Skip to main content Scroll Top

መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ

መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ፤
ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ትመራለች ፤ ቤተ ክርስቲያን ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንደ ተናገረው ከእግዚአብሔር የተወለደችው በርደተ መንፈስ ቅዱስ ነው ። ቤተ ክርስቲያን የተወለደችውም ያደገችውም በመንፈስ ቅዱስ ነው ። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ሕይወቷ መንፈስ ቅዱስ ነው ። የቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሆነ መንፈስ ቅዱስም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሥራዎችን ያከናውናል ለምሳሌ የሚከተሉትን እንመልከት ።
ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን ሁለተኛ ተወልዳበታለች፤
‹‹ኢየሱስም መለሰ እንዲህ ሲል፡- እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው›› (ዮሐ 3፤5-6) ተብሎ የተጻፈው መለኮታዊ ቃለ እግዚአብሔርም የሚያስገነዝበው ይህንኑ ነው፡፡
ቤተክርስቲያንን ለአምልኮተ እግዚአብሔር ያነሣሣል፤
መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያንን ለእውነተኛ አምልኮት እንደሚያነሣሣናቅዱ ርስቲያንም በመንፈስ ቅዱስ እንደምታመልክ መለኮታዊ ቃሉ ይጠቁመናል፡፡ ‹‹እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና›› ። ፊል 3 ፣ 3 ። ኤፌ 5 ፣ 18-19) ጋር ያነጻጽሩ።
ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ትሰብካለች መንፈስ ቅዱስም በቤተክርስቲያን (በምእመናን) ከምእመን ጋር ወንጌልን ይሰብካል፤
‹‹መንፈስም ፊልጶስን፡- ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተናገኝ አለው›› (የሐዋ 8 ፣ 23)
‹‹መንፈሱና ሙሽራይቱም፡- ና ይላሉ›› ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተጻፈ ። ራእ 22 ፥ 7 ።
መንፈሱ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ፥ ሙሽራይቱም የተባለችው ማኅበረ ምእመናን ናቸው ። በመሆኑም ከዚህ በላይ ያየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትም የሚጠቁሙት ይህንኑ ሐቅ ነው ።

መንፈስ ቅዱስ የቤተክርስቲያንን መሪዎች ይሾማል፤
‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ። ሐዋ 20 ፥ 28 ።
ዛሬም ነገም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ ባልመረጣቸው በሥጋዊ አሠራር በተመረጡ ሰዎች የምትመራ ቤተክርስቲያን ወደ እውነት ለመድረስ አትችልም ፣ መሪዎቿ በመንፈስ ቅዱስ አልተሾሙምና ስለዚህ ሹመት እንደ አባቶቻችን ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ሊሆን ይገባል ። የሐዋ 1 ፥25-26 ። 13 ፥ 2 ።
መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የወደፊቱን ክፉም ሆነ በጎ ነገር ይገልጥላታል፣ ይመራታል፣ ያስጠነቅቃታል፤
‹‹መንፈስ ግን በግልጥ፡- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞት ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያዳመጡ ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል ፤ በገዛ ሕሊናቸው እንደሚቃጠሉ ደንዝዘው ፥ እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ ፥ አምነውም እውነትን የሚያውቁ ከምስጋና ጋር ይቀበሉ ዘንድ እግዚአብሔር ከፈጠረው መብል እንዲርቁ ያዝዛሉ ። ››እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና ፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም ፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት ይየተቀደሰ ነውና ።1ጢሞ 4 ፥ 1-3 ።
መንፈስ ቅዱስ በግልጽ እንደ ተናገረ አሁን ካነበብነው ጥቅስ መረዳት ይቻላል ።
ውሳኔዋን መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን ያስተካክልላታል፤
‹‹ለጣዖት ከተሠዋ ፥ ከደምም ፥ ከታነቀም ፥ ከዝሙትም ፥ ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና ። ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ ጤና ይስጣችሁ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ ። የሐዋ 15 ፥ 28-29 ።
የሐዋየርያት ሁለተኛ ሲኖዶስ ውሳኔ የተጠናቀቀውና ውሳኔው የጸደቀው በመንፈስ ቅዱ አማካይነት መሆኑን አንባቢ ልብ ይበል ።
ከዚህ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስትሄድ ይባርካታል ፣ ለእግዚአብሔር አልገዛ ስትል ደግሞ ይገሥጻታል ። ይህንንም እውነት በእስያ ለነበሩት ሰባት አብያተ ክርስቲያናት መንፈስ ቅዱስ በላከው መልእክት ይታወቃል (የዮሐንስን ራእይ ም.2-3 ልብ ብለው ያንብቡ) በእያንዳንዱ መልእክት መዝጊያ ላይ ‹‹መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ›› የሚል ቃል ተጽፏል፡፡

