልጋዮቹን ይተሳሰባቸው ጀመር ።
አንደኛው አምስት የወሰደው መጣና ጌታዬ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር ይኸውና ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ ብሎ አሥር መክሊት ለጌታው ሰጠ ፣ ጌታውም ‹‹መልካም አደረግህ›› አንተ መልካም አገልጋይ (ገብር ኄር) በጥቂቱ ስለ ታመንህ በብዙ ላይ ስለምሾምህ ና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው ።
ሁለተኛው ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አራት መክሊት ብሎ እጥፍ ማትረፉን ገልጾ ለጌታው አስረከበ ፣ እንደ ባለ አምስቱ ‹‹መልካም አደረግህ ቸር አገልጋይ ነህ በጥቂቱ ስለታመንክ በብዙ ላይ እሾምሀለሁ›› ተባለ ።
ሦስተኛው መጣ ፣ ሰነፍ ቃሉም መራራ ነው ፥ ሰነፍ አካሉ ብቻ ሳሆን አእምሮውም ሰነፍ ነው ። ጌታው ገንዘቡን ሲጠይቀው ጌታ ሆይ ! አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ፣ ካልበተንክበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ፣ ስለዚህ ፈራሁህ ሂጄም መሬት ቆፍሬ መክሊትህን ጉድጓድ ውስጥ ቀበርኩት ፣ ገንዘብህ ይኸውልህ ውሰድ አለው ። ጌታውም ይህን ያክል ጨካኝ እንደ ሆንሁ ካወቅህ ንብረቴን ከነወለዱ ልትመልስ ይገባህ ነበር ፤ ገንዘቤን ልትሠራበት ሲገባህ ለምን ቀበርከው ብሎ መክሊቱን ወደ እርሱ ወስዶ ለባለ አምስቱ ጨምሩለት ላለው ይጨመርለታል ይትረፈረፍለትማል ፤ ለሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፣ ይህን የማይረባ አገልጋይ ግን ልቅሶ ፣ ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጽኑ የፍርድ ቦታ ውሰዱት አለ ይላል ፡፡ በምሳሌ የተሰጠው የመድኃኒታችን ትምህርት ። የትምህርቱም ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡፡
የንብረቱ ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ሦስቱ አገልጋዮች ልዩ ልዩ ጸጋ ተሰጥቶአቸው ያሉ ህዝበ ክርስቲያን ምሳሌዎች ናቸው ፤ ስጦታው በአኃዝ ሲታይ ልዩነት መኖሩ ፣ አንዱ ጸጋ ከሌላው የሚለይ መሆኑን ያሳያል ።
የአገልጋዮቹባሕርይ
1. የመጀመሪያውና የሁለተኛው አገልጋዮች መንፈስ ሁለቱም ሠርቶ ማግኘት እንደሚቻል የሚያምኑ ፣ ለጌታቸው ታማኞች ፣ በሥራ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር በማሰብ ጊዜአቸውን የማያጠፉ ናቸው ። ሁለተኛው አገልጋይም እንደ መጀመሪያው አገልጋይ ለምን አምስት አልተሰጠኝም ብሎ ያለኩርፊያ በተሰጠው የሚሠራ ነው ። ባለአምስቱ እምስት ሲያተርፍ ባለሁለቱም ሁለት በማትረፍ ተመሳሳይ ትጋት የታየባቸው