Skip to main content Scroll Top

መፃጉዕ – በሰንበት ለበሽተኞች ዕረፍትን ሰጠ

PostFeaturedImage_KibreQidusan_Final (1)

በዚህ ዕለት ቅዱስ ያሬድ መድኃኒታችን በዕለተ ሰንበት የፈወሳቸውን ልዩ ልዩ ሕሙማን እያስታወሰ ሕይወትና መድኃኒት በመሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ ዳኑ ፥ ተፈወሱ እያለ ይዘምራል ። በመዝሙሩም ‹‹አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዓ ። የአዳም አምላክ ሰንበትን የፈጠረው (የሠራው) ለዕረፍተ ነው›› ስለዚህ በሰንበት ዕውራንን እዲያዩ ማድረጉ ፣ ጎበጣዎችን ቀንተው እንዲሄዱ በማድረግ ማሳረፉ ፣ በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የተያዙትን በመፈወስ ማሳረፉ ፣ እጃቸው የሰለለውን የሰለለ እጃቸውን ማቅናቱ እኮ የአዳም አምላክ ሰንበትን ለዕረፍት ስለ ፈጠራት ነው ። ይህንን በማድረግም ሰዓሬ ሰንበት ሊባል አይገባውም ። ‹‹እግዚአ ሰንበት – የሰንበት ጌታ›› ሊባል ይገባዋል እንጂ ብሎ አይሁድን እየወቀሰ መሲሕን እየቀደሰ ሰንበትን እየተረጎመ እና እያሞገሰ መድኃኒታችን በዕለተ ሰንበት ያደረጋቸውን ተአምራት እያስታወሰ ይዘምራል ። (አንባብያን  የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስትን በማንበብ የአድኅኖቱን ኃይል  ሊገልጡት ይችላሉ።)

አሁንም ሊቁ ያሬድ በዕለተ ሰንበት መፈጸማቸውን እየጠቀሰ የዘመረባቸውን ተአምቀጥለን እንጠቅሳለን

ጥቅስ በግ በሰንበት ፈወሰ ዱያነ ወከሠተ ዐዕይንተ ዕውራን፣ በሰንበት ፈድፋደ ኪያነ አፍቀረነ ፣ ሠርዐ  ለነ ሰንበተ ለዕረፍት ።

ትርጉም በሰንበት ድውያንነ ፈወሰ የዕውራንን ዐይኖች ገለጠ፣ በሰንበት አብዝቶ ወደደን ሰንበትንም ለዕረፍት ፈጠረልን ይላል ።

ቅዱስ ያሬድ በሰንበት ተፈወሱ ያላቸውን የዘመራላቸውን እንጠቅሳለን

1/ የመቶ አለቃውን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የፈወሰው በሰንበት ነው ብሎ ቅዱስ ያሬድ ዘምሯል ።

ጥቅስ በግዕዝ፡- ‹‹ይቤሎ መስፍን ለኢየሱስ በዕለተ ሰንበት ኢይደልወኒ ከመ አንተ ትባእ ታሕተ ጠፈረ ቤትየ ወባሕቱ አዝዝ በቃልከ ወየሐዩ ወልድየ››

ትርጉም ‹‹መቶ አለቃው ኢየሱስን በዕለተ ሰንበት ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም በቃልህ እዘዝ ልጄም ይድናል›› አለው ብሎ ልጁን በሰንበት እንደ ፈወሰው ተናገረ ። (አምላከ አዳም) ማቴ 8 ፥ 1-15 ።

ዕውራንንም ስለ ማብራቱ ሊቁ ‹‹ከልሐ ዕውር በውስተ ፍኖት ወገሠጽዎ እለ ይመርሕዎ ከመ ያርምም ወአዕበየ ከሊሐ እንዘ ይብል ተሣሃለኒ እግዚእየ ወልደ ዳዊት ርድአኒ›› ። ብሎ ዘመረ ።

ትርጉም ‹‹ዕውሩ በመንገድ ላይ አሰምቶ ጮኸ ፣ የሚመሩትም ዝም እንዲል ተቆጡት ፣ እርሱ ግን የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ (እርዳኝ) እያለ ጩኸትን አበዛ ›› ማለት ነው ። ማቴ 20 ፥ 29-10 ።

መፃጉዕንም በሰንበት ስለ መፈወሱ እዲህ ብሎ ዘመረ

ጥቅስ ‹‹አሕየዎ ኢየሱስ ለመፃጉዕ በዕለተ ሰንበት = ኢየሱስ በዕለተ ሰንበት መፃጉዕን ፈወሰው›› አለ (ሐፀቦሙ) ።

የዕውሩንም ዐይን በዕለተ ሰንበት እንዳበራለት ሲናገር እንዲህ አለ ።

ጥቅስ ‹‹በሰንበት ገብረ-ተአምረ ወረቀ ምድረ ወገብረ ፅቡረ እሕየወ ዕውረ በሰንበት››

ትርጉም፡- ‹‹በሰንበት ተአምርን አደረገ መሬት ላይ እንትፍ አለ ጭቃም አዘጋጀ ዕውሩንም በሰንበት አዳነ›› ብሎ ዘመረ ። ዮሐ 9 ፥ 9።