መንፈስ ቅዱስ ለሕይወታችን ።
መንፈስ ቅዱስ ለሕይወታችን ሕይወት ነው ። ቀዳማዊ አዳምን ከፈጠረ በኋላ እግዚአብሔር ለሰዎች ሕይወትን የሰጠው እፍ በማለት በመለኮታዊ እስትንፋሱ ነበር ። ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው የሆነው በመንፈስ ቅዱ ሕይወትነት ነበር ። ዘፍ 2 ፥ 7 ።
ኢዮብም ‹‹የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ›› በማለት የተናረው ይህንኑ ከላይ የጠቀስነውን በጥንተ ፍጥረት መንፈስ ቅዱስ ለሰው ልጅ ሕይወትን ሰጭ መሆኑን ነበር ። ኢዮ 33 ፥ 4 ።
በበደል ምክንያት የሰው ልጅ ንጽሐ ጠባይዕ ካደፈ በኋላ እንደ ገና የተጎሳቆለው መንፈሳዊ ሕይወት የታደሰው የተቀደሰው በመንፈስ ቅዱስ ነው ። ከዚህ የሚከተሉት የሐዲስ ኪዳን ቃላትም ግልጽ የሚያደርጉት ይህንኑ እውነት ነው ።
ቅ/ጳውሎስ ንጽሐ ጠባይዓችን የታደሰው ሁለተኛ ከእግዚአብሔር የተወለድነው በመንፈስ ቅዱስ ነው ይለናል ። ቲቶ 3 ፥ 5 ።
ባለቤቱ ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለድን ሕይወት እንደሌለን ተናግሮ ሁለተኛ ተወልደን ሕይወትን የተላበስንበት መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ነው ይለናል ። ዮሐ 3 ፥ 3-8 ።
=ክርስቶስን በማመን ዳግም ተወልደንበታል ። ቲቶ 3፣5 ። ዮሐ 3 ፣ 3-8)
=በመንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ ቤተሰቦች ሆነናል ። ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎ ‹‹አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና ። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል» ። ብሏል ። 1ቆሮ 12 ፥ 13 ።
ቤተክርስቲያን (ምእመን) በመንፈስ ቅዱስ አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ አካል ቤተሰብ ናት ። የሰው ዘር ሁሉ በክርስቶ ካመነ ባሪያም ቢሆን ጨዋም ቢሆን ወንድም ቢሆን ሴት ትልቅም ትንሽም ቢሆን ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ አንድ አካል አንድ ቤተሰብ ነው ።