አገልጋዮች ናቸው ። ዋጋቸውንም እኩል ነው ያገኙት ለሁለቱም የተሰጠው የክብር ስም አንድ ነው ገብርኄር (ቸር አገልጋይ) የሚል የገቡበትም የክብ ስፍራ አንድ ነው ያም ‹‹የጌታቸው ደስታ›. ነው? ሁለቱም በጥቂቱ የታመኑ ነበሩ ። ከሰጭው አንጻር ሲታይ የባለ አምስቱም እንደ ባለ ሁለቱ የባለ ሁለቱም እንደ ባለአምስቱ ጥቂት ነበር ፣ ሰው በተሰጠው ሳያንጎራጉር ፈጣሪውን ቢያገለግል ክብር ያገኛል ። ለሰው ልጅ የሚጠቅመው ችሎታውን ፣ ጸጋውን መቊጠር ሳይሆን በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ነው ። እነዚህ አገልጋዮች በእውነት በፍቅር በእምነት የሚያገለግሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ያመለክታሉ ።
2. የሦስተኛው አገልጋይ ባሕርይ፡– መልካም ጐኑ ስጦታው አነሰኝ አለማለቱ ነው ፣ በእርግጥ ስንፍናውን ስለሚያውቅ ይሆናል። ይህ ሰው ከሥራ ይልቅ በሥራ ጊዜ የሚፈጠረው ችግር ቀድሞ ይታየዋል ፣ (የሰነፍ አርቆ አስተዋይ) ሲያተርፍ ሳይሆን ሲከስር ብቻ ይታየዋል ፣ አንዱን ሁለት ሲያደርግ ሳይሆን ያንኑ ያለውን ሲቀማ ይታየዋል ፣ በጌታው ፊት እንደ ወንድሞቹ አይነቱን ትርፉን ይዞ ቀርቦ ሲሸለም ሳይሆን አይነታውም ጠፍቶበት ለጌታው የሚመልሰው ሲያጣ ይታዋል ። በመሆኑም ምንም መሥራት አልቻለም ፣ ኪሱንም አላምነው ብሎ መሬት ቆፍሮ ቀበረው ፤ በአጠቃለይ ባለማመን የተያዘ ሰው ነው ። ከጌታው ፊትም ሲቀርብ በጎ አገልጋዮቹ ያልተናገሩትን ነው የተናገረው ፣ ጨካኝ መሆንክን ስላወቅሁ ይጠፋብኛል ብዬ ብርህን አስቀምጨልሃለሁ ይኸውልህ ውሰድ ነው ያለው ፣ ሰነፍ የሚናገረውም አያምር ፣ ተቀምጦም መአት ከማውራት ዝም አይልም ።
ዛሬም ቢሆን ተቀምጠው መአት የሚያወሩ የእግዚአብሔርን ጸጋ የቀበሩ ባስተምርስ መናፍቅ ተከራክሮ ቢረታኝስ ? የማውቀውን እውነት ለመስበክ ስጀምር ቢያሳድዱኝስ ፣ ክፉዎችን ብዘልፍ ቢሳስሩኝስ ፣ በቤተ ክርስቲያን በሕዝብ በገበያ በልዩ ልዩ የሥራ ቦታዎች ያሉትን ኃጢአተኞች ብቃወምስ ፣ ጠላት ሆነው ቢነሡብኝስ? ለምን ዝም ብዬ ደመወዜን ሳልሠራ አልበላም ብለው የሚኖሩ ስንት አገልጋዮች አሉ ። የዚህ ሰው ችግሩ መክሊቱ አንድ መሆኑ ሳይሆን በዚያው አለመሥራቱ ነው ። የተሰጠውን ጸጋ እያንዳንዱ አምኖ በመቀበል ሊያገለግል ሁሉም ሊቀ ጳጳስ ፥ ጳጳስ ፥ ቄስ አይሆንም ፤ ሁሉም ግን በተሰጠው ቢያገለግል እውነተኞቹ ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ጳጳሳት ፣ ቀሳውስት የሚያገኙትን ዋጋ ያገኛል ።
ሁሉም ባለራእይ ፥ ወንጌላዊ ፥ ዘማሪ ፥ ፈዋሽ ሊሆን አይችልም ። ለእያንዳንዱ ልዩ ልዩ ጸጋ አለው ሁሉም በጸጋው ቢያገለግል እኩል ዋጋ ያገኛል ።
