Skip to main content Scroll Top

ትምህርተ ክርስትና

መግቢያ

ትምህርት አንድ

ትምህርተ ክርስትና ብሂል፥-ትምህርተ ክርስትና ማለት ክርስቲያኖች የሚያምኑት፣ የሚያስተምሩት የሚከተሉት መሠረታዊ የክርስትና ሃይማኖት ትምህርት ማለት ነው። በዚህ ተከታታይ ትምህርት በኒቅያ የተሰበሰቡትን የ318 አባቶች ትምህርት እና በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡትን የ 150 አባቶች ትምህርታዊ ውሳኔ መሠረት በማድረግ የክርስትናን ትምህርት እንማራለን።
የትምህርቱ ታሪካዊ መነሻ-ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ሕይወትን በሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሃይማኖት ትምህርቷ ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን በጉባኤ በመመለስ እውነተኛውንና የቀናውን የሃይማኖት ትምህርት ጠብቃ እና አስጠብቃ አቆይታናለች። በሃይማኖት ትምህርት ላይ የተነሡ ጥያቄዎችን ለመመለስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ጉባኤያት ተካሂደዋል። በእነዚህም ጉባኤዎች የተላለፉት ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የትምህርተ ሃይማኖት ውሳኔዎች ነበሩ። ዛሬም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ውሳኔዎች ትቀበላለች። ትምህርታቸውንም ታስተምራለች። ብዙ ጉባኤዎች ቢካሄዱም ሁሉም የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነው የዓለም ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የሚቀበላቸው ጉባኤያት ግን የተወሰኑት ናቸው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በዓለም ሁሉ ያለች ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውን ዋና ዋና ጉባኤዎች እና ውሳኔዎቻቸውን ከዚህ ቀጥሎ እናያለን
1) የኢየሩሳሌም ጉባኤ – 51 ዓ ም(እ,ኤ, አ)
ቦታው – ኢየሩሳሌም
ተሰብሳቢዎቹ – ሐዋርያት
የስብሰባው ምክንያት – ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና በመጡ እና ከአይሁድ እምነት ወደ ክርስትና በመጡ ሰዎች መካከል የባሕል፣ የአመጋገብ፣ የእምነት ስርዓት ልዩነት ስለተፈጠረ ችግሩን ለመፍታት ነበር። በወቅቱ ለነበሩት የወንጌል ሰባክያን ለእነ ጳውሎስ ለእነ ጴጥሮስና ለሌሎችም የሐሳብ መለያየትን ስላስከተለባቸው ውሳኔ ለመስጠት ጉባኤው አስፈላጊ ነበር። ይህም በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ጉባኤ ተብሎ ይታወቃል።
ታሪኩ – የሐዋ 15 ላይ ተጠቅሷል ሙሉውን ያንብቡት
ውሳኔው
1) ለጣኦት የተሰዋ እንዳይበላ
2) የታነቀ ወይም ታርዶ ደሙ ሳይፈስ የሞተ እንስሳ እንዳይበላ
3) ክርስቲያኖች ከዝሙት እንዲርቁ ያዝዛል፤ ያስተምራል፤
2) የኒቅያ ጉባኤ – 325 ዓ ም(እ,ኤ, አ)
ቦታው – በኒቅያ
ተሰብሳቢዎቹ – 318 ሊቃውንት (በእርግጥ የተሰበሰቡት ሊቃውንት ቁጥር ከዚያ በላይ ነው። ይህ በሐሳብ አንድ ሆነው የተገኙትን አባቶችን ቁጥር ነው የሚያመለክተው)
የስብሰባው ምክንያት – በ270 ዓ,ም በሊቢያ ተወልዶ በእስክንድርያ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ይማር የነበረው አርዮስ «ወልድ ፍጡር ነው» ብሎ ስላስተማረ ለእርሱ የክህደት ትምህርት እልባት ለመስጠት ነበር።መጀመሪያ በመምህሩ በተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ተመክሮ ስላልተመለሰ ተወገዘ፤ እለ እስክንድሮስ እና አኬላስ የሚባሉ የትምህርት ቤት ጓደኞች ነበሩት። ጴጥሮስ ከሞተ በኋላ አርዮስ ሐሳቤን ትቼዋለሁ ስላለ በ312 ዓ,ም አኪላስ በጴጥሮስ መንበር ሲቀመጥ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ሲሆን ከውግዘቱ ፈታው። አኪላስ በሥልጣን ብዙ ሳይቆይ ሞተ። እለ እስክንድሮስ ተተካ። እርሱም አርዮስን እንደ ጴጥሮስ አወገዘው። ይኸውም አንደበተ ርቱዕ የነበረውን ሊቀ ዲያቆን አትናቴዎስን ዋና ፀሐፊ በማድረግ በ22 ዓመቱ ሾመው። ከዚያ በኋላ በ319 ዓ,ም እና በ321 ዓ,ም አንድ መቶ ጳጳሳት በተገኙበት በእስክንድርያ አወገዘው።
ይሁን እንጂ አርዮስ ለንጉሠ ነገሥቱ በማይገባ ተወገዝኩ ብሎ አቤት ስላለ አለም አቀፍ ጉባኤ በኒቅያ ተደረገ። ጉዳዩ ከታየ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ አርዮስ በ318 ኤጲስ ቆጶሳት ስምምነት በ325 ዓ,ም ተወገዘ።