በሕይወታችን ይኖራል፤
አምነን የተቀበልነው የእግዚአብሔር መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ ይኖራል ። በውስጣችን መንፈሰ እግዚአብሔር ለመኖሩ ሐዋርያው የሚከተለውን እንዲህ በማለት ጽፏል ። ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን ››1ቆሮ 2 ፥ 12 ። 3 ፥ 16 ።
ሐዋርያው ቅ. ጳውሎስ ሁላችን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች ነንና ሰውነታችንን በቅድስና ልንጠብቀው እንደሚገባ ያስረዳ ሲሆን ፣ በተጨማሪም የእግዚአብሔር መንፈስ የሚኖርበት አካላችንን በኃጢአት በጣዖት ብናረክሰው እግዚአብሔር እኛነታችንን በመዓት እንደሚያፈርሰው በቊ.16 የማስጠንቀቂያ ቃል ጽፎልናል ።
ክርስቲያን ወንድሜ እኅቴ ሆይ ! የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነውን አካላችንን ከጣዖት ፥ ከዝሙት ፥ ከርኩሰት ፥ ከስካር ፥ ከመዳራት ጠብቀነዋልን ? በውስጣችን ያደረውን መንፈስ ቅዱስን አላስመረርነውምን ? እርሱ ቅዱስ መንፈስ ነውና ፤ እኛ ግን ከንቱና ርኩስ ሥራ ከሠራን መንፈስ ቅዱስ አብሮን ሊኖር አይችልም መቅደሱን አሳድፈነዋል ከማሳደፍም አልፎ አፍርሰነዋልና ።
ለመዳን ሕይወታችን ታትሞበታል መንፈስ ቅዱስ
የሕይወታችን ማኅተም ነው ፤

ማኅተም የሚባለው ብዙ ነገሮችን ያመለክታል ። ለምሳሌ የሚከተሉትን እንመልከት ። አለመርሳት አለመዘንጋትን እንደ ማስታወሻ ጽፎ ቈጥሮ ማኖርን ያመለክታል ። ኢዮብ ኃጢአቱም ሆነ ጽድቁ በእግዚአብሔር ፊት የማይዘነጋ መሆኑን ሲገልጽ ማኅተም የሚለውን ቃል ተጠቅሟል ። ኢዮ 14 ፣ 17 ።
ሌላው ደግሞ ህልውና ያለውን አንድን ነገር መጋረድን ወይም ማሳለፍን ያመለክታል ። ኢዮብ 9 ፣ 7 ።
ራእይን ምሥጢረ እግዚአብሔርን ያለ ጊዜው ያለ ወቅቱ እንዳይገለጥ መሸሸግን ያመለክታል ። ዳን 8 ፥ 26 ። ራእ 10 ፥ 4። ማኅተም ስም የተጻፈበት ዓርማ መለያ ያለው ሊሆን ይችላል ፥ በጣት ቀለበትም ሊከናወን ይችል እንደ ነበር ተጽፏል ። ዳን 6 ፥ 17 ።
በአጠቃለይ ማኅተም የታተመ ወረቀትን ሥልጣንን የመስጠት ። ባለቤትነትን ሊያረጋግጥ የሚችል ። ምሥጢራዊ ምልክት ነው ። ዘፍ 41 ፥ 42 ። ኤር 32 ፥ 10-14 ።
በአንድ ባለሥልጣን ማኅም የታተመ ወረቀት የማይለወጥ ውሳኔን የያዘ መሆኑ ግልጽ ነው ። በመሆኑም በንጉሥ ወይም በሌላ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ማኅተም የታተመ ነገር አይለወጥም ። አስ 8 ፥ 8 ። ዳን 6 ፥ 17 ። ማቴ 27 ፥ 66 ።
ከላይ እንደ ተመለከተው በራእይና በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ለተጻፉ የትንቢት ቃላትም ማኅተም የታተመባቸው ምሥጢር በመሆናቸውና በጊዜው ስለሚገለጡ ነው ። ኢሳ 29 ፥ 11 ። ዳን 12 ፥ 9 ። ራእ 5 ፥ 9-10 ። ራእ 22 ፥ 10 ። (የመጽሐፍ ቅ. መዝገበ ቃላት) ።
ከላይ በተመለከትነው ማብራሪ ማኅተም ምን እንደ ሆነ በመጠኑ ከተገነዘብን መንፈስ ቅዱስ ማኅተማችን ነው ። በመንፈስ ቅዱስ ማኅተምነት ታትመናል ስንል ምን ማለታችን ነው ። ንብረትነታችን የእግዚአብሔር ነው ። ማንኛውም በእግዚአብሔር ልጅ አምኖ የተጠመቀ ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የተሰጠው ክርስቲያን የእግዚአብሔር ነው ማለታችን ነው ። በመንፈስ ቅዱስ ስለ መታተማችን የሚያወሱት የመጽሐፍ ቅዱ ክፍሎች ። 2ቆሮ 1 ፥ 22 ። ኤፌ 1 ፥ 13 ። ኤፌ 4 ፥ 30 ። እና ሌሎም ናቸው ።
‹‹ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ›› ይላል ። ኤፌ 4 ፥ 30 ።
አንባቢ ሆይ የታተምክበትን መንፈስ አታሳዝነው ከማኅበረ አጋንንት የተለየህበት ነጻነትህን የተጎናጸፍክበት ሞትን ድል የምትነሣበት ፣ ዓለምን የምታሸንፍበት የእግዚአብሔርነትህ የሚረጋገጥበት መለያህ ክብርህ እርሱ ነውና አታሳዝነው ። እርሱ የእምነት መንፈስ ስለ ሆነ ከመናፍቃን ጋር ስትሄድ ያዝናል ፥ እርሱ የቅድስና መንፈስ ነውና ከርኩሳን ከዘማዎች ጋር ስታብር ዕድል ፈንታህን ከዘማዎች ጋር ስታደርግ ያዝናል ፥ እርሱ ጻድቅ ነውና ከክፉዎች ጋር በክፋት አንድ ስትሆን ያዝናል ። እርሱ አዳኝ ፈዋሽ መንፈስ ነውና ወደ ጠንቋይ ስትሄድ ተስፋህ ፈጣሪ ሳይን ፍጡር ሲሆን ያዝናልና ፣ በእነዚህና ተዘርዝረው በማያልቁ ሌሎችም ኃጣውዕ አታሳዝነው ። (የቀረውን እግዚአብሔር ሲፈቅድ በአዲሱ መጽሐፍ እናነበዋለን)፡፡