አንባቢሆይ በሦስቱ አገልጋዮች አምሳል የተጠቀሱት አገልጋዮች በቤተ ክርስቲያን የሚኖሩ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ያላቸው ክርስቲያኖችን የሚመለከቱ ናቸው ። በቤተክርስቲያን ባለ አምስት አገልጋዮች አሉ ፣ በወንጌል ፥ በእረኝነት ፥ በእርዳታ ፥ በልዩ ልዩ ጸጋ አንዱን ጌታ በቅንነት የሚያገለግሉ ሰዎች ምሳሌ ናቸው ። ባለ ሁለቱም እንዲሁ ልዩ ጸጋ ያለው በጸጋውም የሚያገለግል የጌታ አገልጋይ ምሳሌ ነው ። ባለ አንዱ የእግዚአብሔርን ጸጋ የተቀበለ ግን በጸጋው የማያገለግል ደካማ ሰው ነው ። ምናልባትም ይህ ሰው ራሷ ክርስቶስ በሆነላት ቤተ ክርስቲያን እግር ሁኖ ቢፈጠር የማይሄድ ፣ እጅም ቢሆን የማይዳስስ ፣ ዓይንም ቢሆን የማያይ ስነኩል አካል ነው ። በመሆኑም የክርስቶስ አካል ሁኖ ለመቀጠል አይችልም ።
ወንድሜ አንተስ ጸጋህ ምንድን ነው ? ጸጋህን ታውቀዋለህ? ታገለግልበትስ አለህ ? መቼም ክርስቲያን ሁሉ የክርስቶ አካል ነው ። የሥራ ድርሻ የሌለው የአካል ክፍል ደግሞ የለም ። አንተም ፥አንንቺም የክርስቶ አካል ናችሁ ። ስለዚህ አካሉ በመሆንህ/ሽ ደግሞ ጸጋ አለህ/አለሽ ። በመሆኑም እንደ ጻጋችን እናገልግል ፣ ጸጋውን እንቀበለው ። ወንጌልን በጊዜውም አለጊዜውም ፣ ሲሞላልንም ፣ ሲጎድለንም እንስበክ ። ሀብታሙ ይመጽውት ፣ መምህሩ ያስተምር ፣ ዘማሪው ይዘምር ፣ ጸሐፊው ይጻፍ ፣ ሁሉም በጸጋው ያገልግል ። አንድ መክሊት እንደ ተቀበለው ሰው ነገ እንዲህ ቢሆንስ እንደዚያ ቢፈጠርስ እያልን ባለማመን ዕለታትን ፥ ጊዜያትን አናባክን ፣በመጠራጠር ክፉን እንጂ በጎን ፣ ጥፋትን እንጂ ትርፍን ባለማሰብ ባለማመን ከአገልግሎት አንቆጠብ ። መከራም ቢመጣ ፣ ሞትም ቢመጣ ። በጎም ሆነ ክፉ ነገር ቢከሠት ወይም ባይከሠት ነገን የሚያውቅ ጌታ ብቻ ነው ። ሰው ይጠላኛል ፣ ክብሬ ይቀነሳል ፣ ስሜ ይጠፋል ፣ መናፍቅ ተከራክሮ ይረታኛል ፣ ነገ ችግር ይገጥመኛል ፣ እሠራለሁ ብዬ ከምሰናከልና ከምፈተን ለምን ዝም ብዬ አልቀመጥም አንበል ። ለሥራ ፥ ለአገልግሎት እንነሣ ። እንደ ሁለቱ ቅን አገልጋዮች ይሳካልናል ። ቃሉን በእዝነ ሰማእያን እንዝራው ይበቅልልናል ። ገበሬ እንኳ ‹‹ከወፍ አእላፍ አብላኝ›› ብሎ የተለቀመውን፥ የተበጠረውን፥ የተመረጠውን ፥ ዘር (እህሉን) በእምነት በእርሻ ላይ ዘርቶ ፥ በባዶ መሬት ላይ በትኖ ፣ ምን እንሚያመርት ተፈጥሮ ያስተምረናል ። ገበሬው የዘራሁት ባይበቅልስ ወፍ ቢበላውስ ብሎ ቢያስብ ኑሮ ባልዘራውም ፣ ምርትንም ባላፈሰ ነበር ።
ዛሬም እኛ ቅን አገልጋዮችን በእምነት እንምሰላቸው ፣ በፍቅር በእምነት እናገልግል ፣ ዋጋ እናገኛለን ። እንደ ሰነፉ አገልጋይ ኪሳራችንን ሳይሆን ትርፋችንን ፣ ሞታችንን ሳይሆን ሕይወታችንን ፣ ውርደታችንን ሳይሆን ክብራችንን እያሰብን ልናገለግልበት እንጂ ልንጨነቅበትና ልንቀብረው የተሰጠን ጸጋ የለምና ፤ የምናተርፍበትን እንጂ ኪሳራ የሚሆን ጸጋ አልተሰጠንምና ።
ተስማሚጥቅሶችችከመጽሐፍቅዱስ