የጉባኤው ውሳኔ- «በአንድ አምላክ እናምናለን» ከሚለው ጀምሮ «በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን» እስከሚለው ድረስ ያለው የጸሎተ ሃይማኖት ክፍል የዚህ ጉባኤ ሃይማኖታዊ ውሳኔ ነበር። ይህንንም በሰፊው እንማረዋለን። ከዚህ በተጨማሪ የኒቅያ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያንን ስርዓትና ትምህርት የተመለከቱ 20 አንቀጽ ያላቸው የውሳኔ ሐሳቦችን አስተላልፎአል።

3) የቁስጥንጥንያ ጉባኤ – በ381 ዓ ም(እ,ኤ, አ)
ቦታው – ቁስጥንጥንያ
ተሰብሳቢዎቹ – 150 ኤጲስ ቆጶሳት
ንጉሡ – ታላቁ ቴዎዶስዮስ
የጉባኤው ዋና ዋና ምክንያቶች –
1, አቡሊናርዮስ የሚባል ሰው በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ መካከል መበላለጥ አለ ብሎ ስላስተማረ ነው « መንፈስ ቅዱስ ትልቅ ነው፣ ወልድ የበለጠ ትልቅ ነው፤ አብ ግን ከሁሉም በላይ ነው» ብሎ ስላስተማረ እና ጌታ ሰው ሲሆን «መለኮቱ የነፍስ እና የልቡናን ቦታ ተክቶለታል= ህየንተ ነፍስ ወልቡና ኮኖ መለኮቱ» ብሎ ስላስተማረ እርሱን ለማውገዝ ነበር።
2, አውሳብዮስ የሚባል ሰው «እግዚአብሔር አንድ አካል እንጂ ሦስት አካል የለውም» ብሎ ስላስተማረ ትምህርቱን ለማውገዝ ነበር። ይህ ሰው «በኦሪት እንደ አብ በዘመነ ሐዲስ እንደ ወልድ በበዓለ ሃምሳ እንደ መንፈስ ቅዱስ ስለወረደ ነው እንጂ አንድ አካል ነው» ብሎ ስላስተማረ እርሱንና ትምህርቱን ለመለየት ነበር።
3, መቅዶንዮስ «መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ ነው = ከአብና ከወልድ መንፈስ ቅዱስ ያንሳል» ብሎ አስተምሮ ነበርና እርሱንና ትምህርቱን አውግዞ ለመለየት ነው። ይህ ሰው የቁስጥንጥንያ ኤጲስ ቆጶስ ነበር።

ውሳኔው – በጸሎተ ሃይማኖት «በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን» ከሚለው ጀምሮ እስከመጨረሻው «የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን» እስከሚለው ድረስ ያለው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጉባኤ ሰባት አንቀጾች ያሉበት ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ወስኖአል።