እጁ ሽባ ሁኖ የነበረውን ሰውም በሰንበት ፈወሰው ይላል ቅ.ያሬድ

ጥቅስ– ‹‹ሖረ ኃቤሁ ዘየብሰት እዴሁ ወፈወሶ በዕለተ ሰንበት ወይቤሎ ተሐድገ ለከ ኃጢአትከ ዑቅ ኢተአብስ››

ትርጉም– እጁ የሰለለችበት ሰው ወደ ኢየሱ ሄደ በሰንበት ፈወሰው ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ሁለተኛ እንዳትበድል እወቅ አለው » ብሎ ዘመረ ።

ስለ መፃጉዕም

ጥቅስ– ‹‹በሰንበት ተራከቦ ኢየሱስ ለመፃጉዕ ወይቤሎ ተንሥእ ንሣእ አራተከ ተኃድገ ለከ ኃጢትከ ዑቅ ኢተአብስ ወእምዝ ዘየአኪ ኢይርከብከ ተንሢኦ ነሥአ አራቶ አተወ ቤቶ ውእቱ መፃጉዕ›› (ዕዝል) (ማር 3 ፥ 1-6)

ትርጉም፡- ‹‹ኢየሱስ በሰንበት መፃጉዕን አገኘው ተነሥ አልጋህን ተሸከም ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል ሁለተኛ አትበድል ከዚህ የከፋ እንዳያገኝህ አለው ። መፃጉዕም ተነሥቶ አልጋውን ተሸክሞ ወደቤቱ ሄደ›› ብሎ ዘመረ ።

የቤት ጣራ በስተው ስለ አስገቡት በሽተኛም ሰው ዕለቱ ሰንበት ነበር ይላል ቅዱስ ያሬድ ሲዘምር ።ታሪኩ በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል ተመዝግቧል ። ማር 2 ፥ 3-12 ።

ጥቅስ፡- ‹‹ሰንበት አሜሃ አመ ይቤሎ ለመፃጉዕ ነሠቱ ጠፈረ ወአውረድዎ ኀበ ኢየሱ ርእዮ ሃይማኖቶ ወይቤሎ ለመፃጉዕ ተንሥእ ንሣእ አራተከ››

ትርጉም– ‹‹ኢየሱስ ሃይማኖቱን አይቶ የቤቱን ጠፈር አፍርሰው ወደ ኢየሱ ያወረዱትን መፃጉዕ ኃጢአትህ ተተወልህ ተነሣ ያለበት ቀን ሰንበት ነበር›› ብሎ ዘመረ ።

ሊቁ ያሬድ ተአምራቱን ሲያደንቅ እንዲህ ይላል ። ‹‹ጽቡር ያዐውር ሕያወ ዐይነ ውእቱሰ ወረቀ ምድረ ወገብረ ጽቡረ ወቀብዖ ዐዕይንቲሁ ለዘዕውሩ ተወልደ ወአሕየዎ››

ሲተረጎም ‹‹ጭቃ ሕያው ዐይንን ያሳውራል እርሱ (ጌታ) ግን መሬት ላይ እንትፍ አለ ጭቃንም አደረገ ዕውርም ሁኖ የተወለደውን ዐይኖቹን ቀባው አዳነውም›› አለ ።

የአይሁድን ክህደትና ጥያቄ እንደሚከተለው ዘምሮታል

ጥቅስ– … ወይቤልዎ አይሁድ በአይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት። …. ወይቤሎሙ ብውህ ሊተ እስብክ ግእዛነ ወእክሥት ዐዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ (መዝሙር)

ትርጉም– አይሁድም በምን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት ፣ ኢሱስም እኔ እሠራለሁ ፥ እናንተም በሥራዬ እመኑ ፣ እኔ የሰንበት ጌታ ነኝ …. ነጻነትን ለመስበክ ሥልጣን አለኝ የዕውራንን ዐይን ለመግለጥም አባቴ ላከኝ ። ብሎ ዘመረ ።

ከዚህም ሌላ በሰንበት ባሕር መገሠጹን ፣ ተአምራት ማድረጉን ፣ ማዕበል ሞገዱን ፥ ዓውሎ ነፋሱን መገሠጹን ፣ ተአምራት ማድረጉን ወዘተ አምልቶ አስፍቶ ዘምሯል ።

አንባቢ ሆይ፡- በሰንበት ለዕውራን ብርሃንን በመስጠት ፣ ለምጻሞችን በማንጻት ፣ ሽባዎችን በማርታት ዐሳረፋቸው ። ሰንበት ፥ የሰንበት ጌታ የሥራ ቀን ናት ። ሰንበት ሕመምተኞች ከደዌ የሚያርፉባት የመዳን ቀን ናት ። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ ሰንበትን ተረጎመ እጂ ሰንበትን አልሻረም ።

የክርስቶስ ተከታዮች የሆንን እኛም በሰንበት የታመሙትን ልንጎበኝ በወንጌል ቃል ልናጽናናቸው ፣ የታሰሩትን ልንጠይቅ ፣ ያዘኑትን ልናረጋጋ ይገባናል ። በሰንበት ቀን እንደ በሽተኞች ተኝቶ መዋል ሰንበትን ማክበር አይደለም ። በሰንበት ልንተጋ ይገባናል ። ዕረፍተ ነፍስን ፥ ዕረፍተ ሥጋን ለሰጠን ጌታ ክብር ምስጋና ይሁን ። አሜን ።***** ***** ***** *****

ሥርዐተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ

በመምህር ልዑለቃል አካሉ

Leave a comment