‹‹ልጄ ሆይ አንተ በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው ጸጋ በርታ ፣ ብዙዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን…ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑት ሰዎች አደራ ስጥ›› 2ጢሞ 2 ፥1-3።
‹‹በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን ፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት ፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ ፣ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ. . . ለትሑታን ጸጋን ይሰጣል›› (1ጴጥ 5 ፥ 2-5) ።
‹‹መንፈስ ቅዱስ በእናንተ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ›› (የሐዋ 1 ፥ 6-9) ።
ጥቅስከያሬድመዝሙር
በግእዝ ‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ። ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውሁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ቡዙኅ እሠይመከ ባዕ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ›› (መዝሙር) በአማርኛ ‹‹በጎ ሥራ እየሠራ ጌታው የሚያገኘው ቸር እረኛ የታመነ አገልጋይ ማነው ? ባለው ሁሉ ላይ የሚሾመው ። ደግሞም እግዚአብሔር ቸር ታማኝ አገልግጋይ በጥቂቱ የታመንክ በብዙው እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ የሚለው››
በግእዝ ‹‹ኩኑ እንከ ከመ አግብርት ኄራን ወከመ አግብርተ ክርስቶስ ምእመናን እለ ይጸንሑ እግዚኦሙ እስከ የአቱ እምከብካብ ዘበሰማያት›› (ዓራራይ)
በአማርኛ ‹‹እንደ ቅን አገልጋዮች፣ እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች ምእመናን ሁኑ ጌታቸው ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ ተግተው እንደ ጠበቁት›› (ሉቃ 12 ጋር አነጻጽሩ) ፡፡
ግእዝ ‹‹ከመ ገብር ኄር ለእግዚአብሔር ተቀነዩ በኩሉ ጊዜ ወበኩሉ ሰዓት (አዝ) በኩሉ መአልት ወበኩሉ ሌሊት (አዝ) ጹሙ ወጸልዩ በንጹሕ ልብ ወአክብሩ ሰንበተ በጽድቅ (አዝ) ለቢጽክሙ ሠናየ ሐልዩ አብ ይሄሊ በእንቲአክሙ (አዝ) ወአግእዝዋ እም ኃጢአት ለነፍስክሙ››፡፡
አማርኛ ‹‹እንደ ቸሩ አገልጋይ ለእግዚአብሔር ተገዙ ፣ በሰዓቱ ሁሉ በጊዜው ሁሉ በመዓልት በሌሊት ፣ በንጹሕ ልብ ጹሙ ጸልዩ ፣ በእውነት ሰንበትን አክብሩ ። ለጓደኞቻችሁ በጎ አስቡ ፣ አብም ስለ እናንተ ያስባል ። ከኃጢአት ነፍሳችሁን ነጻ አውጧት።››
እኛም በቅን እንድናገለግል ጌታ ይርዳን ።
አሜን