4) የኤፌሶን ጉባኤ – በ431 ዓ ም(እ,ኤ, አ)
ቦታው – ኤፌሶን
ተሰብሳቢዎቹ – 200 ኤጲስ ቆጶሳት
ንጉሡ – ታናሹ ቴዎዶስዮስ (ንጉሡ በስብሰባው ላይ አልተገኘም። ተወካይ ግን ልኮ ነበር)
የስብሰባው መሪ – ትልቁ ቄርሎስ የእስክንድርያ ፓትርያርክ
የስብሰባው ዋና ዋና ምክንያት –
1, ንስጥሮስ « እመቤታችን የአምላክ እናት አትባልም የወለደችው ክርስቶስ የእግዚአብሔር አምሳያ የሆነ ሰው እንጅ አምላክን አልወለደችም» ብሎ አስተማረ፤ «ክርስቶስም ሁለት ጠባይ ሁለት ፈቃድ አለው» ብሎ ስለ አስተማረ እርሱን ለማውገዝ ተሰበሰቡ። ይሁን እንጅ እርሱ በጉባኤው ላይ አልተገኘም ነበር።
2, ቢላግዮስ የሚባል ሰው «የአዳም ኃጢአት ወደ ልጆቹ አልተላለፈም» ብሎ አስተምሮ ነበርና ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ሐሳቡ ስለሚጋጭ ማሰሪያ ለመስጠት ነበር።
ውሳኔዎቻቸው – እመቤታችን የአምላክ እናት መሆኗን ክርስቶስም አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን ወስነዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ የሆኑ ስምንት ነጥብ ያላቸው የውሳኔ ሐሳቦችን አስተላልፈዋል።

ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው ልዩ ልዩ ትምህርት እየመጣ መጽሐፍ ቅዱሳዊውንና የቀናውን ሃይማኖት እንዳይንድ ቤተ ክርስቲያን የወሰነቻቸው የሃይማኖት ትምህርቶች ለማንኛውም ክርስቲያን በጣም አስፈላጊዎች ናቸው። የኢ,ኦ,ተ,ቤ/ክ ለትምህርትና ለጸሎት የምትጠቀምባቸው በሐዋርያትና በተከታዮቻቸው ስም የሚታወቁ የሃይማኖት አቋም መግለጫዎች አሏት። ከእነዚህም መካከል የሐዋርያት አመክንዮ የሠለስቱ ምዕት አንቀጸ ሃይማኖት እና የቁስጥንጥንያ ጉባኤ አንቀጸ ሃይማኖት «ጸሎተ ሃይማኖት» ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ለጸሎተ ቅዳሴ ለዘወትር ጸሎት ለጥምቀተ ክርስትና ለጸሎተ ፍትሐት እና ለትምህርተ ክርስትና ትጠቀምባቸዋለች። በዚህም መሠረት የኒቅያ ጉባኤና የቁስጥንጥንያ ጉባኤ የወሰነውን የሃይማኖት ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋራ እያዛመድን እንማረዋለን።

ጸሎተ ሃይማኖት (በኒቅያ እና በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ አባቶች የወሰኑት የሃይማኖት አንቀጽ)

1) ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን።

2, ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን።

3, ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።

4, ሁሉ በእርሱ የሆነ፤ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የለም በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።

5, ስለ እኛ ስለ ሰው ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።

6, ሰው ሆኖ በጴንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፣ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ። በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ።

7, በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛ ሕያዋንን ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።

8, ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት የተናገረ።

9, ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቡአት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።

10, ኃጢአትን ለማስተስረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን። የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን።

ጸሎተ ሃይማኖት በመጽሐፍ ቅዱስ

ትምህርት ሁለት

1) ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን።
አንድ አምላክ

«እስራኤል ሆይ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ » ዘዳ 6፥4

«ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፤» ዘጸ 20፥3

«እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፤ በልብህም ያዝ፤» ዘዳ 4፥39

የሁሉ ፈጣሪ

«በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን ባሕርንም ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ » ዘጸ 20፥11

«ከማኅፀን የሠራህ፣ የሚበዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁሉን የፈጠርሁ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤» ኢሳ 44፥24

«ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።» መዝ 89፥ 2

«እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። » ዮሐ 4፥24
ሁሉን ቻይ ፈጣሪ

«ሰው በስውር ቢሸሽግ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርን የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር፤» ኤር 23፥24

«ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፤» 1ቆሮ 8፥6

«ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ፤» ኤፌ 4፥6

ለተጨማሪ ግንዛቤ «ሰማይና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን» የሚለው አንቀጽ እንዳለቀ
አብ ማን ነው? (ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ገጽ 25-33 ያንብቡ)

ትምህርት ሦስት

2, ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን።

ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ

«በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» ዮሐ1፥1

«እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ፤» መዝ 2፥7

«በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና፤» ዮሐ 3፥16

«መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ ተረከው፤» ዮሐ 1፥18

በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን

«እነርሱም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰቦችህም ትድናላችሁ አሉት፤» የሐዋ 16፥31

«ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፤» 1ቆሮ 8፥6

«ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብርሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፤» ፊል 3፥10-11

ትምህርት አራት

3, ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።

ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤

«ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው፤» ዮሐ 8፥ 12

«እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአልና፤» ቆላ 1፥15-17

«ብርሃንም ወደ ዓለም ስለመጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለወደዱ ፍርዱ ይህ ነው፦ ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይወጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይወጣል» ዮሐ 3፥19

«በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ» ዮሐ 9፥5

የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ

«እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ፤» መዝ 2፥7

በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል

«ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ ይህን ያህል ዘመን ከአንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታውቅምን? እኔ የምናገራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል፤» የሐ 14፥ 9-10

«እኔና አብ አንድ ነን፤» ዮሐ 10፥30

ትምህርት አምስት

4, ሁሉ በእርሱ የሆነ፤ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የለም በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።

«ሁሉ በእርሱ ሆነ፤ ከሆነውም አንዳችስ እንኳ ያለ እርሱ አልሆነም፤» ዮሐ 1፥3

«የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአልና፤» ቆላ 1፥15-17

ከትምህርት 2-5 ላለው ተጨማሪ መረጃ ኢየሱስ ማን ነው? ገጽ 65-83(ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ያንብቡ)

ትምህርት ስድስት

5, ስለ እኛ ስለ ሰው ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።

«እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤» ኢሳ 7፤14 ማቴ 1፥22

«የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንደዚህ ነበረ ፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች ።» ማቴ 1፥18

«መላኩም መልሶ እንዲህ አላት -መንፈስ ቅዱስ ባንች ላይ ይመጣል የልዑል ኃይል ይፀልልሻል ስለዚህ ደግሞ ካንች የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤» ሉቃ 1፥35

«ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤» ገላ 4፥4

«በመጀመሪያ ቃል ነበረ። ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ,,, ቃል ሥጋ ሆነ» ዮሐ 1፥ 1 እና ቁ, 14

«ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነ እና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው። ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ። ስለዚህ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ» 1ጢሞ 1፥15-16

«ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ» የሚለው እንዳለቀ
ነገረ ማርያም – ገጽ 273-287(ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ላይ ያንብቡ)

ትምህርት ሰባት

6, ሰው ሆኖ በጴንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፣ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ። በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ።

በነቢያት ትንቢት ፥-«በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ። ሕማማችንንም ተሸክሞአል። እኛ ግን እንደተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሰፈ እንደ ተቸገረም ቆጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቆሰለ። ስለ በደላችንም ደቀቀ። የደኅንነታችን ተግሳጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን» ኢሳ 53፥4-5

«ከስልሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢህ ይገደላል» ዳን 9፥26 ተብሎ ተነግሮ ነበር።

ሰው ሆኖ ጴንጤናዊ በጲላጦስ ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፣ ታመመ፣

«ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ» ማር 15፥15

«ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ ውኃ አንስቶ እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ። ሕዝቡም ሁሉ መልሰው ደሙ በእኛ እና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ። በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል
አሳልፎ ሰጠ» ማቴ 27፥ 24-26

«ሰቀሉትም ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ ,,, ከእርሱም ጋራ ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኝ አንዱን በግራ ሰቀሉ። መጽሐፍም ከአመጸኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ቃል ተፈጸመ» ማር 15፥24-27

