Skip to main content Scroll Top

ሆሣዕና በአርያም

በዚህ ዕለት መሲሕ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የተዘመረው መዝሙር ‹‹ሆሣዕና›› ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ሆሣዕና በአርያም›› የሚል ነበር ። በአጠቃለይ የዕለቱ ወንጌል ታሪክ እንደዚህ ነበር ፤ በኢየሩሌም አቅራቢያ ደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወደምትገኝ ቤተ ፋጌ ከምትባል ስፍራ ደረሱ (‹‹ኢየሩሌም›› ማለት ‹‹የሰላም ከተማ›› ማለት ነው ‹‹ቤተ ፋጌ›› ማለት ደግሞ ‹‹የበለስ ቤት›› ማት ነው ። በእኛ አባቶች ደግሞ ‹‹የተመሳቀለ ጎዳና›› ተብሎ ተተረጒሟአል ።) ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ‹‹በፊታችሁ ወዳለች መንደር ሂዱ የታሰረችን አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ ፣ ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ›› አላቸው ። ሐዋርያትም ፈትተው አመጡለት ። (የሐዋርያት አገልግሎት የታሰሩትን በወንጌል ቃል መፍታት ነው ። ሌቦች አጋንንት ያሰሯቸው ብዙ የኃጢአት እስረኞች አሉ ። ጌታ የታሰሩትን እንደሱ እንዲፈቱ ተማሪዎቹን አዟቸዋል ። በሐዋርት አገልግሎ የተፈቱትም የመሲሑ መገለጫዎች የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ይሆናሉ ።) በዘካርያስ የተነገረው የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ ጌታ በአህያይቱና በውርንጫዋ ላይ ይቀመጥ ዘንድ ሐዋርያት በአህያይቱ ጀርባ ላይ አነጠፉለት ። ዘካ 9 ፥ 9 ።

የዓለምን ኃጢአት የሚጋርድ አዲስ ልብስ ኢየሱስ ክርስቶ ነውና ልብስ ኀፍረትን እንደሚጋርድ ከባቴ አበሳ በደልን የምትጋርድ ነህ ሲሉ ነው ልብስ ያነጠፉለት ፤ ጌታም ተቀምጠባቸው ።

አህያ የተናቀች ናት ፣ ራሳቸውን ዝቅ ባደረጉ መንፈሳቸው ወደ ተሰበረ አምላክ እንሚመለከት ያስተምራል ኢሳ 53 ፥ 23 ። ማቴ 11 ፥ 29 ። መዝ 50 ፥ 17-18) ።

ሕዝቡም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ (እንኳን አንተ የተቀመጥክባት አህያ ትቢያ ሊነካት አይገባም ሲሉ ይላሉ አበው) ለንጉሥ የሚገባውን አክብሮት መግለጻቸው ነው። 2ነገሥ 9 ፥ 13። ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ ሆሣዕና በአርያም› በማለት መዝሙር ጀመሩ ።

ሆሣዕና ማለት አሁን አድን ማለት ነው ። ቃሉ በዳዊት መዝሙር « ኦ እግዚኦ አድኅን ሶ ፣ ኦ እግዚኦ ሠርህ ሶ » አቤቱ ፥ እባክህ ፥ አሁን አድን ፣ አቤቱ ፥ እባክህ ፥ አሁን አቅና ። ተብሎ ተጠቅሷል። መዝ 117 ፥ 25 ።

በአርያምየሚለው ቃል የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰማይን ያመለክታል ፣ በመሆኑም በሰማይ ያለ በሰማይ የሚኖር ሰማያዊ የሆንህ መድኃኒት ሆይ! አሁን አድን እያሉ ዘመሩ ። ጩኸታቸው በሁለት መንገድ ሊታይ ይችላል ።

የመጀመሪያው ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ አድን የሚል የሥጋ ጩኸት ሲሆን

ሁለተኛው ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ አድን ማለታቸው ነበር ። ሌላው በምስጋናቸው ውስጥ የተካተተው ቃል ‹‹የዳዊት ልጅ›› የሚል ሲሆን እርሱ መሲሑ መሆኑን ሕዝቡ እንደተገነዘቡ ያመለክታል ። (ማቴ 12 ፥ 23 ። 20 ፥ 30 ። 22 ፥ 41) ፡፡

‹‹የአባታችን የዳዊት መንግሥት›› ማለታቸው ለዳዊት የተሰጠው የተስፋ ቃል መፈጸሙን ያመለክታል ። የእስራኤል መንግሥት የእግዚአብሔር መንግሥት ነበረች ፤ የሰው ሁሉ ገዥ እግዚአብሔር ስለ ሆነ ፥ ከአዳም እስከ ሳሙኤል ሕዝቡን የሚያዝ የሚመራ በተስፋው የዘር ሐረግ ውስጥ ባለቤቱ እግዚአብሔር በመሆኑ ንጉሥ አልነበረም ። በሳሙኤል ጊዜ ግን ሕዝበ እስራኤል እንደ አሕዛብ ንጉሥ ፈለጉና ንጉሥ አንግሥልን ብለው ሳሙኤልን ጠየቁት ፣ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ቢያመልክት አንተን ሳይሆን እኔን ነውና የናቁት አንግሥላቸው አለው ። ሳሙኤልም ንጉሣችን እግዚአብሔር ስለ ሆነ ይቅርባችሁ ቢላቸው እንቢ ስላሉት አህያ ጠባቂውን ሳኦልን ሾመላቸው ። እግዚአብሔር እንዲገዛው ያልወደደን ሕዝብ የአህያ እረኛ ይገዛዋል ።