በጸጋው ባዶነታችንን የሚሞላ የጸጋ መንፈስ በመሆኑ በጸጋው ያስጌጠናል፤
ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትም የሚያንጸባርቁት ይህንኑ ነው ።
‹‹የጸጋው ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው ፤አግልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው ፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው ። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል ። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና ፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል ፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት ፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ ፥ ለአንዱም ትንቢት መናገር ፣ ለአንዱም መናፍስትን መለየት ፣ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር ፣ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል›› 1ቆሮ 12 ፥ 6-11 ።
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች ቤተ ክርስቲያን ተቀብላ ራሷን ያስጌጠች መሆኗን ልብ እንበል ። ቤተ ክርስቲያን ማለት በአዳም በደል ጸጋው ከተነሣው በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በረከት የተቀበለች የሰው ልጆች ኅብረት ማለት ናት። በመሆኑም መንፈሰ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን አከበራት ከፍ ከፍ አደረጋት አገነናት ።
እንዴት መጸለይ እንዳለብን ስለማናውቅ በውስጣችን ሁኖ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንድንጸልይ ያደርጋል ። ሮሜ 8 ፥ 26 ።
እርሱ አባ አባት ብለን ወደ እግዚአብሔር የምንጮህበት ቅዱስ መንፈስ (መንፈሰ ልደት) የልጅነት መንፈስ ነውና ። (ገላ 4 ፥ 6) ።
ሕይወታችንን ወደ እውነት ይመራል ። ዮሐ 16 ፥ 13 ።
ቅድመ ርደተ መንፈስ ቅዱስ የሰው ልጆች ጸሎት ‹‹ወመንፈስከ ቅዱስ ይምርሐኒ በምድረ ጽድቅ›› ሲተረጎም ‹‹ቅዱስ መንፈስህ ወደ ምድረ ጽድቅ ይምራኝ›› የሚለው ነበር ። (መዝ 141 ፥ 10)
ዛሬ ግን ወደ እውነት የሚመራን መንፈስ ተገለጠ በመሆኑም ሁላችን በዚህ መንፈስ ምሪት ልንጓዝ ያስፈለጋል ። ‹‹በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው›› ተብሎ ተጽፎአልና ። ሮሜ 8 ፥ 14 ።
የሕይወታችን መምህር ነው፤
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶ መንፈስ ቅዱ የሕይወታችን መምህር መሆኑን ሲገልጽልን ‹‹አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነ አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል ። እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል›› ብሏል ። ዮሐ 14 ፥ 26 ።
ከዚያ አስቀድሞም ‹‹መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩት የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና›› በማለት ስለ ወንጌል ስለ ክርስቶ በባለ ሥልጣናት ፊት ስለሚናገሩት ነገር እንደሚገልጽላቸው ተናግሮ ነበር ። ሉቃ 12 ፥ 12 ።
ቅ/ጳውሎም ስለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ‹‹እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም›› በማለት ተናግሮአል ።1ቆሮ 2 ፥ 12 ።
ቤተ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ጌትነት የምትመሰክረውም ከመንፈስ ቅዱስ ተምራ መሆኑን ‹‹ስለዚህ ማንም በእግዚአብሔር መንፈስ ሲናገር፡- ኢየሱስ የተረገመ ነው የሚል እንደሌለ በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ›› በማለት ነበር ሐዋርያው ቅ ጳውሎ የገለጸው ።1ቆሮ 12 ፥3 ።
እንዲሁም ቅ/ዮሐንስ ስለ ቤተክርስቲያን ዕውቀት ሲናገር ‹‹እናንተም ከቅዱሱ ቅባት (መንፈስ ቅዱስ) ተቀብላችኋል ፣ ሁሉንም ታውቃላችሁ›› ብሏል ። 1ዮሐ 2 ፥ 20-21።
‹‹እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል ፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም ፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ‹‹መንፈስ ቅዱስ) ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ ፥ በእርሱ ኑሩ ›› በማለት መንፈስ ቅዱስ የሕይወታችን መምህር መሆኑን ገልጾልናል ። 1ዮሐ 2 ፥ 26 ።
ስለ ክርስቶስ የምንመሰክርበትን ኃይልና ጥበብ ይሰጠናል፤
‹‹ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ። የሐዋ 1 ፥ 8 ።