ሞተ
«ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምጽ ጩኾ ነፍሱን ተወ» ማቴ 27፥50

ተቀበረ

«ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ገነዘው። ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው። በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ» ማቴ 27፥59-60

በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ።

«ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጉታላችሁ? ተነሥቶአል ከዚህ የለም» ሉቃ 24፥5

«ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ። በመካከላቸውም ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው። ይህንንም ብሎ እጆቹንም ጎኑንም አሳያቸው። ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው» ዮሐ 20፥19-20

«እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፤ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና» የሐዋ 2፥24

ስለኛ ስለ ሰዎች

«መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ ተቀበረም፤ መጽሐፍ እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአስራ ሁለቱ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስካሁን አሉ፤ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ። ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔም ደግሞ ታየኝ» 1ቆሮ 15፥3-9

«ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቁጣ እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋራ በልጁ ሞት ከታረቅን ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን። ይህም ብቻ አይደለም ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን» ሮሜ 5፥ 8-11

«የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል» 1ዮሐ 1፥ 7

ኢየሱስ ክርስቶስ ለክርስቲያኖች ሲል – ገጽ 105-114 (ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ)

ትምህርት ስምንት

7, በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤ ዳግመኛ ሕያዋንን ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።

በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤

«ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋራ ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ» ማር 16፥19

«ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘነድ እሄዳለሁና፥ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደኔም እወስዳችሁአለሁ» ዮሐ 14፥3

«እስከ ቢታንያ አወጣቸው እጆቹንም አንስቶ ባረካቸው ፤ሲባርካቸውም ከነእርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ»ሉቃ 24፥50

«ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ ደመናም ከአይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ እነሆ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ቁመው ደግሞም የገሊላ ሰዎች ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው» የሐዋ 1፥9-11
በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፤

«እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ፣ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም » ቈላ 3፥1 የሐዋ 7፥55-57

ሕያዋንና ሙታንን ይገዛል

«በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ» 2 ጢሞ4፥1

«የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና ያንጊዜም ለሁሉም እንደ ሥራው ያስረክበዋል»ማቴ 16፥27

«በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምጹን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይመጣሉና በዚህ አታድንቁ» ዮሐ 5፥29 ምዕ 12፥48

«ልጁንም አይቶ የሚያምን ሁሉ የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ» ዮሐ 6፥40

ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም

«በያዕቆብ ቤትም ለዘላለም ይነግሳል፤ ለመነግሥቱም ፍጻሜ የለውም»ሉቃ 1፥33

«ግዛቱ የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፣ »ዳን 7፥14

ትምህርት ዘጠኝ

8, ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሠረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት የተናገረ።

«ዳሩ ግን ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል» ዮሐ 15፥26 ምዕ 14፥16-17

«የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ፥ሁሉንም የሚችል የእግዚአብሔር መንፈስ ሕይወትን ሰጠኝ»ኢዮ 33፥4
ከአብና ከወልድ ጋር

«እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁን እንዲጠብቁ እያስማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጉአቸው» ማቴ 28፥19 1ዮሐ5፥7
በነቢያት አድሮ የተናገረ

«ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ፤» 2ጴጥ1፤21

«ለናንተም ስለ ሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር» 1ጴጥ 1፥11

«ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው» ማር 12፥36

«በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን» የሚለው እንዳለቀ
መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? ገጽ 209-217 ድረስ (ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ያንብቡ)

ትምህርት አስር

9, ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቡአት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።

« እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ በዚችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ። የገሀነም ደጆችም አይችሉአትም»ማቴ 16፥18

«ወንድምህም ቢበድልህ ሂደህ አንተና እሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው—ዳግመኛ አንደ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፥እነሱን ባይሰማ ለቤተክርስቲያን ንገራት ። ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት እንደ አረመኔ እና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።» ማቴ 18፥15-17

«ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችሁአል የመአዝኑም ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው—።»ኤፌ 2፥20 ኤፌ 3፥21

«በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ። አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት ፥አንድ ጥምቀት ፥ከሁሉም በላይ የሚሆን አንድ አምላክ—አለ» ኤፌ 4፤4