የሳኦልም መንግሥት ተሻረና እግዚአብሔር ሳኦል እያለ እንደ ፈቃዱ ሕዝቡን የሚመራበትን የእሱ መንግሥት የምትገለጥበትን ዳዊትን እንዲቀባ አደረገ ፤ የዳዊት መንግሥት የእግዚአብሔር መንግሥት ነበረች ፣ ለዳዊትም ከአብራክህ የሚከፈለው ልጅህ በዙፋንህ ላይ ይቀመጣል ብሎ ለጊዜው ለሰሎሞን ሲሆን ፍጻሜው ግን ጌታ ከእርሱ እንደሚወለድ ቃል ገብቶለት ነበር ። መበሥር መልአክ ቅዱስ ገብርኤልም ይህንኑ ተናግሯል ። (ሉቃ 1 ፥ 33) ።

ስለዚህ በስውር ይተላለፍ የነበረው የእግዚአብሔር መንግሥት በእግዚአብሔር ልጅ መወለድ ስለ ተገለጠች ፥ የአባታችን የዳዊት መንግሥት በማለት ዘመሩ  ። በዚህ ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም መሲሕ ሲገባ መላው ከተማ ‹‹ይህ ማነው?›› ብሎ ተናወጠ ፤ ሕዝቡም ‹‹ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው›› አሉ ። ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የንግድ ማዕከል የነበረውን ቤተ መቅደስ ከንግድና በንግድ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች አጸዳ ። «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፏል ፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ብሎ በግልጥ ተናገረ ። በቤተ መቅደስ የነበሩትን ዕውራን ዓይን አበራ ፣ ሽባዎችን አረታ ፣ ጎባጣዎችን አቀና ፣ ለምጻሞችን አነጻ ፤ ነገር ግን ቤተ መቅደሱን ያዙበት የነበሩት የጸሎት ቤቱን የወንገዴ ዋሻ ያደረጉት የአእምሮ ዕውራን ሳይበራላቸው ቀረ ። ስንኩል አመለካከታቸውም ሳይቀና ቀረ በመሆኑም ‹‹ሆሣዕና›› ብሎ የዘመረውን ሕዝብ አጣመው ዓርብ ‹‹ይሰቀል›› እንዲል አደረጉት ።

መድኃኒታችን በቤተመቅደስ እንዳለ በቤተ መቅደስ የነበሩ ሕፃናት መዘመር ጀመሩ ፣ ተማሪዎቹም አብረው ‹‹ሆሣዕና›› ሲሉ የካህናት አለቆች ዓይናቸው ደም ለበሰ ፣ ልባቸው ቁጣ ተሞላ ። እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን ? ዝም በሉ በላቸው አሉት ጌታን ። ጌታም እነሱ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይዘምራሉ ፣ በዚያውስ ላይ በዳዊት መዝሙር ‹‹ከሚጠቡት ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህልኝ ጠላት ዲያብሎስ ደስ አይበለው ብለህ›› ተብሎ የተነገረውን አታስተውሉምን  ? አላቸው ። መዝ 8 ፥ 2 ።

ባለአእምሮ ነን የሚሉት ልብ ሲታወር ፥ አንደበታቸው በሰይጣን ምክር ሲዘጋ ፣ የሕፃናት አንደበት ግን ምስጋናን ያዘንብ ነበር ።

አንባቢ ሆይ እንደ ሐዋርያት ታዛዥ ልብ ይኖርህ ዘንድ እግዚአብሔርም እስራትህን ይፈታልህ ዘንድ ጸልይ ፣ የተናቀችውን ፍጥረት እንዳልናቀ ፥ ምንም ኃጢአተኞች ብንሆን እንኳ በንስሐ ወደ እርሱ ብንቀርብ እንደሚቀበለን እወቅ ።

አንዳንድ ሰዎች ክብርን ይፈልጋሉ ፣ አያገኙትም ። ትልቅ መባል በሕዝብ ዘንድ መወደድ ይፈልጋሉ ፣ አይሆንላቸውም ። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ ? የክርስቶስ ማደሪዎች ስላልሆኑ ነው ። ነገር ግን የዛሬው ታሪክ የመሲሑ መቀመጫ የሆነች አህያ በምትረግጠው ምድር ላይ ጨርቅ ሲነጠፍላት ፥ ቅጠል ሲጎዘጎዝላት አየን ፣ በራሳቸው ለመክበር የሚፈልጉ ግን ክብርን አያገኙም ። የክብር ባለቤት ክርስቶስ ያደረባቸው መንፈሳቸው የተሰበረ ቅዱሳን ግን ክብር አላቸው ። እናከብራቸውማለን ፥ እርሱ የቅዱሳን ክብር ነውና። ምስጋን ለእርሱ ይሁን ። አሜን ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Leave a comment