ሕይወታችንን በፍቅር ያረሰርሳል፤
‹‹በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም›› ተብሎ እንደተጻፈ ። ሮሜ 5 ፥ 5 ። ዮሐ 4 ፥ 14 ። 7 ፥ 38 ።

ሰውነታችንና ውስጣዊ ሕይወታችንን በቃለ እግዚአብሔር በጸሎት የሚያጸና መንፈስ ነው ።
‹‹በመንፈሱ በውጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ ። ኤፌ 3 ፥ 16 ።
የክርስቲያን ሕይወት መንፈሳዊ ፍሬ እንዲያፈራ ያደርጋል፤
‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር ፥ ደስታ ፥ ሰላም ፥ ትዕግሥጥ ፥ ቸርነት ፥ በጎነት ፥ እምነት ፥ የውሃት ፥ ራስን መግዛት ነው ። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም›› ። ተብሎ የተነገረውም መለኮታዊ ቃል የሚገልጸው ይህንኑ ነው ። ገላ 5 ፥ 22-23 ።
ወንድሜ አንባቢ ሆይ መንፈስ ቅዱስ ከዚህ ላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በአንተ ሕይወትስ አከናውኖአልን ?
ክርስቲያኑን ከሞት ለዘላለም ሕይወት ያስነሣዋል፤

‹‹ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር ፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል›› ተብሎ እንደ ተነገረ ። ሮሜ 8 ፥ 11 ።

የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ በልዩ ልዩ ነገሮች ተመስሏል ነገር ግን የተመሰለባቸው ነገሮች መንፈስ ቅዱስ ናቸው ማለት አይደለም ። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የተመሰለባቸው ምሳሌዎች ናቸው ። ከተመሰለባቸው ምሳሌዎች ጥቂቱን ብንጠቅስ፡-
በነፋስ ይመሰላል
መንፈስ ቅዱስ በነፋስ መመሰሉ ነፋስ ነው ማለት አይደለም ነገር ግን ጌታችን እንደ መሰለው ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል ድምፁም ይሰማል ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንደሚሄድ እንደማይታወቅ ሁሉ ፥ ጸጋ መንፈስ ቅዱስም ሆነ ራሱ መንፈሰ እግዚአብሔር ሰው ላይ ሲያድር አይታይም አይታወቅም ፥ ነፋስ ዛፍን ሲያንቀሳቅስ ባሕርን ሲያናውጽ ይታያል እንጂ መልኩ እንዳይታይ መንፈስ ቅዱስም ምሥጢር ሲገልጽ ቋንቋን ሲያናግር ይታወቃል እንጂ በሰዎች ሲያድር አይታወቅምና ። ነፋስ (አየር) ለሕይወት አስፈላጊ እንደ ሆነ ሁሉ ያለ አየርም ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ በሕይወት መኖር እንደማይችል እንደዚሁ ሁሉ ያለ መንፈስ ቅዱስም ክርስቲያናዊ ሕይወት የለምና ። ‹‹እስመ ነፋስ ይስሕቦ ለቁመተ ሥጋነ›› ነፋስ ሥጋዊ አካላችንን ያሳድጋል ተብሎ እንደ ተጻፈ ፣ መንፈስ ቅዱም ቁመተ ነፍሳችንን ያሳድጋልና ‹‹እስመ ነፋስ ያገዝፎ ለፍሬ›› ነፋስ ፍሬን ያሳድጋል ። ‹‹እስመ ነፋስ ነፍሳቲሆሙ ለማያት-ነፋስ የውኃዎች ሕይወት ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ ፣ በመንፈሳዊ ፍሬ የብስ (ደረቅ) እኛነታችንን የሚያስጌጥ ፥ ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስን የሚያድል ስለ ሆነ በነፋስ ይመሰላል ለማስረጃ ‹‹ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል ድምፁንም ትሰማለህ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እዲሄድ አታውቅም ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው›› ብሎ መድኃኒታችን ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ልብ ይበሉ ። ዮሐ 3 ፥ 8 ።
በዓውሎ ነፋስም ይመሰላል ። ሉቃስ ስለ ርደተ መንፈስ ቅዱስ ሲጽፍ እንደ ገለጸልን ፣ ፍሬን ከገለባ ስለሚለይ በነፋስ በዓውሎ ነፋስ ይመሰላል ።
በእሳት ይመሰላል፤
‹‹ወውእቱ ያጠምቀክሙ በመንፈስ ቅዱስ ወበእሳት = እርሱ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ያጠምቃችኋል›› የሚለውን ቃለ ወንጌል ሲተረጉሙ፡- ስለ መንፈስ ቅዱስ በእሳት መመሰል እንደ መረጃ የሚጠቅሱትንና የሚያዛምዱበትን ነጥብ ከአበው ትርጓሜ ወንጌል የተገለጸውን ሙሉ ሐተታ ብንመለከት ምሳሌው ስለሚገባን ሐተታውን እንመልከት ። ‹‹መንፈስ ቅዱስን እሳት አለው ። እሳት ምሉዕ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና ፣ እሳት በምልዓት ሳለ ቡላዱን ካልመቱት አይገለጽም መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጂ አድሮ ሳለ አይታወቅምና ፣ እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያስፋፉታል መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው ኋላ በሥራ ያስፋፉታልና ፣ እሳት ጣዕምን መዓዛን ያመጣል መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን መዓዛ ጸጋን ያመጣልና እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል ። ከመጠን ወጥቶ የሞቁት እንደ ሆነ ግን ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደ ሆነ ሕይወት ይሆናል ። በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደ ሆነ ግን ይቀስፋልና ፣ «እሳት በላዒ ለዓማፅያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ = ትርጉሙ ስሙን ለሚክዱ ዓመፀኞች ሰዎች የሚባላ እሳት ነው ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው» እንዲል (ቅዳሴ ማርያም) ። እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቃጥላል መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡለትን መሥዋዕት ይቀበላልና ። እሳት ውኃ ገደል ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል ፣ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋልና ። እሳት ዱር ይገልጣል ፣ መንፈስ ቅዱም ምሥጢር ይገልጣልና ። እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ያመቻል ፣መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰውነትም ለገድል ለትሩፋት ያመቻልና ። እሳት ከዛኅላቸው (ከዝገታቸው) ሳይሳተፍ ሰባቱን መዐድናት ያጠራቸዋል ፣ መንፈስ ቅዱም ከግብራቸው ሳይሳተፍ ሁሉን ያነጻልና ‹‹ይእቲ ታነጽሕ ወኢትረስሕ›› እንዲል ። እሳት ከአንዱ ፋና አምሳ ስልሳ ፋና ቢያበሩበት ተከፍሎ የለበትም ፣ መንፈስ ቅዱም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽዓት ድረስ ሲሰጥ ይኖራልና ። ‹‹ይእቲ ትሁብ ወኢትቀብል›› እንዲል ። በእሳት ቀድሞ ሰብአ ሰዶም ሰብአ ገሞራን፥ ከእስራኤልም አንዱን ኅብር አጥፍቶበታል ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም እንዳይሉ ለምሕረት እንደ ተፈጠረ ለማጠየቅ ። አንድም ሸክላ ሠሪ ሠርታ ስትጨርስ ነቅ ያገኘችበት እንደ ሆነ እንደ ገና መልሳ ከስክሳ በውኃ ለውሳ በእሳት ታድሰዋለች ፣ ተሐድሶም በመንፈስ ቅዱስ ነውና ።
ከዚህ ላይ የተመለከትነው የአበው ማብራሪያ ስለ መንፈስ ቅዱስ በእሳት መመሰል በቂ ማስገንዘቢያ ይሰጠናል ። በተጨማሪ ስለ ርደተ መንፈስ ቅዱስ ቅ/ሉቃስ የተናገረውን ስንመለከት በእሳት ላንቃ አምሳል መሆኑም ከዚህ የራቀ ትርጉም የለውምና ከላይ የተሰጠውም ከቀደመው ጋር አንድ ነው ። የሐዋ 2 ፥ 2-3 ።
ሌሎች የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌዎች፤
በውኃ ፣ ዮሐ 7 ፥ 37-39 ። ዘካ 14 ፥ 8 ። ሕዝ 47 ፥ 1-5 ። ኢሳ 55 ፥ 1-6 ።
በርግብ ፣ ማቴ 3 ፥ 16 ። ዘፍ 8 ፥ 8-12 ።
በማኅተም ፣ 2ቆሮ 1 ፥ 22 ። ኤፌ 1 ፥ 13-14 ። 4 ፥ 30 ። ተመስሎ ይገኛል ።

ምንጭ ቃለ ጽድቅ ኦርቶዶክሳዊ

Comments (1)

ቃለህይወትን ያሰማልን በሚገባ ተብራርቶ በሚገባ ሁኔታ የቀረበ ነው። መጠየየቅ የፈለኩት ነገር ቢኖር በልጅነት ያገኘነውን የመንፈስ ቅዱስ ፀጋ እያሳደግን እንሄዳለን?በምናይነት ስራስ እናሳድገዋለን?

Comment to elias Cancel reply