የዚህ ዕለት ስያሜ ‹‹ምኩራብ›› ይባላል ። መድኃኒታችን በምኩራበ አይሁድ ተገኝቶ ለታሰሩት ነጻነትን ለሞቱት ሕይወትን ለድሆች ወንጌልን ለተጠቁት ነጻነትን በፍርድ ላሉት ዓመተ-ምሕረትን ስለ ማስተማሩ በትምህርቱም ስለ መደነቁ ይሰበካል ፣ ይዘመራል ። ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ነው ። መድኃኒታችን በምኩራብ የሠራቸውን ነገሮች እያስታወሰ ስለ ዘመረ ዕለቱ ምኩራብ ተባለ ፣ ይህም የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሰንበት ነው ።
መዝሙር ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ።
ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ ።
በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ቅዱሳት መጻሕፍት
ቈላ 2 ፥ 16 እስከ ፍጻሜው
ያዕ 2 ፥ 14 እስከ ፍጻሜው ።
የሐዋ 10 ፥ 1-9 ።
ምስባክ እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዓኒ ፣
ትዕይርቶሙ ለዕለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻእክዋ በጾም ለነፍስየ ። መዝ 68 ፥ 9 ።
በአማርኛ የቤትህ ቅናት በልቶኛል ፣
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ላይ ወደቀ ፣
ነፍሴን በጾም አስመረርኳት (ቀጣኋት) ።
ትርጉም በቤተ መቅደስህ ገበያ አቁመውበት አይቼ የቀናሁት ቅንዓት እንደ እሳት አቃጠለኝ (ትዕይርቶሙ) አንተን በቤተ መቅደስህ ገበያ አድርገው እንደ ተገዳደሩህ ፣ እኔንም ገበያውን ብፈታባቸው ‹‹መኑ አብሐከ ትግበር ዘንተ-ይህን እንድታደርግ ማን ሥልጣን ሰጠህ›› አሉኝ ። ዮሐ 2 ፥ 8 ።
እንዲሁም አንተን መና ከደመና አውርደህ ብትመግባቸው ‹‹ምንት ጣዕሙ ለዝ መና›› «ወይእዜሰ የብሰት ነፍስነ ዘአልብነ ባዕድ ዘንሬኢ ዘእንበለ ዝ መና» ። «ይክልኑ እግዚአብሔር ሠሪዓ ማዕድ በገዳም ይዝብጥ ኰኲሐ ወያውኅዝ ማየ»። ብለው እንደ ተገዳደሩህ ። ዘኊ 11 ፥ 6 ። መዝ 77 ፥ 19 ።
እኔንም ‹‹የሰውን ልጅ ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም›› ብላቸው ‹‹እንበላው ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል›› ብለው ተፈታተኑኝ ። ዘጸ 16 ፥ 15 ። ዮሐ 6 ፥ 52 ።
ወቀጻዕክዋ ሰውነቴን በጾም አደከምኳት ጌታ አርባ ቀንና ሌሊት ጹሟል ። ዘጸ 34 ፥ 28-35 ። ማቴ 4 ፥ 2-6 ።
ወንጌል ዮሐ 2 ፥ 13 -25 ።
ቅዳሴ የጌታችን (ነአኩተከ)
ትምህርት የቤትህ ቅንዓት በላኝ ።
ስለ ቤተ መቅደስ ክብር እና ምንነት የመስከረም ወር 4ኛ ሰንበትን ትምህርት ይመልከቱ ። ምኩራብ ከቤተ መቅደስ በብዙ ይለያል ። ቤተ መቅደስ በብሉይ ኪዳን ከኢየሩሳሌም ውጭ አይሠራም ነበር ። ምኲራብ ግን በየትኛውም ቦታ መሥራት ይቻል ነበር ። የሚሠራበትም ዓላማ ለሕገ ኦሪት መማሪያ ቃለ እግዚአብሔር መንገሪያ ነበር ። በዚህ ዕለት ቅ/ያሬድ በመዝሙሩ ጌታ በምኩራብ ገብቶ ስለ ማስተማሩ ዘምሯል ።
የመዝሙሩ ዘር «ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሀረ ቃለ ሃይማኖት ፥ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት ፣ አነ ውእቱ እግዚአ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ፥ እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለእመሕያው ፣ ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ፣ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠጾሙ ያርምሙ ። አንከሩ ምህሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕስአ አፉሁ ።
ትርጉም ‹‹ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ የሃይማኖትን ቃል አስተማረ ከመሥዋዕት ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው ። የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባትዋ እኔ ነኝ አላቸው ። የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነውና ፣ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ ቤቴ የጸሎት ቤት ነው (ይባላል) ምኩራባቸው ገባ ፥ ዝም ይሉ ዘንድም ገሠጻቸው ። ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ (መወደድ) የነገሩን መወደድ የአፉን ለዛ አደነቁ›› ብሎ መድኃኒታችን በምኩራብ ማስተማሩን ቅዱስ ያሬድ ዘመረ ።
ወንጌላዊ ማቴዎስም ‹‹ኢየሱስ በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝቡም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር›› በማለት ከያሬድ ቀድሞ ተናገረ ። አይሁድ ፊት ለፊት ለታይታ ለከንቱ ውዳሴ በሚቀመጡበት ምኩራብ ፥ ክርስቶስ የነጻነትን ወንጌል እንደ ሰበከ ወንጌላዊ ሉቃስ ‹‹ኢየሱስም ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገባ ፥ ሊያነብም ተነሣ ። የነቢዩንም የኢሳያይስን መጽሐፍ ሰጡት ፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ ፦የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው ፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ ፥ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ፣ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ ፤ በምኩራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር ።
እርሱም ፦ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር ። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ፥ ከአፉ ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ ‹‹ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን ? ይሉ ነበር» ብሎ ጽፎልናል ። ሉቃ 4 ፥ 14-23 ።
በቅዳሴ ጊዜም የተነበበው ወንጌል ፥ በቤተ መቅደስ የሚፈጸመው የንግድ ሥራ እንዳሳዘነው ገልጦ በጅራፍ መንጋዎቹን ከነጋዴዎቻቸው ጋር ከቤተ መቅደስ እንዳስወጣና ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛውም ቀን እኔ እሠራዋለሁ (አስነሣዋለሁ)›› ብሎ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው እንደ ተናገረ ይተርካል ።
በትምህርቱ የተማረኩ ሰዎች ቢያምኑበትም የሰውን ልብ የሚያውቅ ጌታ የልባቸውን አይቶ እንዳልተቀበላቸውም ‹‹ኢይፈቅድ ይንግርዎ ግዕዞ ለሰብእ እስመ ለሊሁ የአምሮ ለሰብእ›› ስለ ሰው ማንነት ሊነግሩት አያሻውም እርሱ ራሱ ሰውን ያውቀዋልና» ብሎ ዮሐንስ እንደ ተናገረ ተጽፏል ።
ወዳጄ ሆይ ! ሕይወትህ ቤተ መቅደስ የኃጢአት ገበያ እንዳይሆን ተጠንቀቅ !