«ባሎች ሆይ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ» ኤፌ 5፥25

ማሳሰቢያ፦ የክለሳ ጥያቄዎችን ይመልሱ

ትምህርት አስራ አንድ

10, ኃጢአትን ለማስተስረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን። የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን።

ኃጢአትን ለማስተስረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን

«ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም» ዮሐ 3፥5

«ያመነ የተጠመቀ ይድናል» ማር 16፥16

«አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት» ኤፌ 4፥5

«እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው» ማቴ 28፥19

«አይሁድ ብንሆንም የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋወችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል» 1ቆሮ 12፥13

«እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኞም በአዲስ ሕይወት እንነሣለን። ከሞቱም ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋራ ተቀበርን» ሮሜ 6፥4

«ጴጥሮስም ንስኀ ግቡ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ። የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ» የሐ 2፥38

«ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ይሆን ዘንድ አሁን ያድነናል። የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጅ» 1ጴጥ 3፥21

«ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ሕይወት በሚሆን መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጅ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም» ቲቶ 3፥4-5

የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን

«በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎቹ ይነቃሉ። እኩሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት እኩሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና» ዳን 12፥2

«በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡም። ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን እኔ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም» ማቴ 22፥30-33

«በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምጹን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል። መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ» ዮሐ 5፥29

«የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው ሁሉ የሚፈርድበት አለው። እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል» ዮሐ 12፥48

«ልጁንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ» ዮሐ 6፥40

የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን

«ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን» 2ጴጥ 3፥13

«እውነት እውነት እላችኋለሁ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው» ሉቃ 18፥29-30

«እኛ አገራችን በሰማይ ነውና። በዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርቶስን እንጠብቃለን። እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደ ሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል» ፊል 3፥20-21

«አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና። ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» ራዕ 21፥1-2

ስለ ሚመጣው ሕይወት ቃለ ጽድቅ ኦርቶዶክሳዊ ገጽ 269-270 ይመልከቱ

ማሳሰቢያ፦ የክለሳ ጥያቄዎችን ይመልሱ

ለትምህርቱ ድጋፍ ሰጭ ንባብ ለሚፈልጉ

1, «ሰማይና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን» የሚለው አንቀጽ እንዳለቀ
አብ ማን ነው? (ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ገጽ 25-33 ያንብቡ)

2, «በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን» እንዳለቀ
ኢየሱስ ማን ነው? ገጽ 65-83( ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ያንብቡ)

3, «ስለ እኛ ስለ ሰዎች ከሰማያት ወረደ» እንዳለቀ
ኢየሱስ ክርስቶስ ለክርስቲያኖች ሲል – ገጽ 105-114 (ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ )

4, «ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ» የሚለው እንዳለቀ
ነገረ ማርያም – ገጽ 273-287( ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ላይ ያንብቡ)

5, «በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን» የሚለው እንዳለቀ
መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? ገጽ 209-217 ድረስ (ከቃለ ጽድቅ መጽሐፍ ያንብቡ)

ለትምህርቱ አስፈላጊ መረጃዎች
1, የተዘጋጀው «ትምህርተ ክርስትና» ማስታወሻ ጹሑፍ
2, ቃለ ጽድቅ ኦርቶዶክሳዊ መጽሐፍ (በመምህር ልዑለቃል አካሉ)
3, ኦዲዮ ሲዲ (ትምህርቱ የተቀረጸበት ሲዲ ለተልዕኮ ተማሪዎች)
4, የክለሳ ጥያቄዎችን መልሶ ለመምህሩ መስጠት

Comments (1)

ሞላ ደሳለኝ(ወልደ ዮሓንስ)
ሞላ ደሳለኝ(ወልደ ዮሓንስ)

በጣም በጣም ከጥማቴ ኧረክቻለሁ፡፡ ሁሌም የኦርቶዶክስ ልጅ ነኝ፡፡
ቃለ ሂወት ያሰማልን መንግስተሰማያትን ያውርስልን፡፡
ኢትዮጵያ ለዘዘላለም ትኑር

Comment to ሞላ ደሳለኝ(ወልደ ዮሓንስ) Cancel